ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የሶማሊያ መንግሥት ከግብፅ ጋር ተደርሷል የተባለውን የወታደራዊ ትብብር ስምምነት አጸደቀ
የሶማሊያ መንግሥት ካቢኔ ከወራት በፊት ከግብፅ ጋር ተደርሷል የተባለው ወታደራዊ ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ተቀብሎ አጸደቀ።
ዝርዝሩ ይፋ ያልተደገው ይህ ወታደራዊ ስምምነት የሶማሊያ ካቢኔ አርብ ሐምሌ 12/2016 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባው ማጽደቁን የአገሪቱ ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።
እአአ 2024 መጀመሪያ ላይ ኢትዮጵያ የባሕር በር የሚያስገኝላትን ስምምነት ከሶማሊያ ተገንጥላ ነጻ አገርነቷን ካወጀችው ሶማሊላንድ ጋር መፈረሟን ተከትሎ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ወደ ካይሮ ባቀኑ ወቅት ግብፅ እና ሶማሊያ ወታደራዊ ስምምነት ሊፈራረሙ ይችላሉ ተብሎ ነበር።
ይሁን እንጂ ይህ ወታደራዊ ስምምነት ስለመፈረሙ በይፋ የተባለ ነገር ሳይኖር ቆይቶ ባሳለፍነው አርብ የሶማሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሐምዛ አብዲ ባሬ በመሩት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ስብሰባ መጽደቁ ተገልጿል።
ይህ በሶማሊያ ካቢኔ ተግባራዊ እንዲሆን የጸደቀው ወታደራዊ ስምምነት ይዘት ዝርዝር እስካሁን በየትኛውም ወገን ይፋ አልተደረገም።
ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ ብዙ ያወዛገበውን የባሕር በር ስምምነት የመግባቢያ ሰነድ በተፈራረሙ በቀናት ልዩነት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ከግብፁ አቻቸው አብዱል ፋታህ አል-ሲሲ ጋር በስልክ ተነጋግረው ነበር።
በወቅቱ የግብፅ ፕሬዝዳንት ቃል አቀባይ አሕመድ ፋሚ ሁለቱ መሪዎች በስልክ በነበራቸው ውይይት ላይ አል-ሲሲ “ግብፅ ከሶማሊያ ጎን ለመቆም ያላትን ጠንካራ አቋም” ገልጸዋል ብለው ነበር።
በስልክ ንግግር ብቻ ያልተገደቡት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት፤ ከግብፅ አቻቸው የቀረባለቸውን ጥሪ ተከትሎ መከላከያ ሚኒስትራቸውን አስከትለው ባለፈው ጥር ወር ወደ ካይሮን አቅንተው ነበር።
በጎበኙበት ወቅት የግብፁ ፕሬዝዳንት አብደል ፋታህ አል ሲሲ በማንኛውም ሁኔታ የሶማሊያን ሉዓላዊነት ለመከላከል ካይሮ ከሞቃዲሾ ጎን እንደምትቆም መግለጻቸው ይታወሳል።
በጉብኝቱ ወቅትም ግብፅ እና ሶማሊያ ያላቸውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር እና በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ አብሮ በመሥራት ዙሪያ መወያየታቸው የተነገረ ሲሆን፣ አገራቱ ወታደራዊ ስምምነትን የሚጨምር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ትብብር ለማድረግ ስምምነት ይፈራረማሉ ተብሎ ነበር።
ይሁን እንጂ ወታደራዊ ስምምነቱ ስለመፈረሙ በይፋ የተባለ ነገር ሳይኖር ቆይቶ የሶማሊያ ካቢኔ አርብ ዕለት በሁለቱ አገራት መካከል የተፈረመው የመከላከያ ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን ውሳኔ አስተላልፏል ተብሏል።
ይህ ስምምነት ግብፅ እና ሶማሊያ በወታደራዊ መስክ ትብብር እንዲያደርጉ ከማስቻሉ በተጨማሪ ፤ የሶማሊያ የመከላከያ እና የደኅንነት አቅምን ለማሻሻል የሚያስችሉ ተጨማሪ ድጋፎችን፣ ሥልጣናዎችን እንዲሁም የመረጃ ልውውጥ እንደሚኖር ተገልጿል።
ግንባታው በሊጠናቀቅ በተቃረበው የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ምክንያት ከኢትዮጵያ ጋር ለዓመታት በዘለቀ ውዝግብ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፣ ከሶማሊያ ጋር የተፈመው ወታደራዊ ስምምነት ግብፅ በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር የምትሞክረብት እንደሆነ ይታመናል።
ይህ የሶማሊያ እና የግበፅ ወታደራዊ ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን የሶማሊያ ካቢኔ ማሳለፉ ኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የተፈራረሙትን የመግባቢያ ሰነድ ወደ ተግባር ለመለወጥ ገፊ ምክንያት ሊሆን ይችላል እየተባለ ነው።
አዋዛጋቢውን የኢትዮጵያ እና ሶማሊላንድ የባሕር በር ስምምነት ተከትሎ ሶማሊያ ከቱርክ ጋር እንዲሁ ወታደራዊ ስምምነት መፈራረሟ ይታወሳል።
ሁለቱ አገራት ባለፈው የካቲት 1/2016 ዓ.ም. በተለያዩ ወታደራዊ ዘርፎች ትብብር ለማድረግ ስምምነት መፈራረማቸውን ይታወሳል።
የዚህ ስምምነት ዝርዝር ይፋ ባይሆንም ቱርክ የሶማሊያን ባሕር ኃይልን ለማሠልጣን እና ለማስታጠቅ እንዲሁም በአካባቢው ያለውን የባሕር ላይ ደኅንነት ለማስጠበቅ ተስማምታለች ተብሏል።
በአንጻሩ ቱርክ ከሶማሊያ የባሕር የተፈጥሮ ሃብት ተጠቃሚ እንደምትሆን ሪፖርቶች ይጠቁማሉ።
የአንካራ እና ሞቃዲሾ ስምምነትን ተከትሎ ሚያዚያ 15/2016 ዓ.ም. ዓይነቷ ያልተገለጸች ግዙፍ የቱርክ የጦር መርከብ ወደ ሞቃዲሾ ደርሳ ነበር።