ሮናልዶ ሁለት ጎሎች ባስቆጠረበት ጨዋታ ከአል-ናስር ጋር የመጀመሪያ ዋንጫውን አነሳ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በአረብ ክለብ ቻምፒዮንሺፕ ዋንጫ ፍፃሜ ሁለት ጎሎች በማስቆጠር ከአል-ናስር ጋር የመጀመሪያ ዋንጫውን አንስቷል።
ምንም እንኳ አል-ናስር ሁለት ተጫዋቾችን በቀይ ካርድ ቢያጣም በጭማሪ ደቂቃ የማሸነፊያዋን ጎል በማስቆጠር ክለቡ ድል እንዲያደርግ ረድቷል።
የ38 ዓመቱ ፖርቹጋላዊ አጥቂ አል-ናስር ተቀናቃኙ አል-ሂላልን በመርታት ዋንጫ እንዲያጣጥም ትልቅ ሚና ተጫውቷል።
አል-ሂላል ጨዋታውን 1-0 ለባዶ እየመራ እስከ 74ኛ ደቂቃ ቢቆይም ሮናልዶ ጎል አስቆጥሮ አቻ ማድረግ ችሏል።
ጨዋታው 1 አቻ ከተጠናቀቀ በኋላ 30 ደቂቃ ተጨምሮ በመጀመሪያው አጋማሽ ሮናልዶ ሁለተኛዋን ጎል አስቆጥሮ ታሪክ ፅፏል።
የአል-ናስሮቹ አል- አምሪ እና ናዋፋ ቡሻል በ71ኛው እና በ78ኛው ደቂቃ በቀይ ካርድ ተሰናብተዋል።
አምስት ጊዜ የዓለም ምርጡ ተብሎ የተሸለመው ሮናልዶ ጨዋታው ሊጠናቀቅ አምስት ደቂቃዎች ሲቀሩት ባጋጠመው ጉዳት በቃሬዛ ከሜዳ ወጥቷል።
በሳዑዲ ፕሮ ሊግ የሮናልዶ አል-ናስር ስቲቨን ጄራርድ ከሚያሰልጥነው አል-ኢቲፋቅ ጋር የውድድር ዓመቱ የመጀመሪያ ጨዋታውን ከሶስት ቀናት በኋላ ያደርጋል።
የቀድሞው የሪያል ማድሪድ፣ ማንቸስተር ዩናይትድ እና ጁቬንቱስ አጥቂ ባለፈው ታኅሣሥ ነው ወደ ሳዑዲ ያቀናው።
አል-ናስር ባለፈው የውድድር ዘመን በሳዑዲ ፕሮ ሊግ ሁለተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።
ሮናልዶ ወደ ሳዑዲ ካቀና በኋላ በርካታ የአውሮፓ ድንቅ ተጫዋቾች እሱን ተከትለው ለሳዑዲ አረቢያ ክለቦች ፈርመዋል።
በክረምቱ የዝውውር መስኮት ሳዲዮ ማኔ፣ ሴኮ ፎፋና እና ማርሴሎ ብሮዞቪች ለአል-ናስር ፈርመዋል።
ሪያድ በሚገኘው የንጉሥ ፋህድ ስታድየም በተካሄደው የዋንጫ ጨዋታ በመጀመሪያው አጋማሽ ሮናልዶ፣ ማኔ እና ብሮዞቪች የአል-ሂላሉን በረኛ ቢፈትኑም ስኬታማ አልሆኑም።
አል-ሂላል በቀድሞው የባርሴሎና የክንፍ መስመር ተጫዋች አማካይነት የመጀመሪያውን ጎል ቢያስቆጥርም ዋንጫው አምልጦታል።
ሮናልዶ የመጀመሪያውን ጎል አስቆጥሮ ቡድኑ አቻ ከሆነ ከአራት ደቂቃ በኋላ ነው ሁለት ተጫዋቾች በቀይ ከሜዳ የወጡበት።
ክሪስቲያኖ ሮናልዶ በውድድሩ ባለፉት ስድስት ጨዋታዎች ስድስት ጎሎችን አስቆጥሯል።
የሳዑዲ፣ ካታር፣ ዩኤኢ፣ ኢራቅ፣ ሞሮኮ፣ ቱኒዚያ እና አልጄሪያ ክለቦች በሚሳተፉበት አረብ ክለብ ቻምፒዮንሺፕ ውድድር ሮናልዶ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ሆኖ አጠናቋል።












