ጂሃዲስቶች ከሚታሰሩበት የኒጀር ማረሚያ ቤት በርካታ እስረኞች አመለጡ

የፎቶው ባለመብት, AFP
የኒጀር ባለሥልጣናት ግጭት ከማያጣት ቲላቤሪ ግዛት በርካታ እስረኞች አምልጠው መውጣታቸውን ተከትሎ በአካባቢው ሰዓት እላፊ ጥለዋል።
ጠንካራ ጥበቃ እንዳለው የሚነገርለት እስር ቤት በቁጥጥር ሥር የዋሉ ጂሃዲስቶች የሚገኙበት ነው።
ከዋና ከተማዋ ኒያሚ 50 ኪሎ ሜትር ርቆ ከሚገኘው ኮቱካሌ እስር ቤት እስረኞች አምልጠው የወጡት ሐሙስ ማታ መሆኑን የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
ከዚህ ቀደም በአውሮፓውያኑ 2016 እና 2019 ሁለት ጊዜ እስረኞች አልምጠው ለመውጣት ያደረጉት ሙከራ አልተሳካም።
ባለፈው ዓመት በመፈንቅለ-መንግሥት ሥልጣን የያዘው የኒጀር ወታደራዊ ኃይል በተለይ በምዕራቡ የአገሪቱ ክፍል ከጂሃዲስቶች በርካታ ጥቃት እየደረሰበት ይገኛል።
የአገር ውስጥ ሚኒስቴሩ በመግለጫው ምን ያህል እስረኞች ከእስር ቤቱ አምልጠው እንደወጡ ይፋ ያደረገው ቁጥር የለም።
ቢሆንም አል-ቃኢዳ እና ኢስላሚክ ስቴት ከተባሉ ታጣቂ ቡድኖች ጋር ግንኙነት ያላቸው እስላማዊ ኃይሎች ከእስር ቤቱ ካመለጡት መካከል ሳይሆኑ አይቀርም እየተባለ ነው።
ባለሥልጣናት በቲላቤሪ ግዛት ፀሐይ ጠልቃ እስክትወጣ የሚቆይ የሰዓት እላፊ ሲያውጁ በሥፍራው ያለው የፀጥታ ኃይልም እንዲጠናከር ተደርጓል።
በሰዓት እላፊው መሠረት ማንኛውም መንገደኛ፣ ብስክሌተኛም ሆነ ተሽከርካሪ በምሽት መንቀሳቀስ አይችልም።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት መፈንቅለ መንግሥት ያስተናገዱት ኒጀር እንዲሁም ጎረቤቶቿ ማሊ እና ቡርኪና ፋሶ በወታደራዊ ሥርዓት የሚመሩ ሲሆን፣ አገራቱ ከጂሃዲስቶች በሚደርስባቸው ጥቃቶች እየታመሱ ይገኛሉ።
ባፈለው ሰኞ በቲላቤሪ ግዛት ከአል-ቃኢዳ ጋር ግንኙነት አለው የተባለ አንድ ጂሃዲስት ቡድን ባደረሰው ጥቃት 14 ወታደሮች ሲገደሉ 11 ወታደሮች ደግሞ ቆስለዋል።
ኢላ ፋሪ እና ጃንጎሬ በተሰኙት ሥፍራዎች መካከል ድንገተኛ ጥቃት ከደረሰባቸው ወታደሮች መካከል 24 ገደማዎቹ እስካሁን አድራሻቸው አይታወቅም።
ሦስቱም በወታደራዊ ኃይል የሚመሩ አገራት የፈረንሳይ ወታደሮችን ከአገሮቻቸው ያስወጡ ሲሆን የፈረንሳይ ጦር በእነዚህ ሀገራት ጂሃዲስት ኃይሎችን በመዋጋት ይታወቅ ነበር። ኒጀር፣ ማሊ እና ቡርኪና ፋሶ ወዳጅነታቸውን ከሩሲያ ጋር አድርገዋል።
በታጣቂዎች በሚደርሱ ጥቃቶች ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲገደሉ 3 ሚሊዮን ገደማ ሰዎች ደግሞ ቤት ንብረታቸውን ጥለው ተፈናቅለዋል። በዚህ ምክንያት በአካባቢው ሰብዓዊ ቀውስ እየተስፋፋ ነው።












