የሳዑዲ አረቢያ ክለቦች ሚሊዮኖች እያወጡ “ገና ብዙ ተጫዋቾችን ያስፈርማሉ”

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሳዑዲ ፕሮ ሊግ ከአውሮፓ ተጫዋቾችን ለማምጣት ብዙ ረብጣ ሚሊዮኖችን መክፈሉን ተያይዞታል፤ ወደፊትም ይቀጥላል ይላሉ ከሊጉ አመራሮች አንዱ።
“ለሚቀጥሉት ዓመታት የሚሆን በጀት አለ። ይቀዘቅዛል የሚል እምነት የለኝም” ይላሉ ከሊጉ ቦርድ አባላት አንዱ ብሪታኒያዊው ፒተር ሁቶን።
ባለፈው ጥር የአምስት ጊዜ ባለን ደ ኦር አሸናፊው ክሪስቲያኖ ሮናልዶ ከማንቸስተር ዩናይትድ ወደ ሳዑዲ አረቢያ ካቀና በኋላ በርካታ ስም ያላቸው ተጫዋቾች ተከትለውታል።
የቀድሞው የሪያል ማድሪድ አጥቂ ካሪም ቤንዜማ፣ የሊቨርፑል አምበል ጆርዳን ሄንደርሰን አልፎም የቼልሲ፣ ማንቸስተር ሲቲ እና የባየርን ሙኒክ ተጫዋቾች ወደ ሳዑዲ ሄደዋል።
ባለፈው ወር አል-ሂላል የፓሪ ሳን ዠርማውን ኪሊያን ምባፔ ለመግዛት 259 ሚሊዮን ፓውንድ ማቅረቡ አስደንጋጭ ነበር።
የፌስቡክ፣ ዩሮስፖርት፣ ኢኤስፒኤን እና አይኤምጂ የተሰኙት ድርጅቶች ከፍተኛ አመራር ሆነው ያገለገሉት ሁቶን “ለ40 ዓመታት በስፖርቱ ዓለም ሠርቻለሁ፤ እንዲህ ያለ ትልቅ ፕሮጀክት ግን አላየሁም” ይላሉ።
እሳቸው እንደሚሉት ፕሮጀክቱ “ትልቅ ዕቅድ ያለው፤ ለስኬታማነት ጠንክሮ የሚሠራ ነው።”
የአውሮፓ እግር ኳስ ልክ እንደ ቀድሞው ጠንካራ ሆኖ መቀጠል የማይችል ከሆነ የሳዑዲ ዕቅድ “ክፉ ነው ብዬ አላስብም” ሲሉ ለቢቢሲ ይናገራሉ።
ምንም እንኳ ሳዑዲ አረቢያ ለእግር ኳስ እያወጣች ያለችው ገንዘብ ትልቅ መነጋገሪያ ቢሆንም “የፕሪሚዬር ሊግ ክለቦች በያዝነው የዝውውር መስኮት ካወጡት ጋር ሲነፃፀር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም” ሲሉ ይከራከራሉ።
የማንቸስተር ሲቲው አሠልጣኝ ፔፕ ጉዋርዲዮላ የሳዑዲ ፕሮ ሊግ የገንዘብ አቅም “የዝውውር ገበያን ይለውጣል” የሚል እምነት አላቸው።
የሊቨርፑሉ አቻቸው ዩርገን ክሎፕ ደግሞ የሳዑዲ ፕሮ ሊግ የዝውውር መስኮት ዘግይቶ መዘጋቱ “አሳሳቢ” ነው።
ነገር ግን ሁቶን እንደሚሉት የሳዑዲ ሊግ ብዙ ገንዘብ አውጥቶ ተጫዋቾች መግዛቱ “ወደፊት የአውሮፓ እግር ኳስ ጥንካሬ ይዳከማል ማለት አይደለም። እግር ኳስ በዓለም ዙሪያ እየጠነከረ መሄዱ መልካም ነው።”
‘በስፖርት ስም’
ሳዑዲ አረቢያ በተለይ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ለስፖርት ከፍተኛ ወጪ ማድረግ ጀምራለች። በስፖርት ስም ገጽታዋን ለመገንባት ሞክራለች የሚል ወቀሳም ደርሶባታል።
ሳዑዲ የሰብዓዊ መብት እና የሴቶችን መብት በመጣስ ስሟ በተደጋጋሚ ይነሳ። ይህም ብቻ ሳይሆን የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን እስከ ሞት ቅጣት ሊበይንባቸው ይችላል።
የሊቨርፑሉ አምበል ወደ ሳዑዲው አል-ኢቲፋቅ ሲያቀና ለተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪያን ይሰጥ ከነበረው ድጋፍ አንፃር ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሞት ነበር።
ሁቶን “መሬት ላይ እየሆነ ያለውን ስላየሁ ነው ወደ ሳዑዲ አረቢያ እግር ኳስ የመጣሁት” ይላሉ።
“ሚስቴ በፊፋ (በዓለም አቀፉ የእግር ኳስ አስተዳዳሪ) የሴቶች እግር ኳስ ክፍል ነው የምትሠራው። ሳዑዲ ውስጥ እየሆነ ስላለው ነገር ታውቃለች። ለውጥ እያየን ነው። ስፖርቱ ለሳዑዲ ዜጎች ምን ያህል ደስታ እያመጣ እንዳለ እያየን ነው።”
ከምዕራቡ ዓለም ጋር ሲነፃፀር ቀርፋፋ ቢመስልም፤ ሴቶች በሳዑዲ ማኅበረሰብ ውስጥ ያላቸው ሚና በፍጥነት እየተቀየረ ነው ባይ ናቸው።
“አሁን 50 ሺህ ትምህርት ቤት ውስጥ ያሉ ታዳጊ ሴቶች እግር ኳስ ይጫወታሉ። 1000 ያህል ሴት አሠልጣኞች አሉ። በ2018 የተመዘገቡ አሠልጣኞች 750 ነበሩ። አሁን ይህ ቁጥር ወደ 5500 አድጓል።”
ሳዑዲ ለእግር ኳስ እያወጣች ያለችው ወጪ ቻይና አንድ ሰሞን በወፍራም ደመወዝ የአውሮፓ ተጫዋቾችን ታግዝ ከነበረው ክስተት ጋር ተነፃፅሯል።
የሳዑዲ አረቢያ ሕዝብ ኢንቨስትመንት ፈንድ አራት የሊጉን ክለቦች የግል ንብረቱ አድርጓል።
የቦርድ አባሉ እንደሚሉት ልክ እንደ ሳዑዲ ሁሉ ሌሎችም አገራት በመንግሥት በኩል ስፖርቱን ማስኬድ ቢችሉ አካዳሚዎችን፣ የሴቶች እና የወንዶች እግር ኳስን፣ እንዲሁም ፌዴሬሽኖችን ማስተዳደር ይቀላቸዋል።
ሁቶን እንደሚያምኑት በሚቀጥሉት ዘጠኝ እና አሥር ዓመታት የሳዑዲ ሊግ ገቢ ማምጣት ይጀምራል።












