ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ቴን ሃግ የቀድሞ የዩናይትድ አስልጣኝ ራይኒክ ስለቡድኑ ችግሮች የተናገሩት ትክክል ነበር አሉ
የማንቸስተር ዩናይትድ ጊዜያዊ አሰልጣኝ የነበሩት ራልፍ ራይኒክ ቡድኑ ያለበትን ችግር ለመፍታት የሰጡት አስተያየት ትክክል ነው ሲሉ አሰልጣኝ ኤሪክ ቴን ሃግ ተናገሩ።
ራይኒክ ክለቡ ያላበትን ውስብስ ችግር ለመግለጽ “የልብ ቀዶ ጥገና” ያህል ከባድ ሥራ ያስፈልገዋል ብለው ነበር።
ቴን ሃግ የቀድሞ አስልጣኝ የሰጡት አስተያየት “ፍፁም ትክክል ነው” ብለዋል።
የ54 ዓመቱ ቴን ሃግ ቡድኑን እንዲመሩ በ2022 የተሰየሙት ቡድኑን ለሰባት ወራት ከመሩት ራይኒክ በኋላ ነው።
በአሁኑ ወቅት የኦስትሪያ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ የሆኑት ጀርመናዊው ራይኒክ፤ ዩናይትድ በፕሪሚዬር ሊጉ ስድስተኛ ደረጃ እንዲይዝ ቢያስችሉም ካደረጓቸው 29 ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻሉት አስራ አንዱን ብቻ ነው።
ራይኒክ ክለቡ "የልብ ቀዶ ጥገና” እንደሚያስፈልገው እና ችግሮቹ "በጥቃቅን ለውጦች" ሊፈቱ እንደማይችሉ ተናግረው ነበር።
በዚህ ወር የአንድ ዓመት የኮንትራት ማራዘሚያ የፈረሙት ቴን ሃግ የራይኒክ ትንታኔ ትክክል ነበር ብለዋል።
ቴን ሃግ ከደቹ አድ ስፖርትወረልድ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “ራይኒክ በጣም ትክክል ነበር" ሲሉ ተናግረዋል።
"በዚህ ላይ ለሁለት ዓመታት ጠንክረን ስንሠራ ብንቆይም በትክክል ገልጾታል። ጥልቅ፣ በጣም ውስብስብ ቀዶ ጥገና ነው። ሥራውን ስረከበት ከባድ እንደሚሆን አውቅ ነበር።"
ሰር ጂም ራትክሊፍ ባለፈው ታህሳስ ወር የክለቡ 27.7 በመቶ ድርሻ ከገዙ በኋላ ዩናይትድ ከሜዳ ውጭ ብዙ ለውጥ አድርጓል።
ኦማር በራዳ፣ ዳን አሽዎርዝ፣ ጄሰን ዊልኮክስ እና ክሪስቶፈር ቪቭል የክለቡን ቦርድ ተቀላቅለዋል። ክለቡ የልምምድ ሜዳውን ለማሻሻል የ50 ሚሊዮን ፓውንድ ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል።
አጥቂው ጆሹዋ ዘርከዚ እና ተከላካዩ ሌኒ ዮሮ ከቦሎኛ እና ሊል ቡድኑን ተቀላቅለዋል። ቴን ሄግ የባየር ሙኒኩን እና የኔዘርላንዱን የመሃል ተከላካይ ማቲያስ ደ ሊት ለማስፈረም ፍላጎት እንዳላቸውም አረጋግጠዋል።
“ደ ሊት ስለመምጣቱ የምናየው ነገር ይሆናል” ብለዋል ቴን ሃግ።
በቀድሞው ክለባቸው አያክስ ከደ ሊት ጋር የሠሩት ቴን ሃግ፤ የመሐል ተከላካዩን የዝውውር ዒላማ አድርጎ ያቀረበው የዩናይትድ የተጫዋች ምልመላ ክፍል ነው ብለዋል።
ከእሳቸው ጋር በተፈጠረ አለመግባባት ያለፈውን ዓመት የውድድር ዘመን ሁለተኛ አጋማሽ በውሰት በዶርትሙንድ ያሳለፈው አጥቂው ጄደን ሳንቾ በድጋሚ ለቡድኑ እንደሚጫወት ቴን ሃግ አረጋግጠዋል።
"ሁሉም ሰው ሊሳሳት ይችላል" ብለዋል ቴን ሃግ።
ትላንት ምሽት ማንቸስተር ዩናይትድ በሁለተኛው የቅድመ ውድድር ዘመን ጨዋታ ሬንጀርስን 2 ለምንም ሲያሸንፍ አማድ ዲያሎ እና ጆ ሁጊል ጎሎችን አስቆጥረዋል። በጨዋታው ላይ ሳንቾ እና አዲስ ፈራሚው ዮሮ ተሰልፈው ተጫውተዋል።
“የቡድኑ ደረጃ በጣም ተሻሽሏል። አሁን ለማየት አስደሳች እየሆነ ነው” ሲሉ ቴን ሃግ ለቡድኑ የቴሌቭዥን ጣብያ ከጨዋታው በኋላ ተናግረዋል።