የመከላከያ ሚኒስትሯ በሠራዊቱ ላይ ያላቸው ሥልጣን ምን ያህል ነው?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የመሪነት ሥልጣን ላይ በቆዩባቸው ባለፉት ስድስት ዓመታት በአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር ኃላፊነት ላይ አምስት ሰዎች ለስድስት ጊዜ ተፈራርቀውበታል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ባሉት ዓመታት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችን እንደ አዲስ ከማደራጀት ባሻገር በተለያዩ ጊዜያት በካቢኔ ሚኒስትሮቻቸው ላይ ሹም ሽር አድርገዋል። የመከላከያ ሚኒስቴር ደግሞ በዚህ ሂደት ተደጋጋሚ ለውጦችን አስተናግዷል።
በስድስት ዓመታት ውስጥ ስድስት ጊዜ ሚኒስትሮች የተሾሙለት የመከላከያ ሚኒስቴር በአማካይ በየዓመቱ አንድ ሚኒስትር በኃላፊነት ቆይቷል። በዚህም ሳቢያ ሚኒስትሮቹ ከስድስት ወራት እስከ አንድ ዓመት ተኩል ለሚጠጋ ጊዜ በቦታቸው ቆይተዋል።
በስድስት ዓመቱ ውስጥ ስድስት ጊዜ የመከላከያ ሚኒስትርነት ሹመት የተሰጠ ሲሆን፣ ከቀናት በፊት በጠቅላይ ሚኒስትሩ ሹመታቸው ይፋ የሆነው አይሻ መሐመድ ደግሞ ለሁለተኛ ጊዜ ወደ መከላከያ ሚኒስትርነት ተመልሰዋል። አይሻ በአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስቴር ታሪክ የመጀመሪያዋ ሴት ሚኒስትር ናቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የመጀመሪያ ካቢኔያቸውን ሲያዋቅሩ አቶ ሞቱማ መቃሳን የሾሙ ሲሆን፣ ከዚያም አይሻ መሐመድ፣ አቶ ለማ መገርሳ፣ ዶ/ር ቀነዓ ያደታ፣ ዶ/ር አብርሃም በላይ፤ አሁን ደግሞ አይሻ መሐመድ የሚኒስትርነት ቦታውን ተረክበዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም በአገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት አመራር ላይ ከፍተኛ ሥልጣን እንዳላቸው በሕገ መንግሥቱ እና በሠራዊቱ አዋጅ ላይ ሰፍሯል።
ለመሆኑ መከላከያ ሠራዊትን በመምራት ረገድ የእነዚህ ሦስት አካላት ሥልጣንና ኃላፊነት ምን ምንድን ነው?
ጠቅላይ ሚኒስትሩ
በምድር፣ በአየር፣ በባሕር እና በሳይበር ክፍሎች መደራጀቱ የሚነገርለት የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት የመከላከያ ሠራዊት በአገር መከላከያ ሚኒስቴር ሥር የተዋቀረ ሲሆን፣ በተለያዩ ደረጃዎች ሠራዊቱን የሚመሩ ባለሥልጣናት አሉት።
የመከላከያ ሚኒስቴርን እና በውስጡ ያሉትን ኃይሎች እና ተቋማትን የዕለት ከዕለት ሥራ በመምራት እና በማስተዳደር በኩል ሚኒስትሯ/ሩ ዋነኛ ሚና ቢኖረውም በወሳኝ የሠራዊቱ እንቅስቃሴ እና ተግባራት ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ እና የኤታማዦር ሹሙ ሚና ጉልህ ነው።
በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 74 ላይ እንደ ሰፈረው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካሏቸው ሥልጣን እና ኃላፊነቶች መካከል አንዱ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ በመሆን የአገሪቱን ሠራዊት በበላይነት ማዘዝ ነው።
የመከላከያ ሚኒስትር
በ2015 ዓ.ም. በወጣው የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የመከላከያ ሠራዊት አዋጅ የአገሪቱ ካቢኔ አባል የሚሆኑት የመከላከያ ሚኒስትር የሚኖራቸውን ሥልጣን እና ተግባራት በዝርዝር አስቀምጧል።
በዚህም መሠረት ሚኒስትሯ/ሩ መከላከያን በተመለከተ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ሊመከርባቸው እና ሊወሰኑ የሚገባቸውን ጉዳዮች በማቅረብ ያስወስናሉ፣ ሠራዊቱ የሚተዳደርባቸውን ሕጐች፣ ፖሊሲዎች እና ስትራተጂዎችን ያዘጋጃሉ፣ ሲጸድቁም በተግባር ላይ መዋላቸውን ያረጋግጣሉ።
በተጨማሪም የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱን በጀትን በማቅረብ ያስፈቅዳሉ በተግባር መዋሉን ይቆጣጠራሉ፤ የሚኒስቴሩን የልማት ድርጅቶች እና የመከላከያ ሠራዊት ፋውንዴሽንን ይቆጣጠራሉ፤ ከውጭ መንግሥታት እና መንግሥታዊ እንዲሁም መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ግንኙነት ያደርጋሉ።
ወታደራዊ ዘመቻን በተመለከተም “በመንግሥት ውሳኔ መሠረት አገር አቀፍ የክተት ዘመቻዎችን” እንደሚያስተባብር የሚኒስቴሯ/ሩ ኃላፊነት ውስጥ ከተጠቀሱት ኃላፊነቶች እና ሥልጣኖች የሚጠቀሱ ናቸው።
በዚህም አብዛኛው የመከላከያ ሚኒስትር ሥልጣን እና ኃላፊነት በተቋሙ ውስጥ ያሉ አስተዳደራዊ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ናቸው ማለት ይቻላል።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም
በአገሪቱ ወታደራዊ ተቋማት ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን ካላቸው ግለሰቦች መካከል የጦር ኃይሎች ኤታማዦር ሹሙ አንዱ ናቸው። በአሁኑ ውቅት በዚህ የኃላፊነት ቦታ ላይ የሚገኙት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ናቸው።
በመከላከያ ሠራዊት አዋጅ መሠረት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹሙ ሥልጣን አና ኃላፊነት ጠቅላይ ሚኒስትሩን እና የመከላከያ ሚኒስትሩን በወታደራዊ ጉዳዮች ላይ ያማክራል፣ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ትዕዛዝ መሠረት ሠራዊቱን ያሰማራል፤ ያዋጋል።
በተጨማሪም ከክልሎች አቅም በላይ የሆነ የፀጥታ ችግር ሲያጋጥም ኃላፊነት ሲሰጠው እንዲሰማራ ያደርጋል፣ በአገሪቱ ውስጥ የሚደነገጉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ያስፈጽማል።
ስለዚህም በአፍሪካ ውስጥ ቀዳሚ ከሆኑ ጦር ኃይሎች መካከል አንዱ የሆነውን የኢትዮጵያን የመከላከያ ሠራዊት ከመምራት አንጻር በወታደራዊ ጉዳዮች ዋነኛው ሥልጣን ያለው የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ በሆኑት በጠቅላይ ሚኒስትሩ እጅ ሥር ሲሆን፣ በተከታይነት ደግሞ ሥልጣኑ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦሩ ነው።
ቢሆንም ግን የመከላከያ ሚኒስትር አጠቃላይ የሠራዊቱን የዕለት ከዕለት እንቅስቃሴ እና አስተዳደራዊ ጉዳዮችን ከመምራታቸው ባሻገር ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በሚኒስትሮች ምክር ቤት፣ ከኤታማዦር ሹሙ ጋር ደግሞ በመደበኛ ሥራ የቀረበ ግንኙነት አላቸው።












