ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ግምት፡ ዩናይት ከቶተንሀም፤ ሊቨርፑል ከሲቲ - ማን ያሸንፋል?
ካለፉት ስድስት ጨዋታዎች አንዱን ብቻ ያሸነፈው ማንቸስተር ሲቲ እሑድ ከሊቨርፑል ይፋለማል።
ባለፈው ሳምንት ከቶተንሀም በነበረው ጨዋታ ሁለት ለባዶ ከመመራት ተነስቶ አቻ መውጣቱ የሲቲን አቋም ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው።
የቢቢሲ ስፖርት ተንታኙ ክሪስ ሱተን ማንቸስተር ሲቲ ከየትኛውም ውድድር ርቋል ማለት አይቻልም ይላል።
በ25ኛ ሳምንት የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታዎች ሊቨርፑል ከሲቲ እንዲሁም ማንቸስተር ዩናይትድ ከቶተንሀም የሚያደርጉት ፍልሚያ ይጠበቃል። መሪው አርሰናል ደግሞ በሜዳው ሰንደርላንድን ያስተናግዳል።
ሱተን የጨዋታዎቹን ግምት እንዲህ አስቀምጧል።
ሊድስ ከኖቲንግሀም
የወራጅ ቀጣናው ፉክክር አሁን እየበረታ ይመስላል።
እኔ በበኩሌ ዎልቭስ እና በርንሊ ወርደዋል ነገር ግን ዌስት ሀም ወይስ ሌላ ሦስተኛ ቡድን ይወርዳል የሚለው ጥያቄ ነው የሚያሳስበኝ።
ሊድስ እና ኖቲንግሀም እኩል 26 ነጥብ ይዘው በመቀመጣቸው ይህ ጨዋታ ለሁለቱም ወሳኝ ነው።
ሊድስ ባለፈው ሳምንት በአርሰናል በሰፊ ጎል ቢሸነፍም በያዝነው የውድድር ዓመት በሜዳው የተሻለ የሚባል ቡድን ነው።
ኖቲንግሀም ደግሞ በተቃራኒው ከሜዳው ውጭ የተሻለ አቋም ያሳያል።
ይህ ጨዋታ ፉክክር የሚታይበት እንደሆነ እገምታለሁ። ግጥሚያውን ሊድስ እንደሚያሸንፍ አስባለሁ። ነገር ግን በአቻ ውጤት እንደሚጠናቀቅም ውስጤ ይነግረኛል።
ግምት፡ 2-1
ማንቸስተር ዩናይትድ ከቶተንሀም
ዩናይትድ ባለፈው ሳምንት ፉልሀምን ማሸነፋቸው የዕድል ጉዳይ ነው። ጨዋታው በአቻ ውጤት መጠናቀቅ ነበረበት።
ቤንጃሚን ሼሽኮ ባለቀ ሰዓት ጎል ማስቆጠሩ ለተጫዋቹ እና ለቡድኑ ደስታን አጎናፅፏል።
ቶተንሀም በበኩሉ ሲቲን አስተናግዶ በሶላንኬ ሁለት ጎሎች ከሁለት ለባዶ መመራት ተነስቶ አቻ መውጣት ችሏል። ሶላንኬ ሲሰለፍ ቶተንሀም ጥሩ ቡድን ይሆናል።
የማይክል ካሪክ ቡድን ወደፊት ሲጓዝ የተከላካይ መስመሩን ያዳክመዋል።
በዚህ ጨዋታ ሶላንኬ ጎል እንደሚያስቆጥር አስባለሁ። ነገር ግን ዩናይትድ ጨዋታውን የሚያሸንፉበት መንገድ ያገኛሉ።
ግምት፡ 2-1
ቦርንመዝ ከአስተን ቪላ
ቪላ በተከታታይ ሁለት ጨዋታዎች በኤቨርተን እና ቪላ ተሸንፈዋል። የአማካይ ክፍላቸው በጉዳት ምክንያት ተዳክሟል።
ቦርንመዝ ካለፉት አራት ጨዋታዎች ሦስቱን አሸንፈዋል። በሜዳቸው እንደመጫወታቸው የተሻለ የማሸነፍ ዕድል እንዳላቸው አስባለሁ።
ባለፈው ኅዳር በቪላ ፓርክ በነበረው ጨዋታ አስተን ቪላ ቦርንመዝን 4-0 ቢያሸንፍም ይህ ጨዋታ የተለየ ይሆናል።
ግምት፡ 2-1
አርሰናል ከሰንደርላንድ
አርሰናል በዚህ ጨዋታ ጎል የሚቆጠርበት አይመስለኝም። ካለፉት 24 ጨዋታዎች በ12ቱ ጎል አልተቆጠረበትም።
ግራኒት ዣካ በጉዳት ምክንያት የቀድሞ ክለቡን መግጠም አለመቻሉ የሚያሳዝን ነው። በመጀመሪያው ጨዋታ አርሰናልን ለመጀመሪያ ጊዜ ያርበደበዱት ሰንደርላንዶች ነበሩ።
የዣካ ልምድ ከወጣት ተጫዋቾች ጋር ተዳምሮ ሰንደርላንድ የዘንድሮው ፕሪሚዬር ሊግ ክስተት እንዲሆን አስችሎታል።
ይህ ጨዋታ ለሰንደርላንድ ቀላል አይሆንም። በዚያ ላይ ጥቋቁር ድመቶቹ ከሜዳቸው ውጭ ያላቸው አቋም ይህን ያህል የሚያስደንቅ አይደለም።
አርሰናል ምናልባትም መደናቀፍ እያሳየ ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ ሊድስን 4-0 መርታት ችሏል። ይህን ጨዋታም በቀላሉ እንደሚያሸንፉ ጠብቃለሁ።
ግምት፡ 2-0
በርንሊ ከዌስት ሀም
እኔ በርንሊ ወርደዋል ብዬ ብደመድምም የኔን ሐሳብ ውድቅ ለማድረግ ይህ ጨዋታ ጥሩ አጋጣሚ ነው።
በሜዳቸው በደረጃ ሰንጠረዡ ከነሱ አንድ ከፍ ብሎ ከተቀመጠ ቡድን ጋር ነው የሚጫወቱት። ደጋፊዎቻቸው ለረዥም ጊዜ ሲጠብቁ የነበሩትን ድል ለማጣጣም ጊዜ አሁን ሊሆን ይችላል።
እኔ ግን ይህ የሚሆነው አይመስለኝም። ዌስት ሀም ወጥ የሆነ አቋም ማሳየት ቢሳነውም በቅርብ ሳምንታት መሻሻል ይታይበታል።
ዌስት ሀም ጎል ይቆጠርባቸዋል። ነገር ግን በርንሊ ያሸንፋል ብዬ አልገምትም።
ግምት፡ 1-1
ፉልሀም ከኤቨርተን
የፉልሀሙ ሀሪ ዊልሰን በዘንድሮው የውድድር ዘመን አስደናቂ ጎሎችን አሳይቶናል። በእሑዱ ጨዋታ ግን ተሰልፎ የመጫወቱ ነገር አጠራጣሪ ነው።
ኤቨርተን ከብራይተን ጋር በነበረው ፍልሚያ 1 ለባዶ ሲመሩ ቆይተው ባለቀ ሰዓት ቤቶ ባስቆጠራት ጎል አቻ መውጣት ችለዋል።
አሰልጣኝ ዴቪድ ሞዬስ ከጎል በኋላ ደስታቸውን በመግለፃቸው ቢጫ ካርድ ማየታቸው ተገቢ ነው ብዬ አላስብም።
ይህም ጨዋታ ፉክክር የሚታይበት እና 2-1 የሚጠናቀቅ ነው ብዬ ባስብም ፉልሀም በጠባብ ውጤት ያሸንፋል።
ማርኮ ሲልቫ ከኦልድ ትራፈርድ የሆነ ነገር ይዘው መምጣት ይገባቸው እንደነበር ያስባሉ። በዚህ ሳምንት ፍልሚያ የሚገባቸውን ደስታ ያጣጥማሉ።
ግምት፡ 1-1
ዎልቭስ ከቼልሲ
ቼልሲ በካራባዎ ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ ከአርሰናል በነበራቸው ግጥሚያ ሽንፈት ቀምሰዋል። በዚህ ጨዋታ ግን ተቃራኒው ነው የሚሆነው።
ዎልቭስ ባለፈው ሳምንት ከቦርንመዝ አቻ ይወጣሉ ብዬ መገመቴ ቆጭቶኛል። ይህን ስህተት አልደግመውም።
ቼልሲ የጨዋታ መደራረብ አለበት። ባለፈው ሳምንት ከዌስት ሀም ጋር በነበረው ግጥሚያ 2 ለባዶ እየተመሩ ቆይተው በሁለተኛው አጋማሽ አሰልጣኝ ሊያም ሮዝኒዮር ባደረጉት ለውጥ 3-2 ማሸነፋቸው የሚደነቅ ነው።
የዎልቭስ አሰልጣኝ ሮብ ኤድዋርድስ በሚቀጥለው የውድድር ዘመን በሻምፒዮንሺፕ ለመጫወት ቢዘጋጅ ይሻለዋል።
ግምት፡ 1-2
ኒውካስል ከብሬንትፈርድ
ረቡዕ ከሲቲ የካራባዎ ዋንጫ ግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ያደረገውን ጨዋታ የተሸነፈው ኒውካስል የተዳከመ ይመስላል። እርግጥ አንቶኒ ጎርደንን ጨምሮ የተወሰኑ ተጫዋቾች ተጎድተውበታል።
ብሬንትፈርድ ባለፈው ሳምንት ከቪላ ያደረጉትን ፍልሚያ በሚገርም ሁኔታ ማሸነፍ ችለዋል። ሁለተኛውን አጋማሽ ሙሉ በሙሉ በ10 ተጫዋች ጨርሰው ሦስት ነጥብ ይዘው በመውጣታቸው ለአሰልጣኝ ኪዝ አንድሪውስ ምስጋና ይገባቸዋል።
ንቦቹ የተከላካይ መስመራቸው የተደራጀ መሆኑ ኒውካስል እንዴት ሰብሮ ሊገባ ይችላል የሚል ጥያቄን ጭሯል።
ሀርቪ ባርንስ እና ኢላንጋ የኒውካስልን አጥቂ መስመር ይመራሉ። ዮዋን ዊሳም የቀድሞ ክለቡን ይገጥማል።
ግምት፡ 3-1
ብራይተን ከክሪስታል ፓላስ
ፓላስ አጥቂው ዮርገን ስትራንድ ላርሰንን አስፈርመዋል። አሰልጣኝ ኦሊቨር ግላስነር ከዣን ፊሊፕ ማቴታ በተጨማሪ የአጥቂ አማራጭ አላቸው።
ለወትሮው ይህ ጨዋታ አቻ ይጠናቀቃል ብዬ ብገምትም በዚህ ጨዋታ ብራይተን እንደሚረታ አምናለሁ።
ብራይተን ባለፈው ሳምንት ባለቀ ሰዓት በተቆጠረባቸው ጎል ከኤቨርተን አቻ ቢወጡም በዚህኛው ጨዋታ ጎል የሚቆጠርባቸው አይመስለኝም።
ግምት፡ 2-0
ሊቨርፑል ከማንቸስተር ሲቲ
ፔፕ ጉዋርዲዮላ በአጥቂው ኧርሊንግ ሀላንድ ምትክ ኦማር ማርሙሽን ያሰልፉ ይሆን የሚለውን እናያለን።
ማርሙሽ በሳምንቱ አጋማሽ ኒውካስል ላይ ሁለት ጎሎች አስቆጥሯል። የአንትዋን ሴሜንዮ እና ራያን ቼርኪ መሰለፍም ትልቅ ያመጣል።
ሊቨርፑልም በተመሳሳይ አጥቂው ኡጎ ኤኪቲኬ የሚገርም አቋሙ ላይ መሆኑ እና የፍሎሪያን ቪርትዝ አቋም መሻሻል የተሻለ የልብ መተማመን የሰጣቸው ይመስላል።
ሲቲ ጎል የሚያስቆጥሩበትን አጋጣሚ ይፈጥራሉ። ሊቨርፑልም በተመሳሳይ የጎል ዕድል የመፍጠር አቅም አላቸው። በዚህ ጨዋታ በርካታ ጎሎች እንደምናይ እገምታለሁ።
ግምት፡ 2-2