ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአደጋ ስጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ በሙስና ተጠርጥረው በፖሊስ ተያዙ
የኢትዮጵያ መንግሥት የአደጋ ስጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ምትኩ ካሳ ከሙስና ጋር በተያያዘ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ብሔራዊው ቴሌቪዥን ዘገበ።
ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል በፌዴራል ፖሊስ በቁጥጥር ስር የዋሉት ዛሬ ረቡዕ ሐምሌ 06/2014 ዓ.ም. መሆኑ ተገልጿል።
በፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ጠቅላይ መምሪያ የሙስና ወንጀሎች ምርመራ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው፣ አቶ ምትኩ ለእስር የበቁት ከአንድ አገር በቀል የበጎ አድራጎት ተቋም ጋር ተባብረው ፈጽመውታል በተባለ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ነው።
በዚህም ኮሚሽነር መትኩ ካሳ “ኤልሻዳይ” ከተባለ የበጎ አድራጎት ማኅበር ባለቤት ጋር በመመሳጠር የሙስና ወንጀል እንደፈጸሙ መጠርጠሩን ፖሊስ ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ገልጿል።
ኮሚሽነሩ የበጎ አድራጎት ድርጅቱ በተለያዩ ቦታዎች ላይ የሌሉ ተፈናቃዮች እንዳሉ በማስመሰል ለሚያቀርበው ጥያቄ የተለያዩ የእርዳታ አቅርቦቶችን እንዲሰጥ አድርገዋል የሚል ክስ ቀርቦባቸዋል።
ኮሚሽነሩ በቁጥጥር ስር ከመዋላቸው በፊት ፖሊስ በአቶ ምትኩ ካሳ ላይ “ሰፊ ክትትል ሲያደርግ እንደነበረ” ገልጿል።
በተጨማሪም ይህንን ሐሰተኛ የተረጂዎች ጥያቄ ተከትሎ የሚቀርበው የእርዳታ እህልና አልባሳት በበጎ አድራጎት ድርጅቱ በኩል ተሽጦ “ለተጠርጣሪው መኖሪያ ቤት መግዛቱን” ፖሊስ በምርምራ ማረጋገጡን ረዳት ኮሚሽነር ታደሰ አያሌው መናገራቸው ተዘግቧል።
ፖሊስ ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ላይ ካደረገው ክትትል በኋላ በሙስና ተጠርጥሮ በቁጥጥር ስር እናዳዋላቸው ከመግለጹ ባሻገር፣ የእርዳታ አቅርቦቶችን በሕገ ወጥ ሁኔታ በመውሰድ ለሽያጭ አቅርቧል ስለተባለው ግብረ ሰናይ ድርጅት ያለው ነገር የለም።
ቢቢሲ ከኮምሽነሩ መታሰር ጋር ስሙ ስለተነሳው "ኤልሻዳይ" ከለተባለው በጎ አድራጎት ድርጅት ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
አቶ ምትኩ ካሳ ለበርካታ ዓመታት የአገሪቱ የአደጋ ስጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ ኮሚሽኑ በተለያዩ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ችግሮች ምክንያት ለተጎዱ ዜጎች ከአገር ውስጥና ከውጭ የሚገኘውን እርዳታ የሚያስተባብር ነው።
የአቶ ምትኩ በሙስና ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር መዋል ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በከፍተኛ ባለሥልጣን ላይ የተከሰተ የሙስና ክስ ነው።
በደቡብ ኢትዮጵያ ይርጋለም የተወለዱት፤ አቶ ምትኩ ካሳ የብሔራዊ የአደጋ ስጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ከመሆናቸው በፊት በደቡብ ክልል የምግብ ዋስትና ሥራዎች ማስተባበሪያ ክፍል ኃላፊ ነበሩ።
አቶ ምትኩ ካሳ እአአ 2019 ላይ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ ስር ተቋቁሞ በነበረው የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ውስጥ አባል ሆነው ተመርጠው ነበር።
አቶ ምትኩ ካሳ ላለፉት ሰባት ዓመታት የአደጋ ስጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር በመሆን አገልግለዋል።