አሜሪካ ከኢራን ጋር በቀጥታ የኒውክሌር ድርድር እያደረገች መሆኑን ትራምፕ ተናገሩ

የፎቶው ባለመብት, AFP
አሜሪካ እና ኢራን በኒውክሌር ስምምነት ላይ "ቀጥታ ውይይት" ቅዳሜ ዕለት እንደሚጀምሩ ዶናልድ ትራምፕ ተናገሩ።
የኢራን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ውይይቱ እንደሚካሄድ አረጋግጠው፣ ውይይቱ የሚካሄደው "በተዘዋዋሪ ሊሆን ይችላል" ካሉ በኋላ "እድል የመሆኑን ያህል፣ ምን እንዳለ ለመቃኘት ይረዳል" ብለዋል።
የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ሰኞ ዕለት በዋሽንግተን እና ቴህራን መካከል የሚደረገው ውይይት "በከፍተኛ ባለስልጣናት ደረጃ ነው" በማለት ተናግረው፣ ስምምነት ላይ ካልተደረሰ "ለኢራን በጣም መጥፎ ቀን ይሆናል" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
ባለፈው ወር የኢራን ከፍተኛ ሃይማኖታዊ መሪ አያቶላ አሊ ካሜኔይ አሜሪካ ያቀረበችውን የቀጥተኛ ንግግር ጥያቄ በይፋ ውድቅ ካደረጉ በኋላ ዶናልድ ትራምፕ በኢራን ላይ ወታደራዊ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚችል ተናግረው ነበር።
ትራምፕ ውይይት ለማድረግ ቀጠሮ መያዙን የተናገሩት ከእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ጋር በኋይት ሀውስ ከተገናኙ በኋላ ነው።
ትራምፕ "ቅዳሜ [ከኢራን] ጋር በጣም ትልቅ ስብሰባ አለን፣ ከእነሱ ጋር በቀጥታ እንነጋገራለን… እና ምናልባት ስምምነት ሊደረስ ይችላል፣ ያ የሚሆን ከሆነ ጥሩ ነው" ብለዋል ።
ትራምፕ አክለውም ድርድሩ ካልተሳካ ኢራን "ትልቅ አደጋ" ውስጥ ትገባለች ሲሉ የተናገሩ ሲሆን፣ "ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ሊኖራት አይችልም፤ እና ውይይቱ ካልተሳካ በእውነቱ ለኢራን በጣም መጥፎ ቀን ይሆናል ብዬ አስባለሁ" ብለዋል ።
ፕሬዚዳንቱ የሚደረገው ንግግር በምን ደረጃ ላይ እንዳለ እንዲሁም የትኞቹ ባለስልጣናት እየተሳተፉ እንደሆነ ከመናገር ተቆጥበዋል።
የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋሽንግተን እና ቴህራን ሚያዝያ 4/ 2017 ዓ.ም. በኦማን እንደሚገናኙ አረጋግጠዋል።
አባስ አራክቺ በኤክስ ገጻቸው ላይ "ያለውን የምንፈትሽበት የመሆኑን ያህል እድልም ነው፤ ኳሱ በአሜሪካ ሜዳ ውስጥ ነው" ብለዋል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ዶናልድ ትራምፕ በመጋቢት ወር በተባበሩት አረብ ኢምሬትስ በኩል ለኢራን መሪ ለድርድር ያላቸውን ፍላጎት የሚገልጽ ደብዳቤ ልከው ነበር።
ምንም እንኳን የዶናልድ ትራምፕ የእንደራደር ጥያቄ ውድቅ ቢደረግም የኢራን ባለስልጣናት በሶስተኛ ወገን ከአሜሪካ ጋር ሊኖር ስለሚችል ውይይት ያላቸውን ፈቃደኝነት አሳይተው ነበር።
የኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ የመገንባት አቅምን መግታት ለአሜሪካ እና አጋሮቿ ለአስርት ዓመታት የዘለቀ ቁልፍ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ግብ ሆኖ ቆይቷል።
እአአ በ 2015 የወቅቱ ፕሬዝዳንት ባራክ ኦባማ ከኢራን ጋር የኒውክሌር እንቅስቃሴዋን እንድትገድብ የሚያደርግ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ተቆጣጣሪዎች ወደ አገሪቱ ገብተው የኒውክሌር ማብላያዎቹ ከሲቪል ዓላማ ውጪ ለጦር መሳሪያ ማምረቻ አለመዋላቸውን አንዲከታተሉ ስምምነት ተፈራርመው ነበር።
በምላሹም ኢራን ኢኮኖሚዋን ካሽመደመደው ማዕቀብ እፎይታ ለመስጠት ተስማምተው ነበር።
በዛ ስምምነት ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ሩሲያ እና እንግሊዝ ፊርማቸውን አኑረውበታል።
ሆኖም እአአ በ2016 ትራምፕ አገራቸው ከስምምነቱ መውጣቷን አሳውቀዋል።
ዶናልድ ትራምፕ በመጀመሪያው የፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ዘመቻቸው ወቅት ስምምነቱን በከፍተኛ ሁኔታ ሲተቹት ነበር።
በቀጣዮቹ ዓመታት ኢራን የገባችውን ስምምነት መጣሷ ተገልጿል።
ዓለም አቀፉ የአቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ቴህራን የኒውክሌር ቦምቦችን ለመስራት የሚያገለግል የበለፀገ የዩራኒየም ክምችት መገንባቷን ጠቅሶ አስጠንቅቋል።
ከቅርብ ወራት ወዲህ ትራምፕ ከኢራን ጋር አዲስ ስምምነት የማድረግ ተስፋን ያነሱ ሲሆን፣ ያ የማይሆን ከሆነ ግን ወታደራዊ እርምጃ እንደሚወስድ እየዛቱ ነበር።
እስራኤል ተቀናቃኟ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንዳታገኝ ማድረግ የረዥም ጊዜ ደህንነቷ ዋና ማዕከል አድርጋ ትመለከተዋለች።
ባለፈው ዓመት ኢራን ቀደም ሲል በእስራኤል ላይ ለፈጸመችው የሚሳኤል ጥቃት አፀፋ የኢራንን ኒውክሌር ጣቢያ መምታቷ ይታወቃል።
ኔታንያሁ በኋይት ሀውስ ንግግር ሲያደጉ "ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንዳታገኝ ለማድረግ እኛ እና አሜሪካ ሁለታችንም አንድ ነን። በሊቢያ እንደተደረገው ሙሉ በሙሉ በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ሊደረግ ይችላል፤ ያ መንገድም ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ" ብለዋል።












