በዘረፋ እና በወንጀል እየተናጠች ያለችው ትግራይ

መቀለ

የፎቶው ባለመብት, atakhelti dejene

የምስሉ መግለጫ, መቀለ በምሽት

መሠረት ሓድሽ ከቀናት በፊት ሞባይሏ መልዕክት እንደደረሳት የሚጠቁም ድምጽ አሰማት - አንድ አርቲስት ባልደረባዋ ነበር።

“ትናንት እኔም እንደአንቺ ተመሳሳይ ነገር ደረሰብኝ፤ ልዩ ኃይል ነን ያሉ ታጣቂዎች ጨለም ወዳለ ቦታ ወስደው ያለኝን ነገር በመዝረፍ ቀጥቅጠው አሰናበቱን” የሚል መልዕክት እንደላከላት ታስታውሳለች።

ይህም የራሷን አጋጣሚ አስታወሳት።

ሰኞ ጥር 22/2015 ዓ.ም. ከሥራ ወጥታ ወደ ቤቷ እየተመለሰች ሳለ መቀለ ሐውዜን አደባባይ አካባቢ ጎረምሶች በጠራራ ፀሐይ ዘረፋ ፈጽመውባታል።

ሐውዜን አደባባይ ከከተማዋ መሃል የሚገኝ ስፍራ ነው፤ ይህ በመደበኛ ዕለት ብዙ መኪኖች የሚተላለፉበት፣ የሰዎች እንቅስቃሴ የማይለየው ነው።

አራት ወጣቶች ከበው አንዱ እጇን ይዞ፣ ሌላው ኪሷን፣ ሌላኛው ደግሞ ቦርሳዋን ሲናጠቁ በአካባቢው ጥጉን ይዞ የሚታዘብ በርካታ ሰው እንደ ነበር ታስታውሳለች።

“እርዱኝ. . . እየተመታሁ ዝም ብላችሁ ታያላችሁ እንዴ?. . . እያልኩ ስጮህ ነበር። ነገር ግን የፊልም ቀረጻ እስኪመስል ድረስ ሰዉ ቆሞ ይመለከት ነበር።”

ሰዉም ቢሆን ለራሱ ስለሚሰጋ እንደ በፊቱ ለማስጣል ወይ ለመርዳት አይደፍርም ትላለች።

“ቀደም ሲል ሕዝቡ እንደዚህ አልነበረም፤ አሁን ግን ሁሉም በሩቅ ሲመለከት በጣም አዘንኩኝ። ሁኔታው በአጭር ጊዜ የተፈጸመ ቢሆንም ለእኔ ከባድ ነበር” ትላለች።

መሠረት በቅርቡ በትግራይ ጦርነት ምክንያት በፆታዊ ጥቃት ሰለባ የሆኑ ሴቶችን ሁኔታ እና ሌሎች ማኅበራዊ ጉዳዮችን የሚዳስስ የቴሌቭዥን ፕሮግራም ማዘጋጀት የጀመረች የሙዚቃ መምህርት ነች።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በትግራይ ካለው የማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ባሻገር ሰዎች በተለምዶ “ሃንግ” እያሉ የሚጠሩት ዘረፋ በነዋሪው ፀጥታ እና ደኅንነት ላይ ከፍተኛ ስጋት እንደጋረጠ በስፋት እየተነገረ ነው።

ይህ የወንጀል ድርጊት ደግሞ በተደራጁ እና በታጠቁ ግለሰቦች የሚፈጸም መሆኑ ደግሞ በተለይ በክልሉ ዋና ከተማ ያለውን ነዋሪ የዕለተ ዕለት ደኅንነት አደጋ እያንዣበበት እንደሆነ እንዲሰማው እንዳደረገ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ሰዎች ገልጸዋል።

መሠረትም በከተማዋ እያጋጠመ ባለው የዝርፊያ ጥቃት የተነሳ “እናቶችን፣ ወጣቶችን፣ ከትግል የተመለሱትን ሳይቀር እያጣን ነው። ብዙ ሰው እየሞተ ነው። ምንም ነገር ላያገኙ ነው ሰዉን በቢላ እየወጉ ያሉት። በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሰናል” በማለት የሁኔታውን ክብደት ታስረዳለች።

‘ከመይ ኢልና ንደቅስ?’ (እንዴት ብለን እንተኛ?) የተባለ የትግርኛ መጽሐፍ ደራሲ የሆነው ፀጋይ ገብረመድኅንም ከምሽት አራት ሰዓት ላይ ወደ ቤቱ ሲገባ በሦስት ሰዎች ጥቃት ደርሶበታል።

“ከኋላ መጥተው አንገቴን አነቁኝ፤ መንገድ መሃል ጥለው ኪሴ ውስጥ የነበረ የተወሰነ ገንዘብ እና ሞባይሌን ወሰዱ። ከአንድ ሰዓት በኋላ ይሆናል ወደ ቀልቤ የመለስኩት” ሲል የደረሰበትን ለቢቢሲ ተናገሯል።

በዚህ ሳምንትም በቅርበት የሚያውቃቸው ሁለት ሰዎች የተመሳሳይ ጥቃት ሰለባ መሆናቸውን ይገልጻል።

“ሁለቱም መንገድ ላይ ታንቀው የነበራቸው ጥቂት ገንዘብ እና ሞባይላቸውን ተዘርፈዋል። ጠዋት 12፡30 መሃል መንገድ ላይ በቢላ አስፈራርተው ስልኮቻቸውን የወሰዱባቸው ሁለት ሴቶችንም አውቃለሁ።”

ይህ አሳሳቢ የወንጀል ድርጊት ለተወሰነ ጊዜ ጋብ ብሎ የነበረ ቢሆንም፣ ባለፉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ግን መልሶ በማገርሸት እንደተባባሰ ፀጋይ ይገልጻል።

የፀጥታ መዋቅሩ የነዋሪዎችን ደኅንነት የማይጠብቅበት፣ ሰዉ በስጋት እና በሰቀቀን የሚንቀሳቀስበት ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ በማውሳት ሕዝቡ ያለበትን ሁኔታ አመልክቷል።

“ሰዎች ከቤት ወጥተው መሄድ ይፈራሉ። የባጃጅ ሹፌርን አምኖ ለብቻ መንቀሳቀስ አይቻልም፤ ምክንያቱም እዚያ አስገብተው ወይም መንገድ ላይ ተጨማሪ ሰው አሳፍረው እየዘረፉ እና ንብረት እየቀሙ በመሆናቸው ነው” ሲልም ያክላል ፀጋይ።

የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ በመቀለ ነዋሪዎች ወደ መደበኛ ሕይወት መመለስ ጀምረዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ በመቀለ ነዋሪዎች ወደ መደበኛ ሕይወት መመለስ ጀምረዋል

‘የራሳቸውን ኬላ ያቋቋሙ ዘራፊዎች’

ለሁለት ዓመታት የዘለቀውን የእርስ በእርስ ጦርነት ለማስቆም የፌዴራል መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች ቋሚ የተኩስ አቁም ስምምነት ከተፈራረሙ ሦስት ወራት የተቆጠሩ ቢሆንም፣ በወንጀል ድርጊቶች የተነሳ የነዋሪው ስጋት እንዳለ ነው።

በየትኛውም ወቅት ዝርፊያ አዲስ ክስተት ባይሆንም አሁን ትግራይ ውስጥ ለየት ያሉ ክስተቶች እያጋጠሙ ነው።

ቢቢሲ ስለዚህ ጉዳይ የጠየቃቸው የመቀለ ነዋሪዎች እንደሚናገሩት፣ በተደራጀ ሁኔታ የሰውን አንገት በማነቅ፣ በጩቤ አስፈራርቶ ወይም ወግቶ ንብረትን መቀማት፣ ከዚያም አለፍ ሲል በመሳሪያ እና በመኪና በመታገዝ የሚፈጸም ዝርፊያ በየዕለቱ የሚሰማ ክስተት ነው።

በተጨማሪም እነዚህ በሕዝቡ ደኅንነት ላይ ስጋትን የደቀኑት አደገኛ የወንጀል ድርጊቶች በተለይ በቀበሌ 14፣ 15 እና 16 እንዲሁም አብርሃ ካስል እዲሁም በአዲ ሃቂ ዩኒቨርሲቲ ግቢ አቅራቢያ ማርታ አደባባይ አካባቢ እንደሚፈጸሙ ይጠቁማሉ።

ከሁሉ አሳሳቢው ደግሞ በጦር መሳሪያ ታግዞ የሚፈጸሙ የዝርፊያ ድርጊት ነው። አንድ ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ የትግራይ ኃይል አባል፣ “የመገናኛ ራዲዮ እና መኪና ያላቸው ናቸው እዚህ ተግባር ውስጥ እየተሳተፉ ያሉት” ይላል።

ከዚህ በፊት የመኪና መስታወት በመስበር ከውስጥ ያለ ንብረት ይዘረፍ እንደነበር የሚገልጸው ይህ ግለሰብ፣ “አሁን ግን መኪናው እራሱ እንዳለ ነው የሚወሰደው። መኖሪያ ቤት ገብተው ባለቤቶች ባሉበት ዝርፊያ ይፈጸማል።

“ቤቱን ልንፈትሽ ነው፣ የፍርድ ቤት ወረቀት አለን ብለው ሁሉ በመግባት ወንጀል ይፈጸማል። የመሪዎች ቤት ሳይቀር እየተዘረፈ ነው። ይህ ሁሉ ሁኔታ ዘረፋው የተደራጀ መሆኑን ያመለክታል” በማለት ገልጿል።

ይህ የወንጀል ድርጊት የሰዎችን ሃብት እና ንብረት ብቻ ሳይሆን እያሳጣ ያለው፣ በየዕለቱ የሰዎች ሕይወትም እየጠፋ ነው። በዚህም ስጋት ሳቢያ እሱም ከምሽቱ ሁለት ሰዓት በኋላ በከተማው ውስጥ ለመንቀሳቀስ አይደፍርም።

በዋና ከተማዋ ካለው ሁኔታ በተጨማሪ አዲግራት እና ዓቢ ዓዲን በመሳሰሉ ከመቀለ ውጪ ባሉ ሌሎች ከተሞች እና ገጠራማ አካባቢዎችም ተመሳሳይ ከፍተኛ የወንጀል ድርጊት ስጋት እንዳለም ጨምሮ ይጠቅሳል።

“በከተማው ውስጥ ድሃ ከሀብታም ሳይለይ ጥቃት እየደረሰባቸው ነው። በገጠር አካባቢዎች ደግሞ የአርሶ አደሩን ከብቶች እና እህሉ የሚቀማ አለ። ከዚህ ባለፈ ግን ታጣቂዎች የራሳቸውን አርቲፊሻል ኬላ ያቋቋሙ እና የታጠቁ ናቸው” ይላል።

የሞባይል ንጥቂያ በርካታ ሰዎችን ገጥሟቸዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, የሞባይል ንጥቂያ በርካታ ሰዎችን ገጥሟቸዋል

‘ሱማሌ ተራ’ በመቀለ

ከተስፋፋው ዝርፊያ እና ንጥቂያ ጋር በተያያዘ በአሁኑ ጊዜ በመቀለ ውስጥ ባሉ በሁሉም አካባቢዎች ለማለት በሚያስደፍር ሁኔታ፣ ሞባይልም ሆነ ሌላ ጠቃሚ ነገር ተቀማን፣ ተደበደብን የሚሉ ሰዎችን ማግኘት ቀላል ነው።

በጦርነቱ ምክንያት ከ18 ወራት በላይ ትግራይ ውስጥ ተቋርጦ የቆየው የቴሌኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ወደ ነበረበት ከተመለሰ በኋላ በርካታ ሞባይል ስልኮች መሰረቃቸውን፤ በዚህም ምክንያት ብዙ ሰዎች ላይ አደጋ እየደረሰ እንደሆነ ቢቢሲ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ይገልጻሉ።

ከሁሉ የሚገርመው ደግሞ ከነዋሪዎች የሚሰረቁት ሞባይሎች ዋጋ እና ደረጃ ወጥቶላቸው በከተማዋ ውስጥ ካለው ትልቁ ሆቴል፣ ፕላኔት ጀርባ ባለው ‘ዕዳጋ 11’ መግቢያ ላይ ይሸጣሉ።

አሁን ይህ አካባቢም ልክ አዲስ አበባ የተሰረቁ እቃዎች ይሸጡበታል ሲባል እንደነበረው ‘ሶማሌ ተራ’ የሚል አዲስ መጠሪያ ተሰጥቶታል።

“ገዢ የፈለገውን የሞባይል ዓይነት (ብራንድ) ሲጠይቅ ይቀርብለታል፤ ከሌላቸው ደግሞ ሰርቀው እስኪያመጡ ድረስ የአንድ ወይ የሁለት ቀን ቀጠሮ በመስጠት ያመጣሉ” የሚለው የመቀለ ነዋሪ፣ ይህ ሁኔታም በይፋ የሚታወቅ ነገር መሆኑን ይናገራል።

ያለው የወንጀል ድርጊት በሥራቸው ባህሪይ ምክንያት ስልክ፣ ላፕቶፕ፣ ሃርድ ዲስክ እና መሰል ነገሮችን ይዘው መንቀሳቀስ ያላባቸው ነዋሪዎች ወጥተው በሰላም አስኪመለሱ ድረስ ከባድ ጭንቅ ውስጥ እንደሚቆዩ መሠረት ትጠቅሳለች።

“በዚህም ምክንያት ከቤት ምንም ነገር ይዞ መውጣት ስጋት እና አደጋ ስላለው፣ አንድ ሰው ከቤቱ ወጥቶ እስኪመለስ ድረስ በጣም ያስጨንቃል።”

ጦርነቱ የፈጠረው ቀውስ

የተስፋፋው የወንጀል ድርጊት በክልሉ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር የተያያዘ መሆኑን ነዋሪዎች ይናገራሉ። ከሁለት ዓመት በላይ ሁሉም የሥራ እንቅስቃሴዎች ተስተጓጉለዋል። በርካታ የመንግሥት ሠራተኞች ሥራ አጥ ሆነው ካለደሞዝ ሕይወትን እየገፉ በመሆናቸው ድህነት ስር ሰዷል።

ሁሉም ወጣቶች ከሥራም ሆነ ከትምህርት ውጪ ሆነው ባሉበት እና በበቂ የዲሲፕሊን ሥልጠና ያልታነጹ የትግራይ ኃይሎችን የተቀላቅለው የቆዩ ተዋጊዎች ድንገት ጦርነቱ ሲቆም እጃቸው የገባውን መሳሪያ ለወንጀል ድርጊት እያዋሉት እንደሆነ አንዳንዶች ግምታቸውን ይገልጻሉ።

“ለጦርነት የታነጹት ወጣቶች ለሰላምም ሊታነጹ ይገባል። ቢያንስ ለሠራዊቱ ተሃድሶ መስጠት ያስፈልጋል። ወጣቱ ተሃድሶ ሳይሰጠው፣ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎቹ ሳይመለሱ መፍትሄ አይገኝም። ይህ ከተረሳ ወይም ችላ ከተባለ መዘዙ ቀላል አይሆንም” ሲል የትግራይ ኃይል አባል የሆነው ግለሰብ ለቢቢሲ ተናገሯል።

በመንግሥት እና በህወሓት መሪዎች መካከል ደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ ላይ የተፈረመው ስምምነት ትጥቅ ለሚፈቱ የትግራይ ኃይል አባላት የመልሶ ማቋቋም ሥራ እንደሚኖር የተገለጸ ቢሆንም በስፋት እየተከናወነ ስለመሆኑ የተባለ ነገር የለም።

ከጦርነቱ መጀመር በፊት ክልሉ ከፍተኛ መጠን ያለው ልዩ ኃይል አሠልጥኖ ነበር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከጦርነቱ መጀመር በፊት ክልሉ ከፍተኛ መጠን ያለው ልዩ ኃይል አሠልጥኖ ነበር

የወንጀል ጫና በጤና ተቋማት ላይ

በከተማዋ ውስጥ በሚያጋጥሙ ድንገተኛ አደጋዎች ምክንያት ነዋሪዎች ለህክምና የሚሄዱበት የመቀለ ሆስፒታል ባለፉት ሦስት ወራት ከወንጀል እና ከዝርፊያ ጋር በተያያዘ ጉዳት የደረሰባቸው በርካታ ታካሚዎችን ተቀብሏል።

ከእነዚህም መካከል በአሰቃቂ ሁኔታ ጉዳት ደርሶባቸው ወደ ሆስፒታሉ የሚገቡ ሰዎች ቁጥር ከሌላው ጊዜ መጨመሩን የመቀለ ሆስፒታል ምንጮች ለቢቢሲ ጠቁመዋል።

ቢቢሲ ዝርዝር መረጃውን ከሆስፒታሉ አስተዳደር ለማግኘት ቢሞክርም ከፀጥታ አካላት ውጪ ዝርዝር መረጃ እንደማይሰጡ የሆስፒታሉ ሥራ አስኪያጅ ዶ/ር ፊልሞን ምላሽ ሰጥተዋል።

በተመሳሳይ በተለያዩ ምክንያት በሚፈጸምባቸው ጥቃት ምክንያት ወደ ሆስፒታሉ የገቡት ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን የአይደር ሆስፒታል ሪፈራል ለቢቢሲ ገልጿል።

ከመካከላቸውም በአልኮል መጠጥ ምክንያት የሚደርሱ የቡድን አደጋዎች በቁጥር እንደሚበልጡም ተናግረዋል።

የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር አብርሃ ገብረእግዚአብሔር እንዳሉት፣ በድንጋይ የተመቱ፣ በስለት የተወጉ እና በጥይት የተመቱትን ጨምሮ በየቀኑ ከ10 እስከ 13 ሰዎች ያስተናግዳሉ።

ጨምረውም በጥይት ተመትተው የሚመጡ ሰዎች ቁጥር ከፍ እንደሚል የሚናገሩት ዶ/ር አብረሃም “በጥይት ተመትተው ሕይወታቸው ካለፈ በኋላ ወደ ለአስከሬን ምርመራ የሚመጡም አሉ።”

“በተለይም ከዓርብ እስከ ሰኞ ባሉት ቀናት ድንገተኛ ህክምና ፈልገው የሚመጡ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች እስከ 50 የሚደርሱ ሲሆን፣ ይህም በጦርነቱ ወቅት ከነበረው ይበልጣል” ይላሉ ዳይሬክተሩ።

“እንደ ሕዝብ ከባድ አደጋ ውስጥ ወድቀን እያለ፣ የመድኃኒት እጥረቱ ሳይሟላ፣ ሠራተኞቻችን በድካምና በረሃብ እያገለግሉ ባለበት ሁኔታ ይህ መቆም አለበት”ሲሉ ሕዝቡ መፍትሄ እንዲፈልግ ዶ/ሩ ይማጸናሉ።

“በአቅርቦት ችግር ምክንያት ህሙማን መድኃኒት እየተጠባበቁ ባሉበት ሁኔታ፣ እየቆጠብን እና እየሰሰትን መድኃኒት ለማድረስ በምንሞክርበት ወቅት መከላከል በሚቻል አደጋ ምክንያት የታካሚዎች መጨመር ያሳስበናል” ሲሉ ዶ/ር አብረሃም ጭንቀታቸውን ይገልጻል።

ባለሥልጣናት ምን ይላል?

የትግራይ ፖሊስ ኮሚሽንን የሚመሩት ኮሚሽነር ጄኔራል ይህደጎ ሥዩም በክልሉ ያለውን የፀጥታ ሁኔታ ከጦርነቱ ጋር የሚያገናኙት ብዙ ነገሮች እንዳሉ በመጥቀስ፣ ስርቆት፣ የሞባይል ዝርፊያ እና ከዚህ ሲብስ ደግሞ በመሳርያ የታገዘ ዝርፍያ እንዳለ ያምናሉ።

“በጥቅምት ወይም በኅዳር አካባቢ የታጠቁ ሰዎች ነበሩ። አብዛኞቹን በቁጥጥር ስር ስላዋልን አሁን እንዲህ ዓይነት እንቅስቃሴ የለም። በመሳሪያ እና በተደራጀ መልክ የሚፈጸም ዝርፍያ በእጅጉ ቀንሷል። ነገር ግን እንደ አንድ ክስተት ሊታይ ይችላል” በማለት በዚህ ድርጊት ከሚሳተፉት አንዳንዶቹ የሠራዊት ወይም የፖሊስ አባላት የነበሩ ሊሆኑ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

ካለፈው ዓመት (2014) ጀምሮ በአዲስ መልክ ተቋቁሞ አባላቱን በመመልመል እና በማሠልጠን ወደ ሥራ እንዳሰማሩ ኮሚሽነሩ ገልጸው፣ “ነገር ግን በክረምቱ በሁሉም አቅጣጫዎች የተካሄደው ከባድ ውጊያ ተጽዕኖ ነበረው” ይላሉ።

በትግራይ አስተዳደር ስር ባሉ ከተሞች እና ገጠሮች የተባሉት አይነት ችግሮች ይታዩ እንደነበር የሚገልጹት ኮሚሽነር ጄኔራል ይህደጐ፣ በኅዳር ወርም ሁኔታው የከፋ እንደነበር አረጋግጠዋል።

አክለውም በፌዴራል መንግሥት እና በህወሓት አመራሮች መካከል የተደረገው የተኩስ አቁም ስምምነትን ተከትሎ የፀጥታ ኃይሎች እንደተሰማሩ እና ከታኅሣሥ ወር ጀምሮ በመቀለ አንጻራዊ መረጋጋት እንደተስተዋለ ገልጸዋል።

“መቀለ ውስጥ መንቀሳቀስ አትችልም፣ ሰዎች በየቀኑ ይሞታሉ ብለው ሰዎች ሲናገሩ እንሰማለን። ሁኔታ ግን እንደዚያ አይደለም። አልፎ አልፎ ወንጀል ይፈፀማል” በማለት ሕብረተሰቡ በፀጥታ ሥራው ውስጥ ትልቅ ሚና ስለሚጫወት ወንጀሉን ለመቀነስ እየጣሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ነገር ግን “በተናጠል የሚያጋጥሙ ክስተቶችን ይዞ፣ በሰላም መውጣት እና መግባት አስቸጋሪ ነው፤ በየቀኑ ሰዎች ይገደላሉ ማለት አይቻልም። የባሰበት ጊዜ ነበር። አሁን ግን ተሻሽሏል። ግን ከዚህ በላይ እንዲሆን ስለምንፈልግ ግን ማቃለል አንፈልግም፤ እንስራበት” ለዚህም ይረዳ ዘንድ አዲስ የፖሊስ መዋቅር ተቋቁሞ የ24 ሰዓት አገልግሎት እየሰጠ መሆኑንም ተናግረዋል።

እንደ ፀጋይ ገብረመድኅን ያሉ ነዋሪዎች ከተማዋ የሚሰተዋለው የሥርዓት አልበኝነት እና የመንግሥት አልባነት ስሜት እንደሆነ በመግለጽ ፖለቲካዊ ማስተካከያ እንደደረግ ይጠይቃሉ።

መሠረትም በበኩሏ የምትናፍቀው የመቀለ መረጋጋት በቅርቡ ወደ ነበረበት እንደሚመለስ ተስፋ ታደርጋለች።