ቤቶቻቸውን ሲያጸዱ በማህበራዊ ሚዲያዎች በማሳየት ገንዘብ ማፍራት የቻሉት ግለሰቦች

ካሪስ ሃርዲንግ

የፎቶው ባለመብት, Carys Harding

የምስሉ መግለጫ, ካሪስ ሃርዲንግ

እንደ በርካታ ወላጆች የዩናይትድ ኪንግደም ነዋሪዋ ካሪስ ሃርዲንግ ረጅም ጊዜዋን የምታሳልፈው ልጆቿን በመንከባከብ ነው።

ነገር ግን የ27 ዓመቷ የሶስት ልጆች እናት ከሌሎች ለየት የሚያደርጋት ቤቷን ስታጸዳ፣ ስትወለውል፣ ስትጠርግ፣ አንዱን ስታነሳ ስትጥል፣ ስታዘጋጅ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በማህበራዊ ሚዲያ ይመለከቷታል።

እነዚህ የቤት ውስጥ ጽዳቶች 'ሪሴት' (እንደገና መጀመር) በሚል ሃሽ ታግ ታዋቂ ሆኗል።

ካሪስ በቲክቶክ እና ኢንስታግራም በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ተከታዮች አሏት።

የዕለት ተዕለት ህይወታቸውን በማህበራዊ ሚዲያዎች በማሳየት ገቢ ከሚያገኙበት ተጽእኖ ፈጣሪዎች አንዷ ሆናለች።

"በህይወቴ በየዕለቱ የማደርጋቸው እና የማከናውናቸው ጉዳዮች ሰዎችን የሚስብ ነገር ይሆናል ብዬ ለአንድ ደቂቃም አስቤ አላውቅም ነበር" ትላለች የስዋንሲያ ከተማ ነዋሪ የሆነችው ካሪስ።

ከሶስት ዓመት በፊት ሁለተኛ ልጇን ከወለደች በኋላ ነበር ቤቷን በደንብ ማደራጀት እንዳለባት የተገነዘበችው።

ማታ ማታም ይህንኑ ቤቷን የማዘጋጀት ስራም ታከናውን ነበር።

"ምሽት ላይ እንደገና መጀመር" በሚለውም ፕሮግራሟም 20 ደቂቃ ያህል ትወስዳለች።

ትጠርጋለች፣ ወለሉን ትወለውላለለች ልጆቿ ከተኙ በኋላም ለሚቀጥለው ቀን የሚያስፈልጋትን ታዘጋጃለች።

እነዚህንም የቤት ስራ ተግባሯቿን ስታከናውን ትቀርጽና በአጭር ቪዲዮዎች ለማህበራዊ ሚዲያ ተከታዮቿ ታጋራለች።

"የሚያግዙኝን ሁኔታዎች ለሰዎች ማካፈል እወዳለሁ፤ ምክንያቱም እናት መሆን ከባድ ነው" ትላለች።

"ለቁጥር የሚታክቱ መስራት ያለባችሁ ነገር ስላለ ማሰብ ያስፈልገዋል" ስትል ታስረዳለች።

ካሪስ የምትቀርጻቸው ሆነ የምታጋራቸው ቪዲዮዎች በርካቶች በቀላሉ የሚረዷቸው፤ ራሳቸውን የሚያዩባቸው እንደሆኑ ታስረዳለች።

ቪዲዮዎቿ እናቶች በበቂ እየሰራን አይደለም የሚል ስሜት እንዲሰማቸው ማድረግ በጭራሽ ሃሳቧ እንዳልሆነ ትናገራለች።

"የቤቴን ንጽህና መጠበቅ ህይወቴን ቀለል ማድረግ በዘለለ ምንም ዓላማ የለውም" ትላለች።

"የኔን ቪዲዮ ለመነሳሳት ተጠቀሙበት። ነገር ግን የኔን ቪዲዮ ስትመለከቱ ስለራስዎት ያለዎት እሳቤ የሚቀንስ ከሆነ በጭራሽ አትመልከቱት" ትላለ።

ካሪስ ከሶስት ልጆቿ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Carys Harding

ሌላኛዋ የማህበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ፈጣሪ ኤሚሊ ጆንስ ጊዜ ቆጣቢ የጽዳት ምክሮቿን ከ13 ሺህ በላይ ለሆኑ የኢንስታግራም ተከታዮቿ ስታካፍል 100 በመቶ ግልጽ ለመሆን እንደምትሞክር ትናገራለች።

"ልጄ ሲያንቀላፋ ግማሽ ሰዓት ካለኝ በዚያች ጊዜ ለማጽዳት እና ቤቴን ለማዘጋጀት እሞክራለሁ። የምችለውን በዚያች ባለችኝ ሰዓት እሰራለሁ" ስትል የሁለት ልጆች እና የሆነችው የ32 ዓመቷ እናት ታስረዳለች።

"ቀኑን ሙሉ ማጽዳት አትችሉም። ፍጹም የማይቻል ነው" ትላለች።

"እናት ነኝ። ስራ አለኝ። ሁለት ትናንሽ ልጆች አሉኝ። እንደ ሌሎች ሰዎች በርካታ ማከናወን ያሉብኝ ተግባራት አሉ" ስትል ታስረዳለች።

ኢንስታግራም ላይ ክሊኒንግ (ጽዳት) በሚል ሃሽታግ ከ11 ሚሊዮን በላይ ልጥፎች አሉ።

እንዲሁም ሪሴት (እንደገና መጀመር) በሚል ደግሞ 2.6 ሚሊዮን ልጥፎች ይገኛሉ።

ኤሚሊ ጆንስ

የፎቶው ባለመብት, Emily Jones

የምስሉ መግለጫ, ኤሚሊ ጆንስ

በኢንስታግራም፣ ቲክቶክ፣ ፌስቡክ እና ዩቲዮብ ወደ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ ተከታዮች ያሏት የ30 ዓመቷ ሩ ደይ በዩኬ ካሉ የቤት ጽዳት ይዘቶችን ከሚለጥፉ ተጽእኖ ፈጣሪዎች ታዋቂዋ ናት።

ሩ በማህበራዊ ሚዲያዎቿ ላይ "የአንድ ሰዓት የፍጥነት ጽዳት" የሚል ቪዲዮዎች አሏት።

በዚህም ቆጣሪ አዘጋጅታ በ60 ደቂቃ ምን ያህል ጽዳቶችን እንደምታከናውን ታሳያለች።

"በታቻለ መጠን ለጽዳት አነስተኛ ጊዜ ባጠፋ እመርጣለሁ። ሌሎችም እንዲሁ በተመሳሳይ መልኩ ይሄው እንደሚሰማቸው ይነግሩኛል" ትላለች ሩ።

ሩ እንደምትለው የቤት ውስጥ ጽዳቶች የማህበራዊ ሚዲያ ይዘቶች በሴቶች የተፈጠሩ ቢሆንም ወንዶችም እየገቡበት ነው ትላለች።

"ስለ ሥርዓተ ጾታ እንነጋገር ከተባለ ጽዳትን ሴቶች ብቻ ማከናወን ያለባቸው ተግባር አይደለም" ትላለች።

"በአሁኑ ወቅት በርካታ ወንዶች አሉ ስለ ቤት ጽዳት በማህበራዊ ሚዲያ ይዘቶችን የሚያጋሩ"

"ምንም እንኳን አሁንም በሴቶች የበላይነት መያዙ ቢያስደስተኝም፤ ወንዶችም እየገቡበት ነው" ስትል ታስረዳለች።

በኢንስታግራም፣ ቲክቶክ፣ ፌስቡክ እና ዩቲዮብ ወደ 2 ሚሊዮን የሚጠጉ ተከታዮች ያሏት የ30 ዓመቷ ሩ ደይ

የፎቶው ባለመብት, Roo Day

አዕምሮ የማረጋጋት ችሎታ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

"ጽዳት በተለምዶ በሴቶች የተያዘ ሚና " እንደሆነ የሚናገሩት በለንደን የሴንት ጆርጅ ዩኒቨርስቲ ተባባሪ ፕሮፌሰር ዶክተር ስቴፋኒ አሊስ ቤከር ናቸው።

ለዚያም ነው የሚያውቁትን ጽዳት በማህበራዊ ሚዲያዎች ይዘቶች ለመፍጠር የተሻለ ቦታ የሚያስቀምጣቸው ይላሉ።

"ለዘመናት ሴቶች በተለምዶ የሚሰሩት እና የማይከፈላቸውን የቤት ስራዎች ወደ ማህበራዊ ሚዲያ በማምጣት ገቢ እየፈጠሩባቸው፤ ገንዘብ እያገኙባቸው ነው" ይላሉ።

ዶክተር ቤከር እንደሚሉት የአኗኗር ዘዬን የሚያሳዩ ይዘቶች በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ታዋቂ ቢሆኑም ፍላጎቱ አዲስ አይደለም ይላሉ።

"እንዲህ አይነት ይዘቶች ከማህበራዊ ሚዲያ በፊት ነበሩ። በአሁኑ ወቅት ማህበራዊ ሚዲያው የበለጠ ተደራሽ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል" በማለት ይገልጻሉ።

"መድረኮቹ እና ታዳሚዎች ተለውጠው ሊሆን ይችላል ነገር ግራ ራስን ማሻሻል ጋር የተያያዙ ጉዳዮች በየትኛውም ትውልድ ውስጥ ነበሩ" ሲሉ ያስረዳሉ።

በስዋንሲያ ዩኒቨርስቲ የስነ ልቦና ባለሙያ የሆኑት ዶ/ር ሴሪ ብራድሾው በበኩላቸው የ60 ሰኮንድ ቪዲዮዎች ለሰዎች ሃሰተኛ ምስል እንደሚሰጡ እና እንደሚያታልሉ ያስረዳሉ።

እሳቸው እንደሚሉት የቤት ውስጥ ጽዳቶች እንደሚታየው ቀላል የሰኮንዶች ስራ ሳይሆን ረጅም ሰዓት የሚወስድ አድካሚ ስራ ነው።

"አብዛኛውን ጊዜ በተለያዩ መድረኮች የምንመለከታቸው ሰዎች መሆን እንዳለብን እያሰብን በቀላሉ የምንታለል ይመስለኛል" ሲሉም አክለዋል።

ሆኖም እሳቸው እንደሚሉት የቤት ጽዳቶች ይዘቶችን መመልከት ምን ያህል ሊስብ እንደሚችል ይረዳሉ።

"የጽዳት ይዘቶች ላይ ስንመጣ፤ ማስተካከል የሚያስፈልገው ነገር በፍጥነት በተሳካ ሁኔታ ወዲያውኑ እየተተስካከለ ነው።

"አዕምሮን በጣም የሚያረጋጋ ነው" ይላሉ።