ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከህወሓት መሪዎች ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ ተገናኙ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሁለት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከከፍተኛ የህወሓት ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝተው ተወያዩ።

የፎቶው ባለመብት, @RedwanHussien

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከሁለት ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከከፍተኛ የህወሓት ባለሥልጣናት ጋር ተገናኝተው ተወያዩ።

ይህ የሆነው ደም አፋሳሹ ጦርነትን ያስቆመው የሰላም ስምምነት በፌደራል መንግሥቱ እና በትግራይ ኃይሎች መካከል ከተፈረመ ከሦስት ወራት በኋላ ነው።

በመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን በኩል ይፋ ከተደረገው ከዚህ ዜና ጋር የቀረበው ምስል እና ቪዲዮ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከከፍተኛ የፖለቲካ እና የወታደራዊ ባለሥልጣናቶቻቸው ጋር ሆነው ከህወሓት ልዑካን ጋር ሲወያዩ አሳይቷል።

በዚህም ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አደም ፋራህ፣ ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪያቸው አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ አብረሃም በላይ (ዶ/ር) እና ሌሎችም በውይይቱ ላይ ተሳትፈዋል።

በትግራይ በኩል ደግሞ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ጄኔራል ጻድቃን ገብረ ተንሳይ፣ ሌ/ጄኔራል ታደሰ ወረደ፣ አምባሳደር ወንደሙ አሳምነው እና ሌሎችም ተገኝተዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ የሆኑት አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በትዊተር ገጻቸው ላይ ከህወሓት ተወካዮች ጋር የሰላም ስምምነቱ እየተተገበረ ስላለበት ሂደት ውይይት መደረጉን አስፍረዋል።

ጨምረውም በሁለቱ ወገኖች መካከል ያለውን መተማመን ለማጠናከር እና ሕዝቡ ችግር ለማቅለል ወደ ትግራይ የሚደረጉ በረራዎች እንዲጨመሩ እንዲሁም የባንክ እና ሌሎች ጉዳዮችን በተመለከተ ውሳኔ ማሳለፋቸውን ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከፍተኛ የፌደራል መንግሥቱ እንዲሁም የህወሓት ባለሥልጣናት ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኙት ከአዲስ አበባ ውጪ በደቡብ ክልል ውስጥ እየተገነባ በሚገኘው ሃላላ ኬላ በተባለው ስፍራ ነው።

ጦርነቱን ለማስቆም የፌደራል መንግሥቱ እና ህወሓት በቀዳሚነት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ፣ ከዚያም በኋላ ሁለት ጊዜ ኬንያ ናይሮቢ ላይ በአፍሪካ ኅብረት ሸምጋይነት መደራደራቸው ይታወሳል።

የሁለቱም ወገን ባለሥልጣናት ለመንግሥት መገናኛ ብዙኃን በሰጡት አስተያየት ውይይታቸው በስምምነቱ ላይ የተቀመጡ ጉዳዮች አተገባበር እና በቀጣይ በሚከናወኑ ተግባራት ላይ ግምገማ ማድረጋቸውን ነው።

ባለፉት ሦስት ወራት ሰብአዊ እርዳታ ያለገደብ እየቀረበ፣ መሠረታዊ አገልግሎቶች፣ የህወሓት ተዋጊዎች ትጥቅ መፍታት እና ከመከላከያ ሠራዊት ውጪ የሆኑ ኃይሎች ከትግራይ መውጣት መጀመራቸው ይታወቃል።