በቀይ ባሕር የጦር ሰፈር ለማቋቋም የተቃረበችው ሩሲያ ለቀጣናው ምን ይዛ ትመጣለች?

የፎቶው ባለመብት, EPA
በዓለም ላይ ወሳኝ ከሆኑ የባሕር መተላለፊያ መስመሮች መካከል አንዱ በሆነው ቀይ ባሕር ላይ ከቅርብም ከሩቅም ያሉ አገራት ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ እግራቸውን ለማስገባት እየጣሩ ነው።
ጥቂት የማይባሉ አገራት ከአሜሪካ፣ ከአውሮፓ እና ከሩቅ ምሥራቅ ሳይቀሩ በጂቡቲ ላይ ወታደራዊ ሰፈር መሥርተው በአካበቢው ላይ ሲንቀሳቀሱ ሌሎች ደግሞ የባሕር ኃይላቸውን በአካባቢው አሰማርተው ለጥቅማቸው ዘብ ቆመዋል።
የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ ዩሱፍ ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ እንዳስታወቁት፤ የሱዳን ጦር የሚመራው መንግሥት ከሩሲያ ጋር የቀይ ባሕር ወታደራዊ ሰፈር ግንባታን በተመለከተ የመጨረሻ ስምምነት ላይ ደርሷል።
የየመን ሁቲ ታጣቂዎች ባለፉት ሁለት ዓመታት በቀይ ባሕር የንግድ መርከቦች እንቅስቃሴ ላይ ያሳደሩት ተጽእኖ ምዕራባውያን በአካባቢው ያላቸውን ሚና የበለጠ እንዲያጠናክሩ ሲያደርግ፣ ሌሎች አገራት ደግሞ በቀይ ባሕር ዙሪያ ቦታ ለማግኘት እየሠሩ ነው።
ከእነዚህ መካከልም ሩሲያ ዋነኛዋ አገር ናት። ሩሲያ በአንጻራዊነት ከምዕራባውያኑ በተሻለ ለቀይ ባሕር የቀረበች ብትሆንም በአካባቢ ወታደራዊ ሰፈር የላትም።
ባለፉት ዓመታት የቀይ ባሕር ተዋሳኝ ከሆኑት አገራት ጋር ስትወያይ እና ትብብሮችን ስትፈጽም የቆየችው ሩሲያ ተስፋ ሳትቆርጥ ፍላጎቷን እውን ለማድረግ የተቃረበች ትመስላለች።
ቀይ ባሕር አፍሪካን፣ እስያን እና አውሮፓን በአቋራጭ የሚያገናኝ ወሳኝ ባሕር የንግድ እንቅስቃሴ መስመር ሲሆን፣ በዚህ መተላለፊያ ላይ የሚከሰት ዕክል ታላላቅ የምጣኔ ሀብት እንቅስቃሴዎች ላይ ከባድ ተጽእኖ አለው።
የዓለምችን ከፍተኛ መጠን ነዳጅ፣ ተፈላጊ ማዕድናት እና የኢንዱስትሪ ምርቶች በተለይ ከባሕረ ሰላጤው እና እስያ ወደ አውሮፓ የሚተላለፍበት መሆኑ አገራት ዐይናቸውን እንዲጥሉበት አድርጓል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
እየመጣች ያለችው ሩሲያ
በምጣኔ ሀብትም ሆነ በወታደራዊ አቅሟ ከዓለማችን ኃያላን ተርታ የምትመደበው ሩሲያ በቀይ ባሕር ላይ ሚና እንዲኖራት ለማድረግ ዓመታትን ወስዶባታል።
በዚህም በቀይ ባሕር ላይ ወታደራዊ ሰፈር ለመገንባት ከአውሮፓውያኑ 2017 ጀምሮ እንቅስቃሴ ስታደርግ ቆይታለች።
አሁን ግን በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ከምትገኘው ሱዳን ጋር ከስምምነት ላይ እንደደረሰች የሚያመለክቱ ሪፖርቶች እየወጡ ነው።
ሱዳን ሦስት ዓመት ሊሞላው በተቃረበ ጦርነት ውስጥ ሆና ከባድ ውድመት ደርሶባታል። በጄነራል አል ቡርሐን የሚመራው የአገሪቱ ጦር ሠራዊት፣ ከጄነራል ሐምዳን ዳጋሎ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ጋር እየተፋለመ ነው።
በዚህ ጊዜ ደግሞ መቀመጫውን ፖርት ሱዳን ላይ አድርጎ የቀይ ባሕር ዳርቻ የሆነውን የሱዳንን ግዛት የሚቆጣጠረው የጄነራል አል ቡርሐን ቡድን ከሩሲያ ጋር በመቀራረብ ድጋፍ ለማግኘት እና ለሩሲያም የምትፈልገውን ለመስጠት በሩን ከፍቷል።
ባለፈው ዓመት የካቲት የቀድሞው የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እንዳስታወቁት በሁለቱ አገራት በኩል ሩሲያ በሱዳን የባሕር ዳርቻ ላይ የሚኖራትን "የባሕር ኃይል ሰፈር በተመለከተ በሚደረሰው ስምምነት ላይ መግባባት ላይ መደረሱን" በመግለጽ ይህንንም ተግባራዊ ለማድረግ "ምንም ዓይነት እንቅፋት የለም" ብለው ነበር።
በሞስኮ በኩልም በሱዳን ውስጥ በተለይም ከጦርነት በኋላ በሚኖረው የመልሶ ግንባታ በአገሪቱ ውስጥ መዋዕለ ነዋይዋን ለማፍሰስ ዝግጁ መሆኗን አሳውቃለች።
በከባድ ጦርነት ውስጥ የሚገኙት አል ቡርሐን በአሸናፊነት ለመውጣት የሚያስችላቸውን ድጋፍ ለማግኘት ለሩሲያ የባሕር ኃይል ሰፈር በቀይ ባሕር ዳርቻ ላይ ለመስጠት መዘጋጀታቸውን የሚያመለክቱ መረጃዎች እየወጡ ነው።
ሱዳን ለሩሲያ የባሕር ኃይል ጦር ሰፈር ለመፍቀድ የተነሳችው በምላሹ ዘመናዊ የጦር መሣሪያዎችን ከሞስኮ ለማግኘት መሆኑም ተዘግቧል።
'ዋል ስትሪት ጆርናል' በቅርቡ ባወጣው ዘገባ፤ የሱዳን ጦር በቀይ ባሕር ላይ ለሩሲያ የጦር ሰፈር ይሁንታ የሰጠው በምላሹ ከሩሲያ የጦር መሣሪያ ለማግኘት በተደረሰው ስምምነት መሆኑን ጠቅሷል።
ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት ይህ የሩሲያ ባሕር ኃይል ሰፈሩ ወደ 300 ወታደሮችን የሚይዝ ሲሆን፤ የሱዳን መንግሥት እና የክሬምሊን ስምምነት ለ25 ዓመታት የሚዘልቅ ይሆናል።
ሱዳን ትሪቢዩን እንደዘገበው ከሆነ የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ ዩሱፍ "ሱዳን እና ሩሲያ፤ የሩሲያን የጦር ሰፈር በተመለከተ ስምምነት ላይ ደርሰዋል" ብለዋል።
"ሙሉ ስምምነት ላይ ደርሰናል። ጉዳዩ ቀላል ነው። ምንም መሰናክል የለም" ማለታቸውም ተዘግቧል።
ከሳምንታት በፊት በሞከኮ ይፋዊ ጉብኝት ያደረጉት የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር፤ ከሩሲያው አቻቸው ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር በመሆን በሞስኮ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተው ነበር።
የሱዳን መንግሥት ዜና ወኪል የሆነው ሱና እንደዘገበው፤ የሱዳን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስለ ጉዳዩ መግለጫ ቢያወጣም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን ንግግር አላጣቀሰም።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ መግለጫ የሁለትዮሽ ግንኙነትን በተመለከተ የተለያዩ ነጥቦችን አንስቷል።
ሁለቱ አገራት "ስትራቴጂካዊ ግንኙነታቸውን ለማሳደግ" ያላቸውን ቁርጠኝነት ጠቅሰዋል።
የሱና ዘገባ እንደሚያመለክተው፤ የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ የሁለቱን አገራት ግንኙነት አወድሰው "ሩሲያ ሱዳንን በዓለም አቀፍ መድረኮች ትደግፋለች" ብለዋል።
ሩሲያ ከአውሮፓውያኑ 2017 ጀምሮ ወታደራዊ ሰፈር ለመገንባት ሙከራ ስታደርግ የቆየች ሲሆን፤ ሁለቱ አገራት የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነት ላይ የደረሱት ግን 2020 ነው።
ሆኖም ግን በምዕራባውያን አገራት ጫና ምክንያት የሱዳን ባለሥልጣናት በስምምነቱ ወደፊት ለመግፋት ፍላጎት ሳያሳዩ ቆይተዋል።

የፎቶው ባለመብት, Suna
የጦር ሰፈር በጦር መሣሪያ
ሩሲያ በምትገነባው የባሕር ኃይል ጦር ሰፈር ላይ አንድ ጊዜ አራት የጦር መርከቦችን ማስፈር የምትችል ሲሆን፣ ይህም በኒውክሌር ኃይል የሚንቀሳቀስ የጦር መርከብን የሚያካትት ነው።
የሱዳን መንግሥት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከሩሲያ እና ከኢራን ጋር እየተቀራረበ ነው። ከሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) ጋር ጦርነት ውስጥ የገባው የሱዳን ጦር ድጋፍ በመፈለግ ከሁለቱ አገራት ጋር ያለውን ግንኙነት አጠናክሯል።
ባለፈው ዓመት ጥር ላይ ነዳጅ ከማውጣት እንዲሁም ከማጓጓዝ እና ከውጭ ንግድ ጋር በተያያዘ ሱዳን ከሩሲያ ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርማለች።
ዋል ስትሪት ጆርናት ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው የሱዳን ባለሥልጣናትን ጠቅሶ እንደዘገበው ሱዳን ሩሲያ በግዛቷ ውስጥ የባሕር ኃይል የጦር ሰፈር እንድታቋቁም ይሁንታን የሰጠችው በዚህ ዓመት ጥቅምት ላይ ነው።
ከጦር ሰፈር ግንባታው በተጨማሪ ሩሲያ በሱዳን ውስጥ የነዳጅ ቁፋሮ እንድታደርግ የሚያስችል ስምምነትም ተካቷል።
ሩሲያ በምላሹ በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የድሮን ጥቃቶች እየተፈተነ ላለው የሱዳን ጦር ሠራዊት ዘመናዊ የአየር መቃወሚያ ሥርዓት እንዲሁም ሌሎች የጦር መሣሪያዎችን ታቀርባለች።
'ኢንዲፔንደር ሚሊተሪ ዋች' የተባለው መጽሔት ባለፈው ኅዳር ወር መጨረሻ ላይ ባወጣው ዘገባ፤ የሱዳን መከላከያ ሚኒስቴር ሱ-30 እና ሱ-35 የተባሉ ሩሲያ ሠራሽ ተዋጊ ጀቶችን ለማግኘት ንግግር እያደረገ ይገኛል።
ተዋጊ ጀቶቹ ለሱዳን የሚሰጡት "ቀይ ባሕር ላይ በሚገነባቸው የባሕር ኃይል ጦር ሰፈር ምላሽ" ነው ሲልም መጽሔቱ አትቷል።
በእርግጥ ይህ የሁለቱ ወገኖች ንግግር እና ስምምነት ወደ ተግባር የሚሸጋገር ከሆነ በፖርት ሱዳን ላይ የሚቋቋመው የሩሲያ የባሕር ኃይል ሰፈር በአፍሪካ የመጀመሪያው ይሆናል።
ይህ በሱዳን መንግሥት እና በሩሲያ መካከል የባሕር ኃይል ጦር ሰፈር በቀይ ባሕር ዳርቻ ለማቋቋም የተደረሰው ስምምነት አንድ ተጨማሪ ኃያል አገርን ወደ ቀጣናው የሚያመጣ ነው።
ነገር ግን ከቀይ ባሕር ተጎራባች አገራትም ሆነ ከምዕራባውያን በኩል በአሉታዊም ሆነ በአውንታዊ መልኩ የተሰማ ነገር የለም።
ባለፉት ወራት ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በኩል በተሰነዘረበት ከባድ ጥቃት ቁልፍ ይዞታዎቹን ያጣው የሱዳን ጦር የበላይነት ለማግኘት እና የተነጠቃቸውን ግዛቶች መልሶ ለመያዝ ከሩሲያ ለሚያገኘው ወደታራዊ ድጋፍ ሲል የሚጠየቀውን ሊፈጽም ይችላል።
በሱዳን እየተካሄደ ባለው የእርስ በርስ ጦርነት ሳቢያ ከ150 ሺህ በላይ ሰዎች ሲገደሉ፤ ከ12 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ረሃብ መስፋፋቱም ተገልጿል።
የሱዳን ጦርነት ከሁለት ዓመት ተኩል በኋላም ተባብሶ የቀጠለ ሲሆን፤ ጦርነቱ እንዲራዘም ምክንያት ከሆኑ መካከል የውጭ አገራት ጣልቃ ገብነት ይጠቀሳል።
የሱዳን ጦርን ይደግፋሉ ተብለው የሚታመኑ አገራት ግብፅ፣ ቱርክ፣ ኢራን፣ ሩሲያ እና ኤርትራ ናቸው። አገራቱ ለወታደራዊው መንግሥት ቀጥተኛ ወታደራዊ ድጋፍ እንደሚሰጡ ይታመናል።
በሌላ በኩል፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መሣሪያ፣ የሕክምና ቁሳቁስ እና ሌሎችም ድጋፎችን ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በመስጠት ስትከሰስ እሷ ግን በተደጋጋሚ ታስተባብላለች።
የሳዑዲን ልዑል አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማን በዋይት ሐውስ ባደረጉት ቆይታ በሱዳን እየሆነ ስላለው ለትራምፕ አስረድተው፤ ጣልቃ እንዲገቡም ጠይቀዋል።
ትራምፕም "ሱዳንን በተመለከተ እንቅስቃሴ እንጀምራለን" ብለዋል።
ላለፉት ስድስት ወራት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ማርኮ ሩቢዮ እና የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ማሱድ ቦሉስ ዕቅድ ሲያረቅቁ ቆይተዋል።
አሜሪካ፣ ግብፅ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ያሉበት "ኳድ" የተባለ ጥምረት ጦርነቱን ለማስቆም እየጣረ ነው።
የተኩስ አቁም ላይ መድረስ፣ ሰብአዊ እርዳታ ለማስገባት እና በሲቪሎች የሚመራ መንግሥት ማቋቋም ዋነኛ ግቦቻቸው ናቸው።















