የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ የተጠረጠሩባቸው ወንጀሎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ረቡዕ ሐምሌ 06/2014 ዓ.ም. ከሙስና ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ስር የዋሉት የብሔራዊ አደጋ ስጋትና ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ የተጠረጠሩባቸውን ወንጀሎች ዝርዝር ፖሊስ ይፋ አድርጓል።
ለበርካታ ዓመታት የብሔራዊ አደጋ ስጋትና ሥራ አመራርን በበላይነት የመሩት ኮሚሽነሩ ከኤልሻዳይ ሪሊፍ ኤንድ ዴቨሎፕመንት ከተባለው የበጎ አድራጎት ማኅበር ዳይሬክተር ጋር በመመሳጠር ፈጽመዋቸዋል የተባሉ ወንጀሎች ተጠቅሰውባቸዋል።
በዚህም የእርዳታ ቁሶችን ለግል ጥቅማቸው በማዋል እንዲሁም ሕገወጥ ገንዘብን ሕጋዊ አስመስለው በማቅረብ ወንጀል መጠርጠራቸውን ፖሊስን ዋቢ አድርገው የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የፍትህ ሚኒስቴር የሙስና ወንጀል ዐቃቤ ሕግ ዳይሬክቶሬት ጄኔራል እና የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ወንጀል ምርመራ ቢሮ በጥምረት ሲያደርጉት የቆየ ነው በተባለ ምርመራም የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎች ተዘርዝረዋል።
በተጨማሪም የፌደራል ዋና ኦዲተር የብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን እንዲሁም በአማራ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያና በደቡብ ክልሎች በሚገኙት የኤልሻዳይ ማዕከላት ላይ ያከናወነው የምርመራ ኦዲት ተጠናቆ በምርመራው እንደተካተተም ተገልጿል።
ኮሚሽነሩ የተጠረጠሩባቸው ወንጀሎች
ኮሚሽነሩ በቁጥጥር ስር ከዋሉ በኋላ በቤታቸው በተደረገው ብርበራ ከ605 ሺህ በላይ የውጭ አገር ገንዘብ መገኘቱን የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዘግቧል።
በዚህም ዘገባ ላይ ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ላለፉት 2 ዓመታት ሥልጣን ባለው ተቋም ከአገር እንዳይወጡ እግድ ተጥሎባቸው እንደነበርም ሰፍሯል።
ኮሚሽነሩ አቶ ምትኩ ከኤልሻዳይ የበጎ አድራጎት ማኅበር ዳይሬክተር የማነ ወልደማርያም እና ከሌሎችም የተቋሙ ሠራተኞች ጋር ተገቢ ያልሆነ የጥቅም ግንኙነት በመፍጠር ለእርዳታ የመጡ ቁሳቁሶችን ለግል ጥቅማቸው አውለዋል ብሏል ፖሊስ።
ፖሊስ እንደሚለው አቶ ምትኩ በሺዎች የሚቆጠሩ የሌሉ ተረጂዎችን ስም በመጠቀም እና የእርዳታ ፈላጊዎችን ቁጥር በመጨመር እህልና የምግብ ቁሳቁሶች ከኮሚሽኑ መጋዘን አውጥተው በሚሊዮኖች ብር በመሸጥ ጥቅም አግኝተዋል።
ለእርዳታ ፈላጊዎች የመጣው እህል ለተረጂዎቹም ሳይደርስ ለዱቄት ፋብሪካዎችና ለሌሎች ግለሰቦች ሸጠውታል፤ በዚህም ከአቶ ምትኩ በተጨማሪ በቤተሰቦቻቸውም ስም ከኤልሻዳይ በተለያዩ ጊዜያት በሚሊዮን ብር የሚገመት ጥቅም ማግኘታቸውን ማስረጃ እንዳለው ፖሊስ ገልጿል።
በዚህም ፖሊስ ኮሚሽነሩን በሚመለከት ተገቢ ባልሆነ መንገድ ጥቅም ያገኙበትን እና ለተረጂዎች የሚሰጥ እርዳታን ለራሳቸው ጥቅም አግኝተውበታል ያላቸውን ሁኔታዎች ፖሊስ ዘርዝሯል።
- ከብሔራዊ አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ወጪ ተደርጎ ለኤልሻዳይ የተሰጠና ለግል ጥቅም ውሏል የተባለውም 472 ሚሊዮን ብር፣ 512 ሺህ ኩንታል ስንዴ በግማሽ ቢሊዮን ብር የሚገመት፣ 34 ሺህ ኩንታል በቆሎ፣ 77 ሺህ ሊትር ዘይት፣ 4 ሺህ ኩንታል ሩዝ መሆኑም ተገልጿል።
- በተጨማሪም ኤልሻዳይ በእርዳታ ፈላጊዎች ስም ከኮሚሽኑ የወሰደውን እህል በአዳማ ከተማ ለሚገኘው ኪያ ዱቄት ፋብሪካ 66,483 ኩንታል ስንዴ 66 ሚሊዮን 483,880 ብር በመሸጥ ገንዘቡ ለግል ጥቅም መዋሉም ተጠቅሷል።
- ኤልሻዳይ ሶሮሮ ትሬዲግ የተባለ ድርጅት ከሚያስመጣቸው መኪኖች ውስጥ አራት ደብል ጋቢና ፒካፕ መኪኖችን ለእርዳታ ከተወሰደ 6 ሺህ 450 ኩንታል ስንዴ ወይም በብር 6 ሚሊዮን 450 ሺህ ብር በመለወጥ መኪኖቹን ወስዷል ተብሏል።
- ኤልሻዳይ ለነጃ ሄሬዲን ወይም ሂራ የምግብ ማቀነባበሪያ ፋብሪካ 15 ሺህ ኩንታል ስንዴ በብር 15 ሚሊዮን ብር በመሸጥ ገንዘቡን መወሰዱም ተጠቅሷል።
ኮሚሽነሩ እና ቤተሰቦቻቸው ከኤልሻዳይ ማኅበር በተሰጠ ገንዘብ በቤተሰቦቻው ስም ያፈሩትም ንብረት ፖሊስ ጠቅሷል።
- ከኤልሻዳይ ተገኘ በተባለው ገንዘብ በልጃቸው ስም ቶዮታ ኮሮላ መኪና ከመግዛት በተጨማሪ ይኸው ልጅ ከግብረ ሰናይ ድርጅቱ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በወር 15 ሺህ ብር ግቢ የቤት ኪራይ እየተከፈለለት የቆየ መሆኑም ተገልጿል።
- ሁለተኛዋ ልጃቸው በኤልሻዳይ ተቀጣሪ ባትሆንም ስሟ በደመወዝ መክፈያ ዝርዝር ገብቶ ለ1 ዓመት ያህል በወር 5 ሺህ ብር ተከፍሏታል፤ እንዲሁም ከተቋሙ 893 ሺህ 25 ብር ገቢ መደረጉም ነው የተነገረው።
- በባለቤታቸው ስም ከኤልሻዳይ ማህበር ወጪ በተደረገ 8 ሚሊዮን 306 ሺህ ብር፣ በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ 388 ካሬ ሜትር አፓርታማ መገዛቱ ተጠቅሷል።
- በባለቤታቸው ስም በተጨማሪ በሃዋሳ ከተማ በ9.8 ሚሊዮን ብር 400 ካሬ ሜትር ሶስት ፎቅ ቤት መገዛቱም ተገልጿል። ቤቱ ለባለቤታቸው ከተገዛም በኋላ ኤልሻዳይ ድርጅት እንዲከራየውም መደረጉም ተነግሯል።በተጨማሪ በቦሌ ክፍለ ከተማ ከእንይ ሪል ስቴት አንድ ቤት ተገዝቶላቸዋል ተብሏል።
- በተጨማሪም ለእናታቸው ከግብረ ሰናይ ድርጅት 5 ሚሊዮን ብር ገቢ መደረጉን፣ ሰባት ቤቶች መገዛቱንና እንዲሁም በሳቸው ስም በተከፈቱ ሁለት የባንክ ሂሳብ ቁጥሮች 19.5 ሚሊዮን ብር መገኘቱ ተነግሯል።
ምርመራው እንዳልተጠናቀቀና ሌሎችም ከኮሚሽኑ በመቶ ሚሊዮን ብሮች ወጥተዋል የተባሉ ገንዘቦች እንዲሁም በቤተሰቦቻቸው የተገዙ ቤቶች፣ መኪኖችና ሌሎች የጥቅም ትስስሮች ላይ ምርመራ እየተከናወነ መሆኑን ፖሊስ ገልጿል።












