በእስራኤል ባለስልጣናት ላይ የእስር ማዘዣ በጠየቀው አይሲሲ ላይ ማዕቀብ ልትጥል እንደምትችል አሜሪካ ፍንጭ ሰጠች

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በእስራኤል ከፍተኛ ባለስልጣናት ላይ እስር ማዘዣ እንዲወጣ መጠየቁን ተከትሎ በዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) ላይ ሊጣሉ የሚችሉ ማዕቀቦችን በተመለከተ ከህግ አውጭዎች ጋር እንደሚሠሩ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን ገለጹ።

ፍርድ ቤቱ በእስራኤል ባለስልጣናቱ ላይ የእስር ማዘዣ እንዲወጣ የጠየቀው በፍልስጤማውያን ላይ ፈጸሙት ባለው በሰብዓዊነት ላይ በሚፈጸም ወንጀል እና የጦር ወንጀሎች ምክንያት ነው።

ብሊንከን ለአገሪቱ የምክር ቤቱ አባላት እንደተናገሩት "በተሳሳተው ውሳኔ" ላይ እርምጃ ለመውሰድ "ቁርጠኛ" ናቸው።

ኃላፊው አስተያየት የሰጡት በአይሲሲ ባለስልጣናት ላይ ማዕቀብ እንዲጣል የሪፐብሊካን አባለት ግፊት በሚያደርጉበት እና በዚህም ወዲያውኑ ድምጽ ሊሰጥበት ይችላል ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት ነው።

አሜሪካ የአለም አቀፉ የወንጀል ችሎት ፈራሚ አባል አይደለችም። ሆኖም አይሲሲ በዩክሬን ጦርነት ምክንያት ለሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ያወጣውን የእስር ማዘዣን ጨምሮ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ለፍርድ ቤቱ ድጋፏን ሰጥታለች።

ማክሰኞ በሴኔቱ የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ስብሰባ ላይ ሪፐብሊካኑ ጄምስ ሪሽ ፍርድ ቤቱ "ገለልተኛ፣ ህጋዊ እና ዲሞክራሲያዊ የፍትህ ስርዓት ባላቸው አገራት ውስጥ እጁን ማስገባቱን" የሚያየውን ሂደት ይደግፉ እንደሆን ብሊንከንን ጠይቀዋል።

"ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት ከእናንተ መሥራት እንፈልጋለን። ይህን ለማድረግ ቆርጬያለሁ" ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ምላሽ ሰጥተዋል።

ብሊንከን አክለውም “ይህንን የተሳሳተ ውሳኔ ለማቃናት ተገቢውን እርምጃ ለመውሰዳችን ምንም ጥያቄ የለውም" ብለዋል።

የአይሲሲ ዋና ዓቃቤ ህግ ካሪም ኻን በእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ እና የመከላከያ ሚኒስትሩ ዮአቭ ጋላንት ላይ የእስር ማዘዣ እንዲወጣ ማመልከቻ ማስገባታቸውን ሰኞ ዕለት አስታውቀዋል።

ኻን ለሦስት የሐማስ ባለስልጣናትም የእስር ማዘዣው እንዲወጣባቸው ጠይቀዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

እነዚህም በጋዛ የቡድኑ መሪ ያህያ ሲንዋር፣ የጦር ክንፉ የቃሳም ብርጌድ አዛዥ መሀመድ ዴፍ እና የፖለቲካ ቢሮው ኃላፊ ኢስማኤል ሃኒዬ ናቸው።

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በጦር ወንጀል እየተወነጀሉ ባሉት የእስራኤል ባለስልጣናት የእስር ማዘዣ እንዲወጣ መጠየቁን “አሳፋሪ” ነው ሲሉ ተናግረዋል።

በእስራኤል እና በሐማስ መካከል "እኩልነት የለም፤ አልነበረምም" ሲል አክለዋል።

የብሊንከን አስተያየት የፍርድ ቤቱ ውሳኔ በዋሽንግተን ባለስልጣናት ዘንድ በሰፊው ተቃውሞ እንደገጠመው አስተጋብቷል።

ፍርድ ቤቱ እስራኤል በጋዛ ጦርነት የወሰደችውን እርምጃ በተመለከተ ምርመራውን ባጠናከረበት ወቅት፤ በአይሲሲ ላይ ሊጣሉ የሚችሉ ቢያንስ ሁለት ማዕቀቦች ለምክር ቤቱ ቀርበዋል።

የህግ አውጪዎቹ ድጋፍ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ በቴክሳሱ ቺፕ ሮይ በተጀመረው ህግ ዙሪያ እየተሰባሰበ ይመስላል።

ይህ ጸረ ህገ-ወጥ ፍርድ ቤት የሚባለው ህግ ፍርድ ቤቱ "በአሜሪካ እና በአጋሮቿ በሚጠበቁ ሰዎች ላይ ምርመራ ካላቆመ በስተቀር" በጉዳዩ ላይ የተሳተፉ የአይሲሲ ባለስልጣናት ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ በመከልከል፣ የያዙትን ማንኛውንም የአሜሪካ ቪዛ በማገድ እና በአገሪቱ ንብረት እንዳያፈሩ የሚከላከል ነው።

በሪፐብሊካን የሚመራው ምክር ቤት ውስጥ ያሉ 37 ያህል የህግ አውጭዎች ህጉን ደግፈዋል። የሪፐብሊካኗ ኤልሲ ስቴፋኒክም ህጉን ደግፈው ቆመዋል።

ስቴፋኒክ በቅርቡ ወደ እስራኤል ባደረጉት ጉብኝት ከኔታንያሁ ጋር ተገናኝተው፣ በኬኔሴት (የአገሪቱ ፓርላማ) ንግግር አድርገው እና በጋዛ የታገቱ ሰዎችን ቤተሰቦች አነጋግረው ነበር።

ፍርድ ቤቱ "መብቷን የምታስጠበቅ ሠላማዊ አገርን የዘር ማጥፋት ወንጀል ከሚፈጽሙ አሸባሪ ቡድኖች ጋር እኩል አድርጓል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።