በእምነታቸው ምክንያት በተነሳባቸው ተቃውሞ ቤታቸውን ለመሸጥ የተገደዱት ሕንዳውያን ሙስሊም ጥንዶች

ሙስሊሞች ቤት መግዛታቸው ያስነሳው ተቃውሞ

የፎቶው ባለመብት, AK Mishra

በሕንድ የሂንዱ እምነት ተከታይ ጎረቤቶች አዲስ ቤት ገዝተው የገቡ ሙስሊም ጥንዶችን አላስኖር ስላሏቸው ቤታቸውን ሸጠው ለመውጣት ተገደዋል።

ከጎረቤቶቻቸው እዚህ አትኖሩም በሚል ተቃውሞ በመበርታቱ ነው ጥንዶቹ ቤታቸውን የሸጡት።

ይህ አስገራሚ ሁኔታ የተፈጠረው ሰሜናዊ ሞራዳባድ ከተማ ውስጥ ቲዲአይ በተሰኘው ቱጃሮች እና ቅንጡ መኖሪያ ቤቶች በሞሉት ስፍራ ነው።

በዚያች አካባቢ አንድ ቤት ለሽያጭ ቀርቧል የሚል ዜና መሰማቱን ተከትሎ ከፍተኛ ተቃውሞ ተነሳ። ተቃውሞውን ያስነሳው ቤቱ መሸጡ አልነበረም።

ዶ/ር አሾክ ባጃጅ የተባሉት የቤቱ ባለቤት ጎረቤቶቻቸውን ሳያማክሩ ቤታቸውን ለሙስሊም ቤተሰቦች መሸጣቸው ነው የተቃውሞ ሰልፍ ለመውጣት ምክንያት የሆናቸው። የተቃውሞ ሰልፉ ቪዲዮ በማኅበራዊ ሚዲያዎች መጋራቱን ተከትሎ በሕንድ ከፍተኛ ቁጣ አስነስቷል።

"ከቤተ አምልኳችን ፊት ለፊት ሙስሊም ቤተሰቦች መኖራቸውን የምንቀበለው ጉዳይ አይደለም። ይህ የሴቶቻችን ደኅንነት ጥያቄ ነው" ብላለች አንዲት ነዋሪ።

"ሽያጩ እንዲዘረዝ እንፈልጋለን። የከተማዋ አስተዳደር በአዲሶቹ ባለቤቶች ስም የተደረገውን የቤት ምዝገባ እንዲሰረዝ ጠይቀናል። የሌላ እምነት ተከታይ የሆኑ ሰዎች እዚህ መጥተው እንዲኖሩ መፍቀድ አንችልም። በዚህ ቤት እንዲኖሩ አንፈቅድላቸውም። እስካልወጡ ድረስ በተቃውሟችንን እንቀጥላለን" ስትል ግለሰቧ አክላለች።

በርካታ የአካባቢው ነዋሪዎች ቅሬታቸውን ለማቅረብ የወረዳው ዳኛ ቢሮ ሄደው ነበር። በቢሮውም ቤቱን በሸጠው ግለሰብ ዶ/ር ባጃጅ እና ሙስሊም ጥንዶቹ ላይ መፈክሮች አሰምተዋል።

የተቃውሞ ሰልፎቹ ያለሙትን ውጤት ማግኘት ችለዋል። ቤቱን የሸጡት ዶ/ር ባጃጅ ለቢቢሲ እንደተናገሩት በከተማዋ ተወካዮች አደራዳሪነት አዲሶቹ ሙስሊም ባለቤቶች ቤቱን እንዲሸጡት ውሳኔ ላይ ተደርሷል ብለዋል።

ቤቱን የሚሸጡት በዚያው አካባቢ ለሚኖሩ የሂንዱ እምነት ተከታይ ቤተሰቦች ነው። በከተማዋ የዓይን ሆስፒታል ያላቸው እና በዚያ ሰፈር ከስድስት ዓመት በላይ የኖሩት ዶክተር ባጃጅ ቤታቸውን የሸጡት ዶክተር ለሆኑ ባል እና ሚስት ሲሆን፣ ለ40 ዓመታት ያህል እንደሚተዋወቁም ይናገራሉ።

የተነሳባቸውን ተቃውሞ ተከትሎ ሙስሊሞቹ ጥንዶች ወደ መኖሪያ ቤታቸው ለመግባት ምቾች አልተሰማቸውም ይላሉ።

ጸረ- እስልምናን የሚቃወም መልዕክት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ከቤት ሽያጩ ጋር ተያይዞ የተነሳው ቁጣ አስፈላጊ እንዳልነበረ ጠቅሰው፣ አገራዊ ዜና ይሆናል ብለው በጭራሽ እንዳልጠበቁትም ገልጸዋል።

ነገር ግን በሕንዳውያን ሙስሊም ማኅበረሰብ ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች የሂንዱ አክራሪ የሚባሉት የጠቅላይ ሚኒስትር ናሬንድራ ሞዲ መንግሥት መምጣትን ተከትሎ ባለፉት አስር ዓመታት ውስጥ እንደጨመሩ በርካታ ማስረጃዎች አሉ።

ፀረ ሙስሊም የጥላቻ ትርክቶች በተደጋጋሚ ይሰማሉ። የጠቅላይ ሚኒስትሩ ገዢ ፓርቲ ባህራቲያ ጃናታ ፓርቲ (ቢጄፒ) ከሚመራቸው ግዛቶች ነው አብዛኞቹ እነዚህ ጥቃቶች እና መገለሎች የሚሰሙት።

ለሙስሊም ባለቤቶች ቤት መሸጣቸው ቁጣ የቀሰቀሰባት ሞራዳባድ ከተማን የሚመራት ቢጄፒ ፓርቲ ነው።

ገዢው ፓርቲ ይህንን የሚነሱበትን ክሶች ያስተባብላል።

በሞራዳባድ የተፈጠረው ክስተት "የሃይማኖት ጽንፈኝነት መሬት ላይ መውረዱን እና ስር እየሰደደ መሆኑን ማሳያ ነው" ሲሉ በዴልሂ ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ እና የሕዝብ ፖሊሲ ፕሮፌሰር የሆኑት ታንቪር አኢጃዝ ይናገራሉ።

የቤት ሽያጩ ተቃውሞ የተጀመረው አዲስ የሚገቡትን ሙስሊም ጥንዶች ከጎረቤቶቻቸው ጋር መልካም ግንኙነት እንዲኖራቸው በማለት እንዲተዋወቁ ማድረጋቸውን ተከትሎ እንደሆነ ዶ/ር ባጃጅ ይናገራሉ።

በዚያው ስፍራ የሚኖሩ ሙስሊም ቤተሰቦች እንዳሉ የሚገልጹት ዶ/ር ባጃጅ፤ የአሁኑ ተቃውሞ መነሻው አይታወቅም ይላሉ።

"ከሙስሊም ጎረቤቶቻችን ጋር ጥሩ ግንኙነት ነበረን" ይላሉ።

"ውዝግቡ የከተማዋን ትስስር እና ገጽታ እየቀየረ ነው። በዚህ ቤት ሽያጭ ብጥብጥ መፍጠር አላሰብንም። እንዲህ ዓይነት ሽያጭን የሚከለክል ሕግ የለም" ብለዋል።

በዚህ መኖሪያ ቤት ሰፈር ሽያጭ የሚያጸድቅ የነዋሪዎች ማኅበር አልነበረም ይላሉ። "አሁን ያንን ማኅበር ወደማቋቋሙ መሄዳቸው አይቀርም" ሲሉ ዶክተር ባጃጅ ይገልጻሉ።

የሂንዱ እምነት ተከታዮች በሚበዙበት ሞራዳባድ ከተማ ሙስሊሞች ቤቶች መግዛታቸው ተቃውሞ ሲገጥም ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ከሦስት ዓመታት በፊት ሁለት ሙስሊሞች ከሂንዱዎች ቤት መግዛታቸውን ተከትሎ ነዋሪዎች እና ጽንፈኛ የሚባሉ የሂንዱ ድርጅቶች ተቃውሟቸውን አሰምተዋል።

በገጠሪቷ ሕንድ በእምነት እና በመደብ ክፍፍል ተለያይቶ የመኖሪያ አካባቢዎችን መመሥረት የተለመደ ነው።

ከተሞች ከተለያዩ እምነቶች እና መደቦች የመጡ ማኅበረሰቦችን በአንድነት የሚያቅፉበት ነው ተብሎ ይታሰብ ነበር። ነገር ግን ሕህንድ የሚታየው እውነታ በከተሞችም ዘንድ የተለያዩ መገለሎች የሚታዩበት እንደሆነ አሳይቷል።

በተለይም እንደ ሙስሊሞች ባሉ አናሳ ማኅበረሰቦች ላይ የሚደረጉ መድልኦዎች በበርካታ የሕንድ ከተሞች ውስጥ የተለመዱ ናቸው። በርካታ የመኖሪያ ቤት ማኅበራት አትክልት ብቻ ነው መመገብ የሚቻለው የሚሉ ጥብቅ መመሪያዎችን በማውጣት ያገሏቸዋል።

እንደ ጉጅራት እና ማሃራሽትራ ባሉ ግዛቶች እንዲሁም በመዲናዋ ዴልሂ ሂንዱዎች በሰፈሩባቸው አካባቢዎች ቤቶችን መከራየትም ሆነ መግዛት ፈታኝ ሆኖብናል ይላሉ። ከጥቂት ዓመታት በፊት የቦሊውድ ተዋናዩ ኤምራን ሃሽሚ በቦምቤይ አፓርታማ ለመግዛት በእስልምና እምነቱ ምክንያት መከልከሉን መግለጹን ተከትሎ መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

በሞራዳባድ የፈለጉትን ቤት ገዝተው ለመኖር ያልቻሉት ሙስሊም ጥንዶች ጉዳይ "አድሎአዊ እንዲሁም "ፍጹም ኢ- ሕገ መንግሥታዊ ነው" ሲሉ ፕሮፌሰር አኢጃዝ ያስረዳሉ።

"ይህ መሠረታዊ እና ሕጋዊ መብቶቻቸውን የሚጥስ ነው። የአንድን ሰው የእኩልነት እና የነጻነት መብት የሚገረስስ ነው እናም እንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ከጨመሩ የሕንድ ሕገ መንግሥት ላይ አደጋ ይጋርጣል" ይላሉ።

ፕሮፌሰሩ ሕገ መንግሥቱ ለችግር ተጋላጭ ናቸው ተብለው የሚታሰቡትን ሴቶች እንዲሁም ዳሊትስ የተባሉትን የሚገለሉ ማኅበረሰቦች የመጠበቅ ልዩ መብቶች አስቀምጧል።

ነገር ግን "በሕንድ ውስጥ በከፍተኛ ሁኔታ ተጋላጭ የሆኑትን ሙስሊሞች የመጠበቅ መብትን አላስቀመጠም" ሲሉ ፕሮፌሰሩ ይጠይቃሉ።

በዚህች ከተማ የተፈጠረው ክስተት በአገሪቱ የሰፈነውን ፀረ-ሙስሊም ሁኔታ ያጋለጠ ሲሆን በርካቶችም ቁጣቸውን ወደ ማኅበራዊ ሚዲያ ገጾች ወስደውታል።

"እንኳን ወደ አዲሲቷ ሕንድ በሰላም መጣችሁ" ሲል ነበር ኮሚኩ አካሽ ባኔርጄ በምጸት በኤክስ ገጹ ላይ መልዕክቱን ያሰፈረው።

"አንድ ዶክተር ለሌላ ዶክተር ቤቱን ሸጠ። ለምንድን ነው ይሄ ተቃውሞም/ቁጣ የሚያስነሳው?" ሲል አክሎ ይጠይቃል።

"እንደ አገር ብዝኃነትን የምናቅፍ እንደሆንን ስንመካ እንሰማለን። እነዚህ ክስተቶች ሊያሳፍሩን ይገባል" ሲሉ የሕንድ ኮሚኒስት ፓርቲ የፓርላማ አባል ጆን ብሪትስ ተችተዋል።

ጥንዶቹ ላይ ተቃውሟቸውን ያሰሙት "ስም የሌላቸው፣ ፊታቸው የማይታይ ግለሰቦች አልነበሩም። ጭፍን ጥላቻቸውን እና ፀረ-ሙስሊምነታቸውን በአደባባይ ለማሳየት ያልፈሩ እና የማያፍሩ ግለሰቦችን አይተናል" ሲሉ አንድ ግለሰብ በኤክስ ገጽ አስፍረዋል።