ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት ስለተጋራው ተንቀሳቃሽ ምሥል ምላሽ ሰጠ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት የተሠራጨው ተንቀሳቃሽ ምሥል የተከሰተውን ነገር እውነታ በትክክል የሚያሳይ አይደለም ሲል ማስተባበያ ሰጠ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን ውስጥ የተቀረጸው ተንቀሳቃሽ ምሥል እንዲት ተሳፋሪ በአየር መንገዱ ሠራተኞች ከአውሮፕላኑ እንድትወርድ ስትጠየቅ እና ተሳፋሪዋ አልወርድም እያለች ከሠራተኞቹ ጋር የምታደርገውን የተካረረ ክርክር ያሳያል።
ጉዳዩ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ መነጋገሪያ የሆነው እና በኢትዮጵያ አየር መንገድ ላይ ወቀሳ እና ቃውሞ የቀረበው ታዋቂው ኬንያዊ የሲንኤንኤን ጋዜጠኛ ላሪ ማዶዎ በተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ ገጾቹ ላይ ቪዲዮውን ከጋራ በኋላ ነው።
ላሪ ካጋራው ቪዲዮ ጋር ባሰፈረው ጽሑፍ እንደገለጸው፤ “ተጓዧ እንድትወርድ የተጠየቀችው የሚኒስትር ማዕረግ ባለው የመንግሥት ባለሥልጣን ወንበሯ በመያዙ ነው” ብሏል።
“ይቅርታ አልጠየቋትም እየጮኽች በኃይል ከአውሮፕላኑ አስወርደዋታል። ሚኒስትሩን ምንም ያደረጉት ነገር የለም። አሳፋሪ ነው” ሲል ጋዜጠኛ ላሪ ማዶዎ ጽፏል።
ጋዜጠኛው ቪዲዮን በኤክስ፣ በቲክ ቶክ እና በፌስቡክ ገጾቹ ላይ አጋርቶ በአጠቃላይ ከ8 ሚሊዮን ጊዜ በላይ ታይቷል።
ይህን ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድ እሁድ ሐምሌ 14/2016 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት የተሰራጨው ተንቀሳቃሽ ምሥል እውነታውን የሚገልጽ አይደለም ብሏል።
አየር መንገዱ አርብ ሐምሌ 12/2016 ዓ.ም. ከአዲስ አበባ ተነስቶ ወደ ናይሮቢ ኬንያ ለተደረገው በረራ ከወንበር ቁጥር በላይ ተሳፋሪዎች ትኬት መቁረጣቸውን ገልጿል።
ሦስት “ተጠባባቂ የኢኮኖሚ ክፍል ቲኬት” የያዙ መንገደኞች አውሮፕላኑ ስለሞላ በቀጣይ በሚኖረው በረራ እንደሚጓዙ ተገልጾላቸው አውሮፕላን መሳፈር እንደማይችሉ በሠራተኞቹ እንደተገለጻቸው አየር መንገዱ አስታውቋል።
በአየር መንዶች አሠራር “ተጠባባቂ ቲኬት” የያዘ ተጓዥ፤ ሁሉም ተሳፋሪ በሰዓቱ ሳይገኝ የሚቀር ከሆነ በሚኖረው ትርፍ ቦታ ብቻ እንዲሳፈሩ ይፈቀድላቸዋል።
አየር መንገዱ ከሦስቱ ተጓዦች ሁለቱ ከአውሮፕላኑ ለመውረድ ፍቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው በፀጥታ አባላት እንዲወርዱ ተደርጓል ብሏል።
አየር መንገዱ ጨምሮም በስፋት በተጋረው ቪዲዮ ላይ የምትታየው መንገደኛ እንዳትሳፈር የተከለከላችው ቦታዋ የሚኒስትር ማዕረግ ባለው ባለሥልጣን ስለተያዘባት ነው የተባለውን አስተያየትም ትክክል አይደለም ሲል አጣጥሎታል።
መንገደኛዋ ቲኬት የገዛችው በኢኮኖሚ ክፍል መሆኑን እና በቢዝነስ ክፍል ይበር ከነበረው እና ኢትዮጵያዊ ዜግነት ካለው መንገደኛ ጋር ምንም የሚያገናኛት ነገር የለም ብሏል።
“ሁኔታውን ሲመለከቱ በነበሩ ተሳፋሪዎች ዘንድ ወንበር ለሌላ ተሳፋሪ ተላልፎ ተሰጥቷል የሚል የተሳሳት እምነት አደረ። የሆነው ይህ አይደለም። የተሠራጨው ምሥል የተፈጠረውን ትክክለኛ ሁኔታ የሚገልጽ አይደለም” ብሏል አየር መንገዱ።
አየር መንገዱ በመጨረሻም በዕለቱ በረራቸውን ማድረግ ያልቻሉ ተሳፋሪዎች በቀጣይ በረራ ወደ መዳረሻቸው እንዲበሩ መደረጉን ጨምሮ ገልጿል።
ይህ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት መነጋገሪያ ስለሆነው ተሳፋሪዎችን ከአውሮፕላን የማስወረድ ክስተትን በተመለከተ አሁንም ድረስ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡ ነው።