ካማላ ሃሪስ በድጋሚ ለአሜሪካ ፕሬዝዳንትነት ሊወዳደሩ እንደሚችሉ ተናገሩ

የቀድሞዋ የአሜሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሃሪስ በድጋሚ ወደ ዋይት ሐውስ ለመግባት ሊወዳደሩ እንደሚችሉ ለቢቢሲ ተናገሩ።
ካማላ ሃሪስ ለመጀመሪያ ጊዜ በዩናይትድ ኪንግደም በሰጡት ቃለ ምልልስ "ምን አልባት" አንድ ቀን ፕሬዝዳንት እንደሚሆኑ የገለጹ ሲሆን፣ ወደፊት በዋይት ሐውስ ሴት ፕሬዝዳንት እንደምትኖር ግን አስረግጠዋል።
ባለፈው ዓመት በተካሄደው ምርጫ በዶናልድ ትራምፕ ከተሸነፉ በኋላ በአውሮፓውያኑ 2028 በሚካሄደው ምርጫ ለፕሬዝዳንትነት እንደሚወዳደሩ የተናገሩት የቀድሞዋ ምክትል ፕሬዝዳንት፣ለቀጣዩ ምርጫ የዲሞክራቲክ ፓርቲ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ያደረጋቸውን ምርጫ ውድቅ አድርገውታል።
ሃሪስ ለቢቢሲዋ ጋዜጠኛ ላውራ ኩይንስበርግ እሑድ ዕለት በሰጡት ቃለምልስ፣ የቀድሞ ተቀናቃኛቸው የነበሩትን ትራምፕን "አምባገነን" በማለት የፈረጇቸው ሲሆን፣ በምርጫ ቅስቀሳ ዘመቻ ወቅት ስለ እርሳቸው የሰጡት ማስጠንቀቂያ ትክክል መሆኑንም ተናግረዋል።
እርሳቸው የወከሉት ዲሞክራቲክ ፓርቲ፣ ከአንድ ዓመት በፊት በተካሄደው ምርጫ ሪፐብሊካኑ ዶናልድ ትራምፕ ለመሸነፋቸው ምክንያቱ ምን እንደሆነ መልስ የፈለገ ሲሆን፣ ያገኘው አብዛኛው ጥፋት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ቶሎ ከውድድሩ ራሳቸውን አለማግለላቸው ላይ ያነጣጠረ ነው።
ሆኖም ሃሪስ ራሳቸውም በአገሪቷ ወሳኝ በሆነው የምጣኔ ሃብት ጉዳይ ላይ ግልጽ ፖሊሲ በማስቀመጥ ጥሩ የምርጫ ቅስቀሳ አካሂደዋል ወይ በሚለው ላይም ጥያቄዎች ተነስተዋል።
ሃሪስ ባልተጠበቀ ሁኔታ ዕጩ ፕሬዝዳንት ሆነው የመቅረብ ዕድል ያገኙት በወቅቱ የዲሞክራቶች ዕጩ ሆነው ቀርበው የነበሩት ጆ ባይደን በዕድሜ መግፋት ምክንያት እራሳቸውን በድንገት ከፉክክሩ ካገለሉ በኋላ ነበር።
በቀሩት 107 የምርጫ ቅስቀሳ ቀናትም የፓርቲው አዲስ ተስፋ ሆነው የነበሩት ሃሪስ፣ የምርጫ ዘመቻውን በስተመጨረሻ ቢያጧጡፉትም ማሸነፍ ሳይችሉ ቀርተዋል።

ሃሪስ በቢቢሲው ቃለ ምልልሳቸው ላይ በቀጣይ ወደ ዋይት ሐውስ ለመመለስ ስላላቸው ዕቅድ ያነሱ ሲሆን፣ የልጅ ልጆቻቸው "በሕይወት ዘመናቸው በእርግጠኝነት ሴት ፕሬዝዳንት ያያሉ" ሲሉ ተናግረዋል።
እርሳቸው ሊሆኑ ይችሉ እንደሁ የተጠየቁት ሃሪስ "ምን አልባት" ሲሉ የመለሱ ሲሆን፣ ለከፍተኛ ኃላፊነት በድጋሚ ለመወዳደር እያሰቡ እንደሆነ ግን አረጋግጠዋል።
ምንም እንኳን ውሳኔ ላይ ባይደርሱም ወደፊት በፖለቲካው ላይ ራሳቸውን እንደሚያዩም አስምረዋል።
"አልጨረስኩም" ያሉት የቀድሞ ፕሬዝዳዳንቷ፣ "የሥራ ዘመኔን በሙሉ ያሳለፍኩት አገልግሎት በመስጠት ነው ይህ ደግሞ አጥንቴ ድረስ የዘለቀ ነው" ብለዋል።
ሃሪስ በቃለ ምልልሳቸው ላይ ያለፈውን የምርጫ ሂደት በተመለከተ ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
በምርጫ ቅስቀሳቸው ወቅት "ዶናልድ ትራምፕ የፋሽስታዊ እና የአምባገነን መሪ ባሕርይ አላቸው" ሲሉ የተነበዩትም አሁን ላይ መገለጡን እንደሚያምኑም ሃሪስ ተናግረዋል።
"ትራምፕ የፍትሕ መሥሪያ ቤቱን እንደ መሳሪያ ተጠቅሟል፤ በትክክል ያደረገው ይህንኑ ነው" ሲሉም ትችታቸውን ሰንዝረዋል።
ለዚህም የኤቢሲ የቴሌቪዥን ፕሮግራም አቅራቢ ኮሜዲያን ጂሚይ ኪሚል፣ የቀኝ ክንፍ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆነው ቻርሊ ከርክ ግድያ ላይ ሪፐብሊካኖች የሰጡትን ምላሽ በተመለከተ ቀልድ ከሠራ በኋላ መታገዱን ጠቅሰዋል።
ትራምፕን ያስደሰታቸው የጂሚ ኪሚል መታገድ የተሰማው በትራምፕ የተሾሙት የሚዲያ ተቆጣጣሪ ለመገናኛ ብዙኃኑ ማስጠንቀቂያ ከሰጡ በኋላ ነበር።
ሃሪስ ጨምረውም በአሜሪካ ያሉ የቢዝነስ መሪዎች እና ተቋማት ለፕሬዝዳንቱ ፍላጎት ያጎበደዱ ናቸው የሚል አመለካከት እንዳላቸው ገልጸዋል።
ዋይት ሐውስ ካማላ ሃሪስ በፕሬዝዳንቱ ላይ የሰጡትን አስተያየት አጣጥሏል።
የዋይት ሐውስ ቃል አቀባይ አቢጌል ጃክሰን "ካማላ ሃሪስ በሰፊ ልዩነት ምርጫውን ሲሸነፉ የአሜሪካ ሕዝብ የእርሷን የማይጨበጥ ውሸት እንደማይፈልግ ፍንጭ ሊወስዱ ይገባ ነበር" ብለዋል።
አስከትለውም "ምን አልባት ይህንን ፍንጭ ስላልወሰዱ ይሆናል ለውጭ መገናኛ ብዙኃን ቅሬታቸውን መግለጻቸው አላቆም ያሉት" ሲሉ ወርፈዋቸዋል።
ካማላ ሃሪስ ወደ ፖለቲካው መድረክ የተሸጋገሩት በዐቃቤ ሕግነት በሠሩባቸው ጊዜያት ባሳዩት ጽኑ የሕግ አቋም ነበር። በዚህም በአውሮፓውያኑ 2017 ለካሊፎርኒያ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባልነት መመረጥ ችለዋል።
ሃሪስ በ2020 ላይ ለፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር ቀርበው የነበረ ቢሆንም የሚያራምዱትን ርዕዮተ ዓለም እና የፖሊሲ አማራጭ በአግባቡ ለማቅረብ ችግር ስለገጠማቸው ብዙም አልገፉበትም። ነገር ግን የጆ ባይደን ምክትል በመሆን በምርጫው ውስጥ ቀጥለው ለአሸናፊነት በቅተዋል።
ካማላ ሃሪስ ባላፈው ዓመት በተካሄደው ምርጫ በዶናልድ ትራምፕ ባይሸነፉ ኖሮ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዝዳንት፣ የመጀመሪያዋ ጥቁር ሴት ፕሬዝዳንት እና የመጀመሪያዋ የሕንድ ዝርያ ያላቸው ፕሬዝዳንት ለመሆን ይችሉ ነበር።















