በሺዎች የሚቆጠሩ የሶማሊላንድ ወታደሮች ለሥልጠና ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው ተገለጸ

የሶማሊላንድ ወታደራዊ ባለሥልጣናት ሠልጣኞቹን በሸኙበት ወቅት

የፎቶው ባለመብት, Somaliland National TV

የምስሉ መግለጫ, የሶማሊላንድ ወታደራዊ ባለሥልጣናት ሠልጣኞቹን በሸኙበት ወቅት

በሺዎች የሚቆጠሩ የሶማሊላንድ ወታደሮች ወታደራዊ ሥልጠና ለመውሰድ ትናንት ሐሙስ ሐምሌ 4/2016 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸው ተገለጸ።

በመንግሥት የሚተዳደረው የሶማሊላንድ ቴሌቪዥን ጣቢያ ለወታደራዊ ሥልጠና ወደ ኢትዮጵያ የሚጓዙ ናቸው ያላቸውን በሺዎች የሚቆጠሩ የሠራዊት አባላት በተሽከርካሪዎች ጉዞ ሲጀምሩ አሳይቷል።

“የሶማሊላንድ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሜጀር ጄኔራል ኑህ እስማኢል ለሥልጠና የሚጓዙትን ሠልጣኞች ሸኝተዋል” ብሏል መንግሥታዊው የሶማሊላንድ ቴሌቪዥን ጣቢያ በዘገባው።

ወታደራዊ ሥልጠናውን በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የተባለ ነገር የለም። ከሶማሊላንድ በኩልም እንዲሁም የሠራዊት አባላቱ ቁጥር “በሺዎች የሚቆጠሩ” ከማለት ውጪ ምን ዓይነት ሥልጠና እንደሚወሰዱ የተገለጸ ነገር የለም።

ቴሌቪዥን ጣቢያው በበርካታ አውቶብሶች እና የደረቅ ጭነት ተሸከርካሪዎች ከሶማሊላንድ ተነስተው ዋጃሌ የተባለች የድንበር ከተማን አቋርጠው ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ አሳይቷል።

ይህንን ጉዳይ በተመለከተ ከኢትዮጵያ እና ከሶማሊያ መንግሥታት በኩል አስካሁን የተባለ ነገር የለም።

ከስድስት ወራት በፊት የሶማሊላንድ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች አዲስ አበባ ተገኝተው በወታደራዊ ትብብር ዙሪያ ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው ጋር ውይይት አድርገው እንደነበረ ይታወሳል።

ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘዋል የተባሉት የሶማሊላንድ ሠራዊት አባለት

የፎቶው ባለመብት, Somaliland National TV

የምስሉ መግለጫ, ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘዋል የተባሉት የሶማሊላንድ ሠራዊት አባለት

በወቅቱ የኢፌድሪ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከሶማሊላንድ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሜጄር ጄኔራል ኑህ ኢስማኢል ታኒ ጋር ዝርዝሩ ይፋ ባልተደረገ ወታደራዊ ትብብር ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸው ተገልጾ ነበር።

ባለፈው ታኅሣሥ 22/2016 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ተነጥላ ነጻ አገር መሆኗን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር የመግባቢያ ሠነድ መፈራረሟን ተከትሏ የሉዓላዊ ግዛቷ አካል እንደሆነች በምትቆጥረው ሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል ከፍተኛ ውጥረት ፈጥሯል።

ይህ ስምምነት ለተገንጣይዋ ሶማሊላንድ ዕውቅናን የሚሰጥ፤ ሶማሊላንድ ደግሞ በምላሹ ለኢትዮጵያ የባሕር በር እና ለባሕር ኃይል ሰፈር የሚውል የባሕር ጠረፍ እንድታገኝ የሚፈቅድ ስለመሆኑ መዘገቡ ይታወሳል።

ከዚህ ስምምነት በኋላ ሶማሊያ በሞቃዲሾ የሚገኘቱን የኢትዮጵያን አምባሳደር ከአገር አስወጥታ በአዲስ አበባ የሚገኙትን አምባሳደሯን መጥራቷ አይዘነጋም።

ኢትዮጵያ ከሶማሊያ ተገንጥላ ነጻ አገርነቷን ያወጀችውን ሶማሊላንድ ሠራዊትን ለማሠልጠን ወታደሮችን የመቀበሏ ሪፖርት በአዲስ አበባ እና በሞቃዲሾ መካከል ያለውን ውጥረት የበለጠ ሊያባብሰው ይችላል።

ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከስድስት ወራት ገደማ በፊት ከሶማሊላንድ ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሜጄር ጄኔራል ኑህ ኢስማኤል ታኒ

የፎቶው ባለመብት, FDRE DEFENCE FORCE

የምስሉ መግለጫ, ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ከስድስት ወራት በፊት ከሶማሊላንድ አቻቸው ሜጄር ጄኔራል ኑህ ኢስማኤል ታኒ ጋር በአዲስ አበባ በወታደራዊ ትብብር ዙሪያ ውይይት አድርገው ነበር

ይህ የሶማሊላንድ ወታደሮች ለሥልጠና ወደ ኢትዮጵያ የመግባት ዜና የተሰማው የሶማሊያው ፕሬዝዳንት በኤርትራ ወታደራዊ ሥልጠና ላይ ያሉ የሶማሊያ ወታደሮችን ከጎበኙ ከቀናት በኋላ ነው።

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ባለፉት 7 ወራት ከኢትዮጵያ ጋር ወዳጅነቷ ወደተቀዛቀዘው ኤርትራ ሲጓዙ ይህን ለሦስተኛ ጊዜ ነው።

ፕሬዝዳንቱ አሥመራ ሲገቡ በአቻቸው ኢሳያስ አፈወርቂ ደማቅ አቀባበል የተደረገላቸው ሲሆን በቆይታቸውም በኤርትራ ሥልጠና እየወሰዱ ያሉ ዕጩ የሠራዊት አባላትን ጎብኝተዋል።

ሶማሊያ፤ ኤርትራ ውስጥ ለረጅም ጊዜ ወታደራዊ ሥልጠና እየወሰዱ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮች ያሏት ሲሆን፣ ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ እነዚህን ሠልጣኞች ወደ አገራቸው ለመመለስ ሲጥሩ እንደነበር ይታወቃል።