የዝውውር ወሬ፡ “ምባፔ በውሰት ወደ ለንደን መምጣት እንደሚፈልግ ለቼልሲ ተናግሯል”

ኪሊያን ምባፔ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የፈረንሳዩ ፓሪ ሳን ዠርማው አጥቂ ኪሊያን ምባፔ በውሰት ወደ ለንደን መምጣት እንደሚፈልግ ለቼልሲ ተናግሯል ሲል የስፔኑ ስፖርት ጋዜጣ ፅፏል።

የ24 ዓመቱ የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን አምበል በሚቀጥለው ዓመት በነፃ ወደ ሪያል ማድሪድ የሚሄድ ከሆነ ለአንድ ዓመት የውሰት ውል ለቼልሲ ሊያኖር ይችላል።

ማንቸስተር ዩናይትድ የሳውዝሀምፕተኑን የ19 ዓመት ቤልጂየማዊ አማካይ ሮሜዮ ላቪያ ለማስፈረም ያስገባው ጨረታ ውድቅ እንደሆነበት ኢንዲፔንደንት ዘግቧል።

ዴንማርካዊውን የ20 ዓመት አጥቂ ለማስፈረም ከጫፍ የደረሰው ዩናይትድ ፊርማው እስከሚቀጥለው ቅዳሜና እሑድ ሊራዘምበት እንደሚችል የዘገበው ደግሞ ማንቸስተር ኢቭኒንግ ኒውስ ነው።

ዩናይትድ ኔዘርላንዳዊውን አማካይ ዶኒ ቫን ደ ቢክ ለሪያል ሶሲየዳድ ለመሸጥ ከስፔኑ ክለብ ጋር ውይይት መጀመራቸውን የሜል ዘገባ ይጠቁማል።

ማንቸስተር ዩናይትድ፤ ቫን ደ ቢክን ከሸጡ የፊዮረንቲናው ሞሮኳዊ አማካይ ሶፍያን አምራባትን እንዲያስፈርሙ ያግዛቸዋል።

የአታላንታው አጥቂ ራስመስ ሆይለንድ በጠቅላላው 77 ሚሊዮን ፖውንድ በሆነ ዋጋ ወደ እንግሊዙ ክለብ እንደሚመጣ ተነግሯል።

የጀርመኑ ቢልድ እንደሚለው እንግሊዛዊው የ30 ዓመት አጥቂ ሃሪ ኬን ከደመወዙ ብዙውን ቀንሶ ወደ ባየር ሙኒክ ለመሄድ ወስኗል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሃሪ ኬንን ሸጠው በሚያገኙት ገንዘብ በርካታ ተጫዋቾችን ለማስፈረም ያቀዱት ቶተንሃሞች የ22 ዓመቱ ተከላካይ ሚኪ ቫን ደ ቬን ከዎልፍስበርግ ለመግዛት መስማማታቸውን ቶክስፖርት አስነብቧል።

ቶተንሃም ከሃሪ ኬን በተጨማሪ የ27 ዓመቱን ዴንማርካዊ አማካይ ፒዬር-ኤሚል ሆይበርግን ለአትሌቲኮ ማድሪድ በ30 ሚሊዮን ፓውንድ ለመሸጥ አቅደዋል።

የጣሊያኑ ኢንተር ሚላን የ24 ዓመቱን ጃፓናዊ የአርሰናል ተከላካይ ታኪሄሮ ቶሚያሱን ለማስፈረም ይሻሉ ሲል የፃፈው ጋዜቴ ዴሎ ስፖርት ነው።

ባርሴሎና ደግሞ የማንቸስተር ሲቲውን የ29 ዓመት ፖርቹጋላዊ ተከላካይ ጃዎ ካንሴሎን ለማስፈረም ንግግር እንደጀመሩ የቶክስፖርት ዘገባ ያስረዳል።

ቼልሲ የብራይተኑን አማካይ ሞይሰስ ካይሴዶ ለማስፈረም ከሌሎች ክለቦች ፉክክር ገጥሞታል። እንደ አትሌቲክ ዘገባ አንድ ስሙ ክለብ ያልተጠቀሰ ኤኳዶራዊውን ተጫዋች ለመግዛት ከቼልሲ በላይ ገንዘብ አቅርቧል።

ወደ 100 ሚሊዮን ገደማ የተገመተው ካይሴዶን ለመግዛት ቼልሲ ተጨማሪ መጠን ያለው ገንዘብ እንደሚያቀርብ ስካይ ስፖርት ዘግቧል።

አስተን ቪላ የሊድስ ዩናይትዱን አሜሪካዊ አማካይ ታይለር አዳምስ ለመግዛት 25 ሚሊዮን ፓውንድ እንዳዘጋጀ ሜል በዘገባው ጠቁሟል።

የሳዑዲ አረቢያው አል-ናስር 13 ሚሊዮን ፓውንድ ከፍሎ የ28 ዓመቱን ፈረንሳዊ ተከላካይ ክሌሜንት ሌንግሌ ከባርሴሎና ለማምጣት ይፈልጋል። ሌንግሌ በቶተንሃምም ይፈለጋል።

ከፉልሃም ጋር አዲስ ፊርማ ካኖረ ሁለት ሳምንት የሆነው ብራዚላዊው ዊሊያን ከሳዑዲው ክለብ አል-ሻባብ እናስፈርምህ ጥያቄ ቀርቦለታል።

ፉትቦል ኢንሳይደር እንደሚለው ቤሺክታሽ የ28 ዓመቱን አይቮሪ ኮስታዊ የመስመር ተጫዋች ኒኮላስ ፔፔ ከአርሰናል ለመውሰድ ሲል ትራንስፈርማርኬት በቱርክ ቋንቋ ፅፏል።

ጋላታሳራይ ደግሞ የማንቸስተር ዩናይትዱን ብራዚላዊ አማካይ ፍሬድ በያዝነው የክረምት ዝውውር መስኮት ሊያስፈርም እንደሚሻ ተሰምቷል።