‘ልጄ መሞቱን ያወቅኩት በማኀበራዊ ሚዲያ ነው’

የማይታወቁ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታይቶ በማይታወቅ ቁጥር አፍሪካውያን ወጣቶች ኬኔሪ ወደ ተሰኘችው ደሴት ለመድረስ ህይወታቸውን አደጋ ላይ እየጣሉ ነው።

ኬኔሪ ወጣቶች ተስፋ የሚያደርጉትን አውሮፓ ለመርገጥ መሸጋገሪያ ነች።

የስፔን የግዛት አካል በሆነችው በዚህች ደሴት እና በሌሎች መንገዶች የሚደረጉ ፍልሰቶች የፈጠሩት ቀውስ ላይ ለመምከር ስፔን ከሴኔጋል፣ ሞሪታንያ እና ጋምቢያ መንግሥታት ጋር ተቀምጣለች።

ይህ የመንግሥታቱ ምክርር ግን ለአሚና ምንም ነው።

አሚና ከሴኔጋል ዋና ከተማ አቅራቢያ በሚገኝ አካባቢ ካለው ቤቷ ለቢቢሲ በሰጠችው ቃለ መጠይቅ ለስደት የወጣው “ልጄ መሞቱን የተረዳሁት በማኀበራዊ ሚዲያ ነው” ብላለች።

“ከልጄ ጋር ሁልጊዜ እናወራ ነበር። ሞሮኮ መሄድ እንደሚፈልግም ነግሮኝ ነበር” ትላለች የ50 ዓመቷ አሚና።

“በጀልባ ለመሄድ እንዳቀደ ግን አልነገረኝም ነበር” ስትል ታብራራለች።

የልጇን ያንኮሃባ ድምጽ ለመጨረሻ ግዜ ባለፈው ጥር ወር ነበር የሰማችው።

ከዚያ በኋላ ደብዛው ጠፋ።

እናት የ33 ዓመት ልጇን ለማግኘት ያደረገችው ጥረት በሙሉ ፍሬ አላፈራም።

ጥቂት ከቆየ በኋላ በሐምሌ ወር መጨረሻ በአትላንቲክ ውቅያኖስ ሌላኛው አቅጣጫ ከዶሚኒካ ሪፐብሊክ 18 ኪሎ ሜትሮችን ርቆ አሳ አጥማጆች አስክሬኖችን አገኙ። ከእነዚህ አስክሬኖች አንዱ የአሚና ልጅ ነው።

ሕይወታቸው ካለፈ እንደቆዩ የሚያስታውቅ ቢያንስ 14 አስክሬኖች በእንጨት ጀልባ ላይ መገኘቱን ፖሊስ ገልጿል።

አብሯቸውም ሞባይል ስልክ እና ሰነዶች የተገኙ ሲሆን አብዛኞቹ ከሴኔጋል፣ ሞሪታኒያ እና ማሊ እንደተነሱ የሚያመለክቱ ናቸው።

ከተገኙት ሰነዶች ውስጥ የአሚና ልጅ የዮንኮሃብ መታወቂያ ወረቀት ይገኝበታል።

የዶሚኒካ ባለስልጣናት አደንዛዥ ዕጽ የያዙ 12 እሽጎችን ከአስክሬኖቹ ጋር ማግኘታቸውንም ተናግረዋል።

የሞታቸው መንስኤ እና ጊዜ መቼ እንደሆነ እየተጣራ ቢሆንም ወደ ኬኔሪ ደሴት እየተጓዙ ሳለ አደጋ እንደገጠማቸው ተገምቷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሲጠቀሙበት የነበረው ጀልባ ሙሉ ለሙለ ከእንጨት የተሰራ እና አሳ ለማጥመድ የተዘጋጀ ሲሆን አብዛኛውን ጊዜ ሕገወጥ ስደተኞች ከምዕራብ አፍሪካ ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሚጠቀሙበት ነው።

ወደ ያንኮሆባ እንመለስ።

ያንኮሆባ ለእናቱ የመጀመሪያ እና ብቸኛ ልጅ ነው። በሴኔጋል በዚህ መልኩ መፈጠር ደግሞ ከከባድ ኃላፊነት ጋር የሚተሳሰር ነው። የመጀመርያ እና ብቸኛ ልጅ መሆን ቤተሰብን ተሸክሞ የማሻገር ኃላፊነት ነው።

ልብስ ሰፊ የነበረው የአሚና ልጅ ባለትዳር የነበረ ሲሆን ሁለት ልጆችም ነበሩት። እንደ አለመታደል ሆኖ ሁለተኛው ልጅ ከአባቱ ሞት በኋላ ነበር የተወለደው።

አሚና የልጇን ሞት ከመረዳቷ አስቀድሞ ልጇን ለመፈለግ አልቦዘነችም ነበር። በአገሪቷ ያሉ ከፍተኛ ተከታይ ያላቸውን የፌስቡክ ተጽዕኖ ፈጣሪዎች ልጆቿን እንዲያፋልጉላት ስትማጸን ነበር።

“ልጄ በሞሮኮ ወይም ቱኒዚያ የሆነ ቦታ ታስሮ ይሆናል የሚል እምነት ነበረኝ” ስትል ድምጿ እየተቆራረጠ ነበር።

አሁን አሁን ከምዕራብ አፍሪካ የሚነሱ ስደተኞች አውሮፓን ለመርገጥ ከሜድትራንያን ይልቅ ኬኔሪ ደሴትን የሚመርጡበት ሁኔታ በከፍተኛ ቁጥር እየጨመረ ነው።

ይህ የሆነበት ምክንያት ደሴቷ ጋር ለመድረስ የሰሃራ በርሃን እና የሜዲትራኒያን ባህርን ማቋረጥ የግድ ስለማይሆን ነው።

ባለፈው ዓመት ብቻ አትላንቲክን ተጠቅመው ወደ አውሮፓ ለመግባት የጣሩ ስደተኞች ቁጥር ከባለፈው ዓመት አንጻር በ161 በመቶ እንደጨመረ የአውሮፓ ሕብረት የድንበር ኤጀንሲ ገልጿል።

ስፔን ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ስደተኞች ከሚቀበሉ የአውሮፓ አገራት አንዷ ናት።

በሴኔጋል የሚገኙ መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሠራተኞች ከአውሮፓ ይልቅ ውድ ነው የሚባለውን የአሜሪካ ጉዞ ይመርጣሉ። ይህም እየጨመረ መጥቷል።

ቢቢሲ ያነገረው ፍውሉም ይህንን ነው ያደረገው።

በዳካር ለ10 ዓመታት ውጤታማ የሆነ የበግ እና ዶሮ እርባታ ንግድ ላይ ተሰማርቶ ቢቆይም መፈተን ጀምሮ ነበር።

“መንቀሳቀስ እንዳቃተኝ ይሰማኝ ነበር። ከምሰራው ንግድ በተጨማሪ ፋብሪካ ውስጥ ተቀጥሬ ነበር፤ ነገር ግን ፍላጎቴን ማሟላት አልቻልኩም ነበር” ሲል ያስታውሳል።

ልክ 30 ዓመት ሲሞላው ያለውን ንብረት ሁሉ ሽጦ ወደ ማዕከላዊ አሜሪካዋ ሀገር ኒኳራጋዋ የመሄጃ ትኬት ቆረጠ።

ከዚያች አገር የየብስ ጉዞ አድርጎ ወደ አሜሪካ ለመግባት ሞክሮ ነበር።

አሜሪካ የሚኖረው ታላቅ ወንድሙ ይህንን ጉዞ እንዲያደርግ ሲያበረታታው ነበር።

ያም ብቻ ሳይሆን ቁጥር ስፍር የሌላቸው ሴኔጋላውያን እንዴት ከመካከለኛው አሜሪካ ወደ አሜሪካ እንደ ተሸጋገሩ የሚገልጹበትን ቨዲዮ በቲክቶክ ተመልከቷል።

“እናቴ እንድሄድ አልፈለገችም ነበር። ነገር ግን እኔ ሞትን ለመጋፈጥ ተዘጋጅቼ ነበር” ይላል።

ፋውሉ ለ16 ቀናት በሕገወጥ አዘዋዋሪዎች ታግዞ ኒካራጉዋ፣ ሆንዱራስ፣ ጓቲማላ እና ሜክሲኮን አቆራርጦ አሜሪካ ለመግባት ሞክሯል። ለዚህ ጉዞ ከ10 ሺህ በላይ የአሜሪካን ዶላር አውጥቷል።

በተቃራኒው “ድሃ” ስደተኞች የኬኔሪ ደሴት አቋርጠው በጀልባ ከሴኔጋል አውሮፓ ለመግባት ሲሞክሩ ለአዘዋዋሪዎች ከ450 ዶላር የበለጠ አይከፍሉም።

ፉውል ያለፈበት መንገድ እጅግ አሰቃቂ እንደነበር ይናገራል።

“ብዙ ሰዎች ፊት ለፊቴ ሞተዋል” ይላል።

“ነገር ግን ልጆቻቸውን በጀርባቸው አዝለው ጭምር ጉዟቸውን የቀጠሉ ሴቶች ሳይ ‘መጠንከር አለብኝ’ ብዬ አሰብኩ” ሲል ይናገራል።

ከዚህ ሁሉ ጉዞ በኋላ አሜሪካ ገብቶ በቁጥጥር ስር ውሎ፣ በማቆያ መዕከል እንዲገባ ተደረገ። በመጨረሻም ተለቆ በአሜሪካ ጥገኝነት ጠያቂ ሆኖ እንዲቆይ ተፈቀደለት።

ቀጥሎ ከወንድሙ ጋር የተገናኘ ሲሆን በአሜሪካ መካኒክ ሆኖ እየሠራ ይገኛል።

ፋውለን ዕደለኛ ነው። ይህ ዕድል ግን በርካታ አሜሪካ ለሚገኙ አፍሪካውያን ስደተኞች ጠባብ ነው።

ባለፈው ዓመት መስከረም ላይ ሜክሲኮን አቋርጠው አሜሪካ የገቡ 140 የሴኔጋል ስደተኞች “ተባረው” ወደ ሀገራቸው ተልከዋል።

የሰብአዊ መብት ድርጅቶች እና የዲያስፖራ ‘ኮሚኒቲ’ የሚያዘጋጇቸው መጠለያዎች እጅግ የተጨናነቁ ናቸው።

አንዳንድ ስደተኞች ጎዳናዎች ላይ ከመተኛት ያለፈ አማራጭ የላቸውም። ሌሎች ደግሞ በጊዜያዊነት መስጊዶች ውስጥ እንዲቆዩ ይፈቀድላቸዋል።

በማዕከላዊ አሜሪካ በኩል ወደ ዩኤስ አሜሪካ ለመግባት የሚሞክሩ አፍሪካውያን ቁጥር እየጨመረ ነው

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, በማዕከላዊ አሜሪካ በኩል ወደ ዩኤስ አሜሪካ ለመግባት የሚሞክሩ አፍሪካውያን ቁጥር እየጨመረ ነው

ከምዕራብ አፍሪካ አገራት የሚነሱ ስደተኞች የተለያዩ አማራጮችን ቢመለከቱም አሁንም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች በሜዲትራኒያን ባህር በኩል ወደ አውሮፓ ለመግባት ይሞክራሉ።

ባለፉት 10 ዓመታት በአንዱ የውሃ አካል ብቻ 28 ሺህ ስደተኞች ሰጥመው መሞታቸውን የመንግሥታቱ ደርጅት የስደተኞች ጉዳይ ኤጀንሲ የሆነው አይኦኤም ገልጿል።

ሴንጋላውያን ለአሳ ማጥመጃነት የሚሰራ የእንጨት ጀልባን ተጠቅመው ወደ አውሮፓ ለመሰደድ ይሞክራሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ሴንጋላውያን ለአሳ ማጥመጃነት የሚሰራ የእንጨት ጀልባን ተጠቅመው ወደ አውሮፓ ለመሰደድ ይሞክራሉ

ፖለቲካዊ ቃልኪዳኖች

የስደተኞች ጉዳይ ባለሙያው አሊ ታንዲያን በደህንነት ችግር፣ በደካማ ተቋማት፣ ከኮቪድ ቀውስ በኋላ በተከተሉ ችግሮች እና በከባቢያዊ ጉዳቶች ምክንያት በርካቶች ከምዕራብ አፍሪካ ለቀው መሄድ እንደሚፈልጉ ይገልጻል።

ለወጣቶች ሥራ ለመፍጠር ቃል የገቡ አዲስ ፕሬዝዳንት ካገኘችው እና በአንጻራዊነት ሠላማዊ ከሆነችው ሴኔጋል የሚወጡ ወጣት ስደተኞች ቁጥር እያሻቀበ ነው።

አዲሱ ፕሬዝዳንት ወደ ሥልጣን ከመጡበት ባለፈው መጋቢት ጀምሮ የመሰረታዊ ሸቀጦችን ዋጋ ቀንሰዋል። ይህም የምግብ ዘይት፣ዳቦ እና ሩዝ ዋጋን ይጨምራል። በዚህም ሳቢያ የኑሮ ውድነት በትንሹ ቀንሷል።

ያ ግን በቂ አይመስልም።

‘ሆራይዘን ዊዝአውት ቦርደርስ’ የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ተቋም ኃላፊ የሆነው ቦባካር ሴዬ “አዲስ መንግሥት ሲመጣ የነበረን ተስፋ የሚሰደደው ሰው ቁጥር እንደሚቀንስ ነበር። እንዳለመታደል ሆኖ ያ አልሆነም” ይላል።

ጨምሮም በማህበረሰብ ደረጃ ሰዎች ሀገራቸው ላይ ሠርተው እንደማይቀየሩ፣ ፍላጎታቸውን ማሟላት እንደማይችሉ እያመኑ መጥተዋል ብሏል።

ሴዬ ለሴኔጋል ባለስልጣናት በጻፈው ደብዳቤ በዶሚኒክ ሪፐብሊክ አስክሬናቸው በተገኙት ስደተኞች ላይ የተከሰተው ምን እንደነበር ለማጣራት ምርመራ እንዲደረግ ተማጽኗል።

“በዚህ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት ዙሪያ ወንጀለኞች አሉ። ወንጀለኞቹ አደንዛዥ ዕጽ፣ መሳሪያ፣ ሰዎች እና የሰዎች አካል እንደሚያዘዋውሩ” የሚያሳይ ሪፖርቶች አሉ ይላል።

ባለፈው በጀልባ ሲጓዙ የነበሩ 89 ሰዎች አደጋ ገጥሟቸው ከሞቱ እና አስክሬናቸው ከተገኘ በኋላ የሴኔጋል ጠቅላይ ሚኒስትር በይፋ በአትላንቲክ ውቅያኖስ በኩል ወደ አውሮፓ ለመሻገር እንዳይሞክሩ የአገራቸውን ወጣቶች ተማጽነዋል።

“የወደፊቷ ዓለም በአፍሪካ ላይ የተመረኮዘች ነች፤ እናም እናንተ ወጣቶች ይህንን ልትገነዘቡ ይገባል” ሲሉም ተደምጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ይበሉ እንጂ፣ በርካታ ወጣቶች ተስፋቸው በሀገራቸው ሳይሆን የትም ሊሆን እንደሚችል አምነው ወደ አውሮፓ ወይም አሜሪካ ለመሰደድ አሁንም በህይወታቸው ‘ሲቆምሩ’ ይታያሉ።