ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ትራምፕ በሺዎች ሊሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው በጥይት የተመታሁት “ለዴሞክራሲ ነው” ሲሉ ተናገሩ
ዶናልድ ትራምፕ በሚሺጋን ግዛት በምርጫ ቅስቀሳቸው ለተገኙ በሺዎች ለሚቆጠሩ ደጋፊዎቻቸው ባደረጉት ንግግር በጥይት የተመታሁት “ለዴሞክራሲ ነው” አሉ።
ትራምፕ ከአንድ ሳምንት በፊት በፔንስልቬኒያ ግዛት የምርጫ ቅስቀሳ እያደረጉ ሳለ የግድያ ሙከራ ተፈጽሞባቸው እንደነበረ ይታወሳል።
የግድያ ሙከራውን የፈጸመው የ20 ዓመት ወጣት የቀድሞውን ፕሬዝዳንት ጭንቅላት ዒላማ አድርጎ የተኮሰው ጥይት ጭንቅላታቸውን ለጥቂት ስቶ ቀኝ ጆሯቸውን በስቷል።
ትራምፕ ከተፈጸመባቸው የግድያ ሙከራ በኋላ በሰጡት አስተያየት “በዕድል ወይም በፈጣሪ ጥበቃ” ከሞት በተዓምር አምልጫለሁ ብለው ነበር።
የሪፐብሊካን ፓርቲ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ የሆኑት ትራምፕ፤ ከተፈጸመባቸው የግድያ ሙከራ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ምርጫውን ካሸነፉ ምክትል ፕሬዝዳንት አድርገው ከሚሾሟቸው ጄዲ ቫንስ ጋር ቅስቀሳ ለማድረግ መድረክ ላይ ወጥተዋል።
ትራምፕ በምርጫ ቅስቀሳቸው ተቀናቃኞቻቸው “ለዴሞክራሲ ስጋት ነህ” ቢሉኝም “በጥይት የተመታሁት ለዴሞክራሲ ስል ነው” የሚል ንግግር አሰምተዋል።
የቀድሞው ፕሬዝዳንት ወደ ዋይት ሃውስ ለመመለስ ዝግጁ መሆናቸውን ሲናገሩ ከደጋፊዎቻቸው ሞቅ ያለ ጭብጨባ ተደርጎላቸዋል።
በምርጫ ቅስቀሳው ላይ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ደጋፊ የተገኘ ሲሆን፤ ከዚህ ቀደም በነበረው ቅስቀሳ ላይ ተኩስ ተከፍቶ አንድ ሰው ቢገደልም ይህ ስጋት ሳይፈጥርባቸው መገኘታቸውን ተናግረዋል።
አንዳንዶች ደግሞ በትለር በተባለችው ከተማ ትራምፕ ላይ ተኩስ መከፈቱ ብቻ በዚህ የምርጫ ቅስቀሳ ላይ እንዲገኙ ምክንያት እንደሆናቸው ተናግረዋል።
በምርጫ ቅስቀሳው ላይ ከተሳተፉ በርካታ ወጣቶች መካከል አንዱ የሆነው የ24 ዓመቱ ወጣት “የግድያ ሙከራ ከተፈጸመባቸው በኋላ የተደረገ የምርጫ ቅስቀሳ ስለሆነ በዚህ ስፍራ መገኘት ትልቅ ትርጉም አለው” ብሏል።
ባሳለፍነው ሳምንት ቶማስ ማቲው ክሩክስ የተባለ የ20 ዓመት ወጣት ከ200 ሜትር ባነሰ ርቀት ውስጥ ሆኖ ትራምፕን ለመግደል ቢያንስ አምስት ጊዜ መተኮሱ ይታወሳል።
ይህ ወጣት ከአሜሪካ ደኅንነት አባላት ዕይታ ውጪ ሆኖ ይህንን ጥቃት እንዴት ሊፈጽም ቻለ ሲሉ በርካታ አሜሪካውያን ጠይቀዋል።
በቀድሞው ፕሬዝዳንት ላይ የተፈጸመው የግድያ ሙከራ ላይ የሚደረገው ምርመራ እንደቀጠለ ሲሆን ወጣቱ ጥቃቱን ለመፈጸም ምን እንዳነሳሳው እስካሁን አልታወቀም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በኮቪድ-19 የተያዙት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የምርጫ ቅስቀሳቸውን ገታ አድርገዋል።
ፕሬዝዳንቱ በፓርቲቸያው አባላቶች እራሳቸውን ከምርጫው እንዲያገሉ ጫናው ቢበዛባቸውም፤ ባይደን በምርጫ ተሳታፊነታቸው እንደሚቀጥሉ እየገለጹ ይገኛሉ።
ትራምፕ ትናንት ቅዳሜ በነበራቸው የምርጫ ቅስቀሳ ላይ፤ “ዴሞክራቶች ችግር ገጥሟቸዋል። እነርሱም ሆኑ እኛ ፕሬዝዳንታዊ ዕጩ ማን እንደሚሆን አናውቅም” ብለዋል።