ለኢትዮጵያውያን፣ ለየመናውያን እና ለኤርትራውያን የሥራ ዕድል የፈጠረው ስደተኛ

ብርሃነ ወልዳይ በ2010 ዓ.ም የትውልድ አገሩን አክሱምን ለቆ ሲወጣ የተሻለ ህይወት እና የወደፊት ተስፋ ነበረው።
ቀልቡና እግሩ ወደ ስደት ከመሸፈቱ በፊት የኔ የሚለውና የሚተዳደርበት ስራ እንደነበረው ይናገራል። "አለኝ፤ ያለኝ ይበቃኛል. . .” ብሎ እንዳይቀጥልበት ግን ትልቅ ምክንያት ነበረው።
“ለስደት የሄድኩት ነገሮች እየከበዱኝ ስለነበር ነው። በርግጥ የብረ ታብረት ሱቅ እና ትንሽ ምግብ ቤት ነበረኝ። ግን መሥራት አልቻልኩም። ከአስተዳዳሪዎች በሚደርስብኝ ጫና ለመስራት ተቸገርኩ። እኔ የሰማዕት ልጅ ነኝ፤ ወንድሞቼ የተሰዉ እኔም ራሴ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ደሜን ያፈሰስኩ ነኝ። ነገር ግን በአገሬ ላይ የመሥራት ዕድል የሰጠኝ አካል አልነበረም” በማለት ስደትን እንደ አማራጭ የወሰደበት ምክንያት ያስረዳል።
ያኔ ለስደት ሲነሳ ከጓደኞቹ እና ከቤተሰቦቹ "ይህን ስራ ጥለህ የት ልትሄድ ነው?" የሚል ጥያቄ የቀረበለት ብርሃነ “ወደ አውሮፓ እሄዳለሁ” የሚል አጭር መልስ መስጠትን ነበር የመረጠው። በመጨረሻም የነበረውን ሀብት አሰባስቦ ከወላጆቹ የወረሰውን ቤት ሳይቀር ሸጦ ወደ ስደት አቀና።
ከቤተሰቡና ከአካባቢው ተለይቶ ጉዞ ጀመረ። ነገር ግን ለጓደኞቹ “አውሮፓ” እንዳለው ሳይሆን አቅጣጫው በህገወጥ መንገድ በጂቡቲ በኩል ወደ የመንና ሳዑዲ አረቢያ ሆነ።
በተለይ በበረሃና በባህር የሚደረግ የስደት ጉዞ አስከፊና እና ግብር የሚከፈልበት ነው። ብርሃነ እንደሚለው “የዕድል ጉዳይ ሆኖ” ከሞት ጋር ፊት ለፊት በመጋፈጥ የተሻገረውን ከባድና ለመከራ የሚያጋልጥ የስደት ጉዞን አልፎ የመን ገባ።
ብዙዎች በጥምና በረሃብ መንገድ ላይ የሚቀሩበት፣ ታጣቂዎችና ህገወጥ አስጋሪዎች ስቃይ የሚያደርሱበትን ሁኔታ አልፎ የመን ሲገባ ፈታኝ ህይወት ይጠብቀኛል ብሎ እንዳላሰበ ይናገራል። የሥራ እድል በማግኘቱ ኑሮውን እዚያው አደረገ።
"በሕይወቴ ሰርቶ በመኖር የማምን ሰው ስለሆንኩ እዚያ ሄጄም ሥራ አላጣሁም። በአንድ ትልቅ ድርጅት ተቀጠርኩ። በስሬ እስከ 300 የሚደርሱ ሰራተኞችን አስተዳድር ነበር። ጥሩ ህይወት ነበረኝ፤ መኪናም ነበረችኝ” ይላል።
"ሌላ ተስፋን ለነገ. . ."
በየመን ህጋዊ የመኖርያና የሥራ ፈቃድ አግኝቶ ለዓመታት ሲሰራ የቆየው ብርሃነ የመን ውስጥ የሚካሄደው ጦርነት እየተባባሰ በመሄዱ ስደተኞች ወደ አገራቸው የሚመለሱበት እድል እንደተፈጠረ ያስታውሳል። ከዚያም እሱና ቤተሰቡ እድሉን ተጠቅመው በመርከብ ተሳፍረው ወደ ጂቡቲ ተመለሱ።
“ብዙ ስደተኞች በመርከብ ተመለስን። በወቅቱ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም በግላቸው አቀባበል አድርገውልናል። ልጆቼን አቅፎ ከመርከቧ አወረደን” ሲል ያስታውሳል።
በመልካም አስተዳደር እጦትና ሲደርሱበት በነበሩ ጫናዎች አገሩን ጥሎ ስለወጣ ግን ወደ ኢትዮጵያ ተመልሶ ኑሮውን ሊመሰረት ፍላጎት አልነበረውም። ይልቁንም ጂቡቲ ቀዳሚ ምርጫው ሆና ስላገኛት እዛው ቀርቶ መጣጣር ጀመረ። በተለያዩ ድርጅቶች ተቀጥሮ ሲሰራ ከቆየ በኋላ ባጠራቀመው ገንዘብ የራሴ የሚለው ስራ ለመስራት ወሰነ።
“በጂቡቲ ውስጥ በተለያዩ ድርጅቶች ተቀጥሬ እሰራ ነበር። ከትላልቅ ኩባንያዎች እስከ ባንክ ድረስ ሠርቻለሁ። የኤርትራውያን ንብረት በሆነው ትልቅ ኩባንያ ውስጥም ሰርቻለሁ። ከዚያ በኋላ ደህና ገንዘብ ስላጠራቀምኩ በቦቴ ሰፈር [በጂቡቲ ከተማ አበሾች የሚበዙበት ሰፈር] ሬስቶራንትና ጋራዥ ከፈትኩ። እርግጥ ነው፣ በባዕድ አገር ሁሉም ነገር ምቹ አይደለም፤ ነገር ጂቡቲ ውስጥ ህግን እና ስርዓትን ተከትለህ ከሰራህ ብዙም የሚከብድ ነገር የለም። በሌላ በኩል የሰራህበትን ክፍያ እስከ መከልከል የሚደርሱም አሉ” ይላል።
ሥራውን ሲጀምር ብዙ ፈተናዎች ገጥመውታል። የጀመራቸውን ሥራዎች ዘጋግቶ ወደ አገሩ ለመመለስ የወሰነባቸው አጋጣሚዎችም እንደነበሩ ያስታውሳል። ሰራተኞች ከማጣት እስከ ለቤት ኪራይ የሚከፍለው ማጣት የመሰሉ ከባድ ፈተናዎቹ ነበሩ።
"ተስፋ ሳትቆርጥ ለነገ ሌላ ተስፋ ሰንቀህ መቀጠል አለብህ። ይህንን ድርጅት ለማቋቋም እና ለማሳደግ በ100 የጂቡቲ ፍራንክ ፓስታ የበላሁበትና እጅግ ጠባብ የቆርቆሮ ቤት ተከራይቼ ያሳለፍኩትን ጊዜ አልረሳውም። ዛሬ ለደረስኩበት መሰረት ለመጣል አስቸጋሪ ሁኔታዎችን አሳልፌያለሁ። የምትፈልግበት ቦታ ለመድረስ ፈተናዎችን ማለፍ ይጠበቅብሃል” ሲል ያሳለፈውን ይገልጻል።
የትግራይ ጦርነት በተቀሰቀሰበት ወቅት በማንነቱ ምክንያት ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታዎችን እንዳሳለፈና ታድኖ እንደታሰረ የሚናገረው ብርሃነ ያኔ ጂቡቲ ውስጥ የነበሩ የትግራይ ተወላጆች ተስፋ የቆረጡበት ወቅት እንደነበር ያስታውሳል።
“እኔ ከአንድ ወር በላይ ታስሬያለሁ። የሚመጡ ስደተኞች እረዳ ነበር። [የትግራይ ተወላጆች] የትራንስ ሾፌሮች እዚህ ችግር ሲያጋጥማቸው የሚያስፈልጋቸውን ነገር አደርስላቸው ነበር። በዚ ምክንያት ደግሞ ‘ይሄ ጁንታ፡ መሳርያ እያደረሰ ነው’ እየተባልኩ መከራ ይደርስብኝ ነበር። በጩቤ እስከመወጋት ደርሻለሁ። እርጉዝ የነበረችው ባለቤቴ ሆዷ ተመትታ እርግዝናው ተጨናግፏል” ይላል።
ይህን ሁሉ ተቋቁሞ በጦርነቱ ምክንያት ከትግራይ ተሰድደው የሚመጡ ወገኖቹን በተቻለው መጠን ማገዝና ማስተባበር ቀጠለ።

እሳት ያወደመው 50 ሚሊዮን ፍራንክ
ብርሃን መጀመርያ የከፈታቸው ድርጅቶች ሙሉ በሙሉ በእሳት በመውደማቸው የተነሳ ለቅቆ አሁን ወዳለበት ከገባ አምስት ወራት ያህል ተቆጥረዋል።
“በቦቴ ሰፈር ቢያንስ ለሰባት ዓመታት ኖርያለሁ። እዚያ አክሱም ሬስቶራንት የሚባል ምግብ ቤትና ትልቅ ጋራዥ ነበረኝ። ጥሩ እየሰራሁ ብዙ ሰራተኞችን አስተዳድር ነበር። አጋጣሚ ሆኖ ግን የእሳት ቃጠሎ ተነሳ፤ ከ50 ሚሊዮን በላይ የጂቡቲ ፍራንክ (300,000 ዶላር የሚጠጋ) የሚገመት ንብረቴ ተቃጠለ” ይላል።
በሁለቱም ድርጅቶቹ በተለይም በጋራዡ ውስጥ ኢትዮጵያውያን፣ ኤርትራውያንና የመናውያን ስደተኞችን ቀጥሮ ያሰራ ነበር። እሳቱ ንብረቱን ሁሉ ሲያወድመው ብርሃነን ብቻ ሳይሆን ሰራተኛውን በሙሉ ያሳዘነ ክስተት ነበር።
አደጋው ከተከሰተ በኋላ ግን ብርሃነ ተስፋ ቆርጦና አንገቱን ደፍቶ መቀመጥን አልመረጠም። ጥርሱን ነክሶ በእሳት ያጣውን ለመተካት መስራት ጀመረ። የስራ እድል ያገኙ ሰራተኞቹም "ከጎንህ ነን" ብለው ያለምንም ክፍያ ድርጅቱን ሌላ ቦታ ለማቋቋም ሌት ተቀን ተረባረቡ።
“እነዚህ የምታያቸው መኪኖች በጦርነቱ ወቅት መስታወታቸው በድንጋይ ረግፏል። አሁንም ድረስ ያልተጠናቀቁ የፍርድ ቤት ጉዳዮች አሉ። እዛ ቦታ እያለሁ ብዙ ፈተናዎች ይገጥሙኝ ነበር። ከዚያም ከእሳት አደጋው በኋላ ቦታውን ለመልቀቅ ወሰንኩ” በማለት አዲስ በተከራየው ግቢ ውስጥ ስራውን እንደቀጠለ ይናገራል።
አክሎም “ምናልባት እንደሌላው ሰው ብሆን ኖሮ በቃጠሎው በወደመው ንብረት ተስፋ ቆርጬ መንገድ ላይ እወድቅ ነበር። ይህ አደጋ ያጋጠመው ሰው ችሎ ቆሞ የሚሄድ አይመስለኝም። እኔ ግን ከአደጋው ማግስት ጀምሮ አስፈላጊውን መሳሪያ ወደዚህ አዲስ ቦታ አምጥቼ ስራዬን ቀጠልኩ። የሚገርምህ አሁን ይህንን በኪራይ የያዝኩትን መሬት ገዝቼ ስራዬን ለማስፋት እቅድ አለኝ” ይላል።

የማይጨበጥ ተስፋን ከመጠበቅ ያገኙትን እየሰሩ መኖር
ጀማል ዑመር ኤርትራዊ ነው። ከአገሩ ከተሰደደ ዓመታትን አስቆጥሯል። በየመን ዓመታትን ያሳለፈው ጀማል ሀገሪቱ ላይ የነበረውን ጦርነት ተከትሎ ወደ ጂቡቲ ተመለሰ። ከስደት ወደ ስደት የሆነ ኑሮው ሊመቸው ስላልቻለ ችግር ውስጥ ወደቀ።
“በ2015 ነው ወደ ጂቡቲ የመጣሁት። ስደተኛ ካምፕ ገብቼ ለስድስት ዓመታት ከየመናውያን ጋር ተቀመጥኩ። ሥራ ፍለጋ ወደ ከተማ ስመጣ ብርሃነ ጋራዥ ውስጥ በያጅ ሆኜ መሥራት ጀመርኩ። ከብርሃነ ጋር የመን ውስጥ አንድ ካምፕ ነበርን። አብረን እንበለና እንጠጣ ነበር። እሱ ከየመን እኛን ቀድሞ መጥቶ ነው ይህንን ስራ የጀመረው” ይላል።
ወደ ጂቡቲ ሲመለስ በወቅቱ የሚያውቀውን ሰው ማግኘት ባለመቻሉ የተቸገረው ጀማል ካምፕ ውስጥ ተቀምጦ አነስተኛ ድጋፍ እየጠበቀ ከመኖር ከጠባቂነት ወጥቶ በሙያው እየሰራ መኖር የሚችልበትን የተሻለ ዕድል ብርሃነ እንደፈጠረለት ይናገራል።
“ብርሃነ ወደዚህ አገር ከመጣ በኋላ በሙያው ተቀጥሮ ይሰራ ነበር። ከዚያም ራሱን ችሎ ድርጅት ከፈተ። ከካምፑ ለመጡ ስደተኞች የስራ እድልን ፈጥሯል። በመሃል ግን ወደ 50 ሚሊዮን የሚጠጋ (የጂቡቲ ፍራንክ) ንብረቱ በእሳት ወድሟል። እሱ ግን ተስፋ አልቆረጠም። ቦታ ተከራይቶ ወደዚህ በመምጣት ስራውን ቀጠለ፤ እናን እዚህ ደረጃ ላይ ደረሰ” ሲል ያስረዳል።
የብርሃነ ድርጅት ውስጥ በሙያቸው ተቀጥረው ከሚሰሩ ስደተኞች አንዱ አብዱ አህመድ መሀመድ ነው። እሱ በመካኒክነት የሚሰራ የመናዊ ስደተኛ ሲሆን ከብርሃነ ጋር ጂቡቲ በሚገኝ ኩባንያ ውስጥ አብረው ተቀጥረው ይሠሩ እንደነበር ያስታውሳል። በኋላ ግን ብርሃነ ስራውን ለቆ የራሱን ኩባንያ በመመሥረት ለሌሎች ስደተኞች የስራ ዕድልን እንደፈጠረ ይናገራል።
“ቅን ሰው ነው። ፈጣሪ ነው የሰጠው። ለማንም ሰው ሥራ የሚሰጥ ችግር የሌለበት ሰው ነው። የነበረው ድርጅት ሲቃጠል ቅያሪ ልብስ ሳይዝ ነበር የቀረው። ነገር ግን ተሯሩጦ ከሰዎች ጋርም ጥሩ ግንኙነት ስላለው የብዙዎች ድጋፍ ታክሎበት መልሶ ተክቶታል። ፈጣሪ ያለው ላይ ይጨምርለት።”
ብርሃነ በአሁኑ ወቅት ከቋሚ ሰራተኞቹ በተጨማሪ በኮንትራት መልክ የሚሰሩ በቀን ከ15 እስከ 20 የሚደርሱ ስደተኞች እንዳሉት ይናገራል። ድርጅቱን በማስፋፋት ለሌሎች በርካታ ስደተኞች የስራ እድል ለመፍጠር እቅድ እና ህልም አለው።
“አብዛኞቹ ሰራተኞች ከትግራይ የመጡ ናቸው። በተጨማሪም አረቦች (የመናውያን)፣ ሌሎች ኢትዮጵያውያን እና ኤርትራዊያንም ተቀጥረው እየሰሩ ይገኛሉ። ምንም ችሎታና ልምድ የሌላቸው ስደተኞች ሲመጡ እንኳን አሰልጥነን እንዲሰሩ እናደርጋለን” ይላል ብርሃነ።
ስደትን ለማንም ሰው እንደማይመኝ ከራሱ ተሞክሮ ተነስቶ የሚናገረው ብርሃነ “ተስፋን ሰንቀው ከሀገር የወጡ ብዙ ሰዎች ያልተፈለገ ቦታ ላይ ወድወቀው ቀርተዋል። ወደ ስደት ከወጡ በኋላ ጥለውት የመጡትን ህይወት መኖር የማይችሉም አሉ” ሲል ያስረዳል።
በሆነ አጋጣሚ አንዴ ወደ ስደት ከወጣህ የማይጨበጥ ተስፋን እየጠበቅክ ጊዜህን ከማጥፋት ያገኘኸውን ማንኛውም ስራ ዝቅ ብለህ መስራት እንዳለህ ይመክራል።
“ወደ ስደት ወጥተው ‘ይህንን ስራ አልሰራም’ ብለው የሚያማርጡ አሉ። እኔ መጀመሪያ ወደ ስደት ስመጣ መኪና አጥብ ነበር። ማረፍያም ስላልነበረኝ ውጭ ተኝቻለሁ። ያኔ ግን ያገኘሁትን ስራ እሰራ ነበር” በማለት የስደት ህይወቱን ጠቅሶ ይመክራል።













