ወላጆችን እያሳሰበ ያለው ከ6 ዓመት ጀምሮ ያሉ ታዳጊዎች የወር አበባ እንዲያዩ የሚያደርጉ ምክንያቶች

ታዳጊዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አርካና የስድስት ዓመት ልጅ አላት። የልጇ ሰውነት ላይ ያልተለመዱ ለውጦች ማየት ስትጀምር ስጋት ገብቷታል።

“በዚህ ትንሽ ዕድሜዋ በትንሽ ነገር መበሳጨቷ ያስፈራኝና ያሳስበኝ ጀመር” ትላለች።

ለዚህ ዘገባ ሲባል ስሟ የተለወጠው አርካና የምትኖረው በምዕራብ ሕንድ፣ ሳታራ ግዛት በሚገኝ መንደር ውስጥ ከቤተሰቦቿ ጋር ነው።

የእርሻ ማሳ አቅራቢያ ያለ አነስተኛ ቤት ከባለቤቷ ጋር ሠርተው ይኖራሉ።አንድ ሴትና አንድ ወንድ ልጅ አላቸው።

ሴቷ የበኩር ልጃቸው ናት።

ከዕድሜዋ በላይ ትልቅ እየመሰለች ስትሄድ እናቷ ወደ ሕክምና ወሰደቻት።

'ለመቀበል ከብዶን ነበር'

ራሺ ደግሞ የምትኖረው ደልሂ ነው። እሷም በልጇ ላይ ያልተለመዱ ለውጦችን ማየት ጀመረች።

የስድስት ዓመት ልጇ ከብደት 40 ኪሎግራም ነበር። “ጤናማ ልጅ ናት” ብላም እናቷ ታምናለች።

ድንገት ግን ልጇ ደም እየፈሰሳት መሆኑን ለእናቷ ተናገረች።

ሐኪም ቤት ከሄዱ በኋላ ልጇ የወር አበባ ማየት መጀመሯን አወቁ።

“ይህንን ለመቀበል ከብዶን ነበር።ልጄ ሰውነቷ ምን እየሆነ እንደሆነ መረዳት አልቻለችም” ትላለች ራሺ።

አርካና ደግሞ የማሕፀን ሐኪም እንድታማክር ተነገራት።

ያነጋገረቻቸው ሐኪም ዶ/ር ሱሺሊ ጋሩድ የሚባሉ ሲሆን፣ በፑን በሚገኘው ማዘርሁድ ሆስፒታል ይሠራሉ።

በልጅቷ ሰውነት ውስጥ ያለው የሆርሞን መጠን በሷ ዕድሜ የሚገኙ ልጆች ካላቸው መደበኛ የሆርሞን መጠን ከፍ እንደሚል አስረዷት።

“ልጅቷ የምትጫወተው ቤት ውስጥ ያሉ 5 ኪሎግራም የሚመዝኑ የፀረ ተባይ ጠርሙሶች መሆኑ ነበር እናትየዋ የነገረችኝ። ሰውነቷ ላይ ለታየው ለውጥ መንስዔ ከሆኑት መካከል አንዱ ሊሆን ይችላል” ይላሉ ሐኪሙ።

ሴቶች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በልጆች ላይ የሚስተዋል ቅድመ ዕድሜ ዕድገት precocious puberty ወይም early puberty በሚል መጠሪያ በእንግሊዘኛ ይታወቃል።

ዕድገት በሴቶች ወይም በወንዶች ሰውነት ውስጥ ያለ ሂደት ሲሆን፣ ይህም የመራቢያ አካላትን ያካትታል።

ወንዶች ፊታቸውና መራቢያ አካላቸው ላይ ፀጉር ያበቅላሉ፤ ድምጻቸውም ይጎረንናል። አብዛኞቹ ሴቶች መራቢያ አካላቸው ላይ ፀጉር ያበቅላሉ፤ ጡታቸው ያድጋል፤ የወር አበባ ማየትም ይጀምራሉ።

ይህ የዕድገት ለውጥ በሴቶች ላይ ከ8 ዓመት እስከ 13 ድረስ፣ በወንዶች ላይ ደግሞ ከ9 ዓመት እስከ 14 ድረስ ይስተዋላል።

ዶ/ር ቫሻኪ ሩስተጊ የልጆችና ታዳጊዎች ሐኪም ሲሆኑ፣ በተለይም ደግሞ ከሆርሞን ጋር የተያያዙ ሕመሞችን ያክማሉ።

ባለሙያዋ እንደሚሉት፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት የሴቶች ዕድገት ላይ ለውጥ እያዩ ነው።

“ታዳጊ ሴቶች ሰውነታቸው ላይ ለውጥ ማየት ከጀመሩ ከ18 ወራት እስከ ሦስት ዓመት ድረስ ቆይቶ የወር አበባ ማየት ይጀምራሉ። አሁን ግን የወር አበባቸው የሚመጣው ከሦስት እስከ አራት ወራት ባለ ጊዜ ውስጥ ነው” ብለዋል።

ወንዶች ሰውነታቸው ላይ ለውጥ ማየት በጀመሩ በአንድ ዓመት እስከ አንድ ዓመት ተኩል ውስጥ ፂም ማብቀል ይጀምራሉ።ከዚህ ቀደም ግን በአራት ዓመታት ውስጥ ነበር የዕድገት ለውጥ ማሳየት የጀመሩት።

በሕንድ በሚገኘው የቻይልድ ኸልዝ ሪሰርች የሚሠሩት ዶ/ር ሹቺትራ ሱርቪ በሠሩት ጥናት የቅድመ ዕድሜ ዕድገት የሚታይባቸው ታዳጊዎች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።

በ2,000 ታዳጊ ሴቶች ላይ በተሠራ ጥናት እናቶች ልጆቻቸው ላይ ለውጥ ሲታይ ለመረዳት ይቸገራሉ።

ለቅድመ ዕድሜ ዕድገት የሚያጋልጡ መንስዔዎችና ምን ሊያስከትል ይችላል የሚለው ላይ ጥናት እየተደረገ ነው።

በ2020 ሙምባይ የሚገኘው ባይ ጀራቢ ዋዲያ ሆስፒታል ከስድስት ዓመት እስከ ዘጠኝ ዓመት ያሉ ሴት ልጆች እንዴት ለቅድመ ዕድሜ ለውጥ እንደሚጋለጡ ጥናት ሠርተዋል።

ዶ/ር ሱድራ ራው “ከስድስት ዓመት እስከ ዘጠኝ ዓመት ያሉ 60 ልጆች ቅድመ ዕድሜ ዕድገት ገጥሟቸዋል። አንዳንዶቹ የወር አበባ ማየት ጀምረዋል” ሲሉ ስለ ምርምሩ ውጤት ያስረዳሉ።

የወር አበባ ንጽህና መጠበቂያ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ቅድመ ዕድሜ ዕድገት ለምን ይከሰታል?

ለቅድመ ዕድሜ ዕድገት የሚያጋልጡ ምክንያቶች ብዙ እንደሆኑ ዶክተሮች ይናገራሉ።አንድ መንስዔ ብቻ የለውም።

ፀረ ተባይ፣ ምግብን ለረዥም ጊዜ ለማቆየት የሚውል ኬሚካል፣ የአየር ብክለትና ከፍተኛ የሰውነት ውፍረት ምክንያት ናቸው።

ዶ/ር ፕሪሻንት ፓቴል በሙምባይ በሚኖሩ ታዳጊ ሴቶች ላይ በሠሩት ጥናት ከልክ ያለፈ ውፍረት ዋነኛው መንስዔ እንደሆነ ለማወቅ ችለዋል።

ከኮቪድ-19 ወዲህ ችግሩ እየተባባሰ መጥቷል።

የዓለም ጤና ድርጅት እንዳለው፣ እአአ በ2022 ዕድሜያቸው ከ5 እስከ 19 የሆነና ከ390 ሚሊዮን በላይ የሚጠጉ ሕጻናትና ታዳጊዎች ወፍራም የሆኑ ሲሆን 160 ሚልዮኑ ደግሞ ከልክ ላለፈ ውፍረት ተጋልጠዋል።

ታዳጊ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ከልክ ያለፈ ውፍረት መከሰቱን ማወቅ የሚቻለው የሰውነት ክብደትን፣ ከፆታ፣ ዕድሜና ቁመት አንጻር በመለካት ነው።

ለረዥም ሰዓት ስልክና ቴሌቭዥን እንዲሁም ሌሎች ኤሌክትሮኒክሶች መጠቀምና የአካል ብቃት እንቅስቃሴ አለማድረግ ከልክ ላለፈ ውፍረት ከሚዳርጉ መካከል ይጠቀሳሉ።

የሕክምና ባለሙያዋ እንደሚሉት ባለፉት ሦስት ዓመታት እስከ ስድስት የሚደርሱ ታዳጊ ሴቶች የወር አበባቸው ቀድሞ መምጣቱ ተመዝግቧል።

“እናቶች በልጆቻቸው ሰውነት ላይ ለውጥ ባዩ በጥቂት ወራት ውስጥ ልጆቹ የወር አበባ ማየት መጀመራቸውን ይናገራሉ። በወንዶች ላይም ለውጥ እየታየ ነው” ይላሉ።

ልጆች ስክሪን ላይ የሚያሳልፉት ጊዜ ለቅድመ ዕድሜ ዕድገት ከሚዳርጉ ምክንያቶች መካከል እንደሚጠቀስ ሐኪሟ ይናገራሉ።

የአርካና እና የራሺ ልጆች የወር አበባቸውን 10 ወይም 11 ዓመት እስከሚሞላቸው ድረስ የሚያዘገይ መድኃኒት እየወሰዱ ይገኛሉ።

አሁን ባሉበት ዕድሜ ራሳቸውን መንከባከብ ወይም ንጽሕናቸውን መጠበቅ እንደማይችሉ ዶክተሮች ይገልጻሉ።

ቅድመ ዕድሜ ዕድገት የሚገጥማቸው ልጆች የሥነ ልቦና ጫና እንደሚያድርባቸው ባለሙያዎች ያስረዳሉ።

ዕድሜ ልካቸውን የሰውነታቸው ገጽታ ለመቀበል እንደሚቸገሩና ያለ ዕድሜያቸው በሰውነታቸው ላይ በታየው ለውጥ ምክንያት ከዕድሜ እኩዮቻቸው ማንጓጠጥ ሊገጥማቸው እንደሚችልም ያክላሉ።