ለመጀመሪያ ጊዜ በቆረጠችው ሎተሪ ከፍተኛውን ዕጣ ያሸነፈችው ካናዳዊት በዕድሜ ትንሿ ሆነች

የፎቶው ባለመብት, ONTARIO LOTTERY
ለመጀመሪያ ጊዜ በቆረጠችው የሎተሪ ትኬት ከፍተኛውን የገንዘብ ሽልማት በ18 ዓመቷ በማሸነፍ በካናዳ የሎተሪ አሸናፊ ታሪክ የመጀመሪያዋ ሆነች።
ካናዳዊት ጁሊየት ላመር 48 ሚሊዮን የካናዳ ዶላር ወይም ከ35 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር በላይ የሆነ የሎተሪ ዕጣን በማሸነፍ በካናዳ ታሪክ ከፍተኛውን የሎተሪ ገንዘብ በማሸነፍ በዕድሜ ትንሿ ሆናለች።
ይህንን ከፍተኛ መጠን ያለውን ዕጣ ያሸነፈችው ወጣት ባገኘችው ገንዘብ ምክንያት ቀደም ሲል የጀመረችውን ዕቅዷን እንደማትቀይር ገልጻለች።
በዚህም የዩኒቨርስቲ ተማሪ የሆነችው ጁሊየት የጀመረችውን ትምህርቷን በመጨረስ ዶክተር የመሆን ዕቅዷን ለማሳካት አጠናለሁ ብላለች።
የካናዳ ኦንታሪዮ ሎተሪ እና ጨዋታ የጥር ወር ዕጣን ያሸነፈችው ጁሊየት፣ ሎተሪው እንደደረሳት ስትሰማ “የደስታ እንባ አንብቻለሁ” ብላለች።
“አሁን ድረስ ለመጀመሪያ ጊዜ በቆረጥኩት የሎተሪ ትኬት ከፍተኛውን የገንዘብ ሽልማት ማግኘቴን ማመን አልቻልኩም።”
ጁሊየት ሎተሪውን ከቆረጠች በኋላ እረስታው እንደነበር የተናገረች ሲሆን፣ የገዛችውን የሎተሪ ቁጥር መፈለግ የጀመረችው የአሸናፊው ዕጣ ቁጥር እሷ ከምትኖርበት ከተማ መሸጡን የሚያመለክት ዜና ከሰማች በኋላ ነበር።
በሞባይሏ ላይ ባለ የሎተሪው መተግበሪያ ላይ ቁጥሯን በማስገባት ስታጣራ የከፍተኛ የገንዘብ ሽልማት አሸናፊ መሆኗን ለመረዳት እንደቻለች ገልጻለች።
ጎደኞቿ እና ሁሉም በዙሪያዋ የነበሩ ሰዎች ለማመን መቸገራቸውን እንዲሁም በምትሰራበት ቦታ አለቃዋ ቶሎ ከሥራ እንድትወጣ ቢፈቅድላትም እናቷ ግን ፈረቃዋን ጨርሳ እንድትወጣ እንደመከሯት ተናግራለች።
ለወደፊት በአባቷ ድጋፍ ያገኘችውን የሎተሪ ሽልማት አብዛኛውን “በጥንቃቄ” በታሰበበት ሥራ ላይ ለማዋል አቅዳለች።
በተጨማሪም ከመንግሥት ድጋፍና ብድር ሳትጠይቅ በተወሰነው ገንዘብ ወጪዋን በመሸፈን ዶክተር የመሆን ህልሟን ዕውን ለማድረግ አልማለች።
በዚህም የህክምና ዶክተር በመሆን ወደ ትውልድ ቦታዋ ሰሜን ኦንታሪዮ በመመለስ ማኅበረሰቡን ለማገልገል ትፈልጋለች።
ነገር ግን በሎተሪ ዕጣ ካገኘችው ገንዘብ ላይ ለአልባሌ ነገር የምታጠፋው ገንዘብ እንደማይኖር የተናገረችው ጁሊየት፣ ትምህርቷን ካጠናቀቀች በኋላ ግን ወደ አንድ አህጉር በመሄድ በምታደርገው ጉብኝት አዲስ ባሕል፣ ቋንቋ፣ ምግብ እና ሌሎችም ነገሮችን ለማወቅ አቅዳለች።
ቤተሰቦቿ ሲያሳድጉ የነገሯትን ወሳኝ ምክርንም ባገኘችው ገንዘብ ምክንያት እንደማትዘነጋው ትናገራለች፤ “ገንዘብ ሳይሆን ሥራው ነው የአንድ ሰው መገለጫው።” የሚለውን።












