የአሜሪካ የጦር መርከብ በጋዛ ወደብ ለመገንባት ወደ መካከለኛው ምስራቅ ጉዞ ጀመረች

የፎቶው ባለመብት, US CENTRAL COMMAND
የአሜሪካ ግዙፍ የጦር መርከብ በጋዛ ጊዜያዊ ወደብ ለመገንባት ወደ መካከለኛው ምስራቅ ጉዞ መጀመሯን የአገሪቱ ጦር አስታወቀ።
ለወደብ ግንባት ግብዓቶችን የጫነችው ጀነራል ፍራንስ ኤስ ቤሰን የተባለችው መርከብ ከትናንት በስቲያ ቅዳሜ ከአሜሪካዋ ቨርጂኒያ ተነስታለች።
የመርከቧ ጉዞ የተሰማው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አሜሪካ ለጋዛ ነዋሪዎች የሰብዓዊ እርዳታ ለማቅረብ ተንሳፋፊ የሆነ ጊዜያዊ ወደብ እንደምትገነባ ካስታወቁ በኋላ ነው።
የተባበሩት መንግሥታት በእስራኤል እና ሐማስ ጦርነት ምክንያት በጋዛ ሕጻናት በረሃብ እየሞቱ ነው ማለቱ ይታወሳል።
ትናንት እሁድ አሜሪካ እና ጆርዳን ሩዝ፣ ዱቄት፣ ፓስታ እና የታሸጉ 11ሺህ 500 ምግቦች ከአየር ላይ መጣላቸውን የአሜሪካ ጦር ገልጿል። ይሁን እንጂ የእርዳታ ምግቦችን ከአየር ላይ መጣል ፈታኝ ሆኖ ቆይቷል።
ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ላይ ከአየር ላይ የተጣለ እርዳታ ፓራሹት ባለመስራቱ አምስት ሰዎችን መግደሉ ተገልጿል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም የሰብዓዊ እርዳታ ሠራተኞቹ ላይ ተኩስ ከተከፈተ እና ዘረፋ ካጋጠመው በኋላ በጋዛ የሚያደርገውን የምግብ እርዳታ አቋርጧል።
የመርከቧን ጉዞ መጀመርን አስመልክቶ የአሜሪካ ጦር በኤክስ ገጹ ላይ የጦር መርከቧ "ለጋዛ መሠረታዊ የሆኑ የሰብዓዊ ቁሶችን ለማቅረብ የሚያስችል ጊዜያዊ ወደብ መገንባት የሚያስችል መሳሪያዎችን ጭናለች" ብሏል።
ፔንታጎን እንደሚለው 1ሺህ ወታደሮች ተሳታፊ የሚሆኑበት ሥራ በ60 ቀናቶች ውስጥ ይጠናቀቃል ብሏል።
ሰብዓዊ እርዳታ አቅራቢ ድርጅቶች ግን በጋዛ ያሉ ሰላማዊ ሰዎች ያለ አስቸኳይ እርዳታ ያን ያክል ጊዜ መቆየት አይችሉም እያሉ ነው።
ጋዛ በሥራ ላይ ያለ ወደብ የሌላት ሲሆን በዙሪያዋ ያለው የውሃ አካል ጥልቅ ስላልሆነ ግዙፍ መርከቦችን ማስተናገድ አይችልም።
ሐማስ መስከረም 26/2016 ዓ.ም. በእስራኤል ላይ ድንገተኛ ጥቃት መሰንዘሩን ተከትሎ እስራኤል ባለፉት ወራት በአየር፣ ከባሕር እና በእግረኛ ኃይል በጋዛ ድብደባዎችን ስታደርግ ቆይታለች።
በሐማስ የሚመራው የጋዛ ጤና ሚኒስቴር እንደሚለው ከሆነ እስካሁን ድረስ አብዛኛዎቹ ሕጻናት እና ሴቶች የሆኑ 30ሺህ 900 ሰላማዊ ሰዎች በጋዛ ተገድለዋል።
በጦርነቱ ከሚገደሉት ሰዎች በተጨማሪ ጦርነቱ በጋዛ እየከፋ የመጣ የሰብዓዊ ቀውስ ፈጥሯል። የመንግሥታቱ ድርጅት እንደሚለው ከሆነ ከአጠቃላይ የጋዛ ነዋሪ አንድ አራተኛ የሚሆነው ግማሽ ሚሊዮን ገደማ ሕዝብ ለከፍተኛ የምግብ እጥረት አደጋ ተጋልጧል።
የሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረስ ምዕራባውያን አገራት ጋዛ መድረስ ስለሚቻልበት ሁኔታ አማራጮች እንዲፈጠሩ እስራኤል ላይ ጫናዎችን ሲያሳድሩ ቆይተዋል።
የተመድ ገለልተኛ የባለሙያዎች ቡድን ባለፈው ሳምንት እስራኤል ሆነ ብላ በጋዛ የሚገኙ ፍልስጤማውያንን እያስራበች ነው ሲል ሪፖርት አውጥቶ ነበር።












