ተመድ በጋዛ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ያቀረበውን ጥሪ አሜሪካ ለስድስተኛ ጊዜ ውድቅ አደረገች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው ምክር ቤት በጋዛ በአስቸኳይ የተኩስ አቁም እንዲደረግ እና ታጋቾች አንዲለቀቁ በመጠየቅ ያቀረበውን ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብን አሜሪካ ለስድስተኛ ጊዜ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብቷን ተጠቅማ ውድቅ አደረገች።
የአሜሪካ የመካከለኛው ምሥራቅ ልዑክ ምክትል ኃላፊ ሞርጋን ኦርታገስ የቀረበው ረቂቅ ሐማስን አይኮንንም ወይም እስራኤል ራሷን የመከላከል መብት እንዳላት ዕውቅና አይሰጥም ብለዋል።
የጸጥታው ምክር ቤት 14 አባል አገራት በሙሉ የቀረበውን ረቂቅ የውሳኔ ሃሳብ ደግፈው ድምጽ ሰጥተዋል።
ረቂቅ የውሳኔ ሃሳቡ በጋዛ ያለውን የሰብዓዊ ሁኔታ "አስከፊ" ሲል የገለፀው ሲሆን እስራኤል የጣለችውን ገድብ እንድታነሳ ጠይቋል።
የጸጥታው ምክር ቤት የውሳኔ ሃሳብ የቀረበው የመንግሥታቱ ድርጅት ሰብዓዊ ቢሮ እስራኤል ወታደራዊ ጥቃቷን እያጠናከረች እና እያሰፋች መምጧቷን ተከትሎ በጋዛ ከተማ ሰላማዊ ዜጎችን ለመድረስ ያለው የመጨረሻው አማራጭ እየወደመ ነው ሲል ካስጠነቀቀ በኋላ ነው።
በዓለም አቀፍ መድረክ እስራኤል እና አጋሮቿ በተደጋጋሚ እየተገለሉ ነው።
ከምክር ቤቱ ስብሰባ በፊት ኦርታገስ በውሳኔ ሃሳቡ ላይ የዋሺንግተን ተቃውሞ "እንደ ድንገተኛ ነገር ሊታይ አይገባም" ብለዋል።
"ሐማስን መኮነን ወይም እስራኤል ራሷን የመከላከል መብት እንዳላት ዕውቅና መስጠት አልቻለም፤ እንዲሁም ሐማስ የሚያቀርበውን እና በአሳዛኝ ሁኔታ በምክር ቤቱ ተቀባይነት እያገኘ የመጣውን ሐሰተኛ ትርክት እውቅና የሚሰጥ ነው" ብለዋል።
ከድምጽ አሰጣጡ በኋላ የመንግሥታቱ ድርጅት አባላት ወዲያውኑ ቅሬታቸውን ገልጸዋል።
በተባበሩት መንግሥታት የፍልስጤም አምባሳደር ሪያድ መንሱር የአሜሪካን ውሳኔ "በጣም የሚጸጽት እና የሚያሳምም" ሲሉ የገለፁት ሲሆን የጸጥታው ምክር ቤት "በዚህ ጥፋት ውስጥ ተገቢውን ሚና" እንዳይጫወት ይከለክላል ብለዋል።
የፓኪስታን አምባሳደር አሲም አህማድ ድምጽን በድምጽ የመሻር መብትን "የዚህ ምክር ቤት ጨለማው ቅጽበት " ሲሉ ገልጸውታል።
አክለውም "ዓለም እየተመለከተ ነው። የልጆች ልቅሶ ልባችንን ዘልቆ ሊሰማን ይገባል" ብለዋል።
የአልጄሪያ አምባሳደር አማር ቤንድጃማ የፍልስጤም ሕዝብን ይቅርታ ጠይቀዋል።
"የፍልስጤም ወንድሞቻችንን፣ የፍልስጤም እህቶቻችን ይቅር በሉን።"
"ይቅር በሉን ምክንያቱም ዓለም ስለመብቶች ያወራል ነገር ግን ፍልስጤማውያንን ይከለክላል። ይቅር በሉን ምክንያቱም ጥረታችን፣ ያለመታከት ያደረግነው ጥረት በእምቢተኝነት ምክንያት እርባና ቢስ ሆኗል።"
ይህ የጸጥታው ምክር ቤት ድምጽ አሰጣጥ የተካሄደው የዓለም መሪዎች አጠቃላይ ጉባዔ ከመካሄዱ ጥቂት ቀናት ቀድም ብሎ ነው።
በዚህ የዓለም መሪዎች ጉባዔ ላይ የፍልስጤም ጉዳይ ዋነኛ መነጋገሪያ ይሆናል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ዩኬን ጨምሮ ሌሎች አገራት ለፍልስጤም አገርነት እውቅና ይሰጣሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በጋዛ የእስራኤል ጦር በሚያካሄደው ዘመቻ የተነሳ ፍልስጤማውያን አሁንም በማያቋርጥ መፈናቀል ውስጥ ናቸው።
የእስራኤል ምድር ጦር በጋዛ በታንክ የታገዘ ጥቃቱን ለሦስተኛ ቀን አጠናክሮ ቀጥሏል።
የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብዓዊነት ቢሮ ቃል አቀባይ ኦልጋ ቼሬቭኮ በጋዛ ከተማ ያለውን ሁኔታ "አውዳሚ እና አሰቃቂ" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በደቡባዊ እስራኤል ድንገተኛ ጥቃት ሰንዝሮ 1,200 ሰዎችን ከገደለ እና 251 ካገተ በኋላ የእስራኤል ጦር መጠነ ሰፊ ወታደራዊ ዘመቻ እያካሄደ ነው።
በጋዛ ጤና ሚኒስትር መረጃ መሠረት የእስራኤል ጦር ወታደራዊ ዘመቻ ከጀመረ ጊዜ አንስቶ 65,141 ፍልስጤማውያን ተድለዋል።
435 ሰዎች በምግብ እጥረት እና ረሃብ መሞታቸውን ሚኒስቴሩ ጨምሮ ገልጿል።












