ትራምፕ የሱዳንን የእርስ በርስ ጦርነት ማስቆም ይችላሉ?

የሱዳን የእርስ በእርስ ጦርነት

የፎቶው ባለመብት, Reuters

    • ፀሐፊ, አሌክስ ደ ዋል

ሱዳን በሁለት ዓመታት የእርስ በእርስ ጦርነት እየታመሰች ነው። እስካሁን የተደረጉ የሰላም ጥረቶች ውጤታማ አልሆኑም። ተዋጊዎቹ ወደ ድርድር ጠረጴዛ እንዲመጡም አላስቻሉም።

የአሜሪካ ቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት የሱዳንን ጦርነት ማስቆም ይችላል?

የፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር የሱዳን ጦርነት "እሳቸው የሚሳተፉበት አይደለም" ሲል፤ ትራምፕም "ከቁጥጥር ውጭ እንደሆነ ነው የማስበው" ብለዋል።

ትራምፕ፤ ይህን ያሉት የሳዑዲውን ልዑል አልጋ ወራሽ መሐመድ ቢን ሳልማን ወደ ዋይት ሀውስ ከመጋበዛቸው በፊት ነው።

ልዑል አልጋ ወራሹ በሱዳን እየሆነ ስላለው ለትራምፕ ተናግረዋል። ጣልቃ እንዲገቡም ጠይቀዋል።

ትራምፕም "ሱዳንን በተመለከተ እንቅስቃሴ እንጀምራለን" ብለዋል።

ከዚያም በማኅበራዊ ሚዲያቸው "ሱዳን ከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ናት። በምድር ላይ ከፍተኛ ነውጥ ያለበት ቦታ ሆናለች" ሲሉ ጽፈዋል።

ከግብፅ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር አብረው ለመሥራትም ቃል ገብተዋል።

አሜሪካ ከዚህ ቀደም ሰላም ለማውረድ በተደረጉ ጥረቶች ተሳትፋለች። ትራምፕ ከሦስቱ አገራት መሪዎች ጋር ካላቸው ቅርበት አንጻር በተሻለ ሁኔታ ተጽዕኖ መፍጠር ይችሉ ይሆናል።

ሦስቱም አገራት በሱዳን ጦርነት ውስጥ እጃቸው እንዳለበት ይገለጻል።

መሐመድ ቢን ሳልማን እና ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በጦርነቱ ምክንያት 12 ሚሊዮን ሱዳናውያን ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል። በአገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎች ረሃብ መስፋፋቱም ተገልጿል።

ሱዳናውያን ከገቡበት ማጥ የሚያወጣቸው ማንኛውንም አማራጭ ሊወስዱ ይችላሉ።

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) ከ500 ቀናት ከበባ በኋላ ኤል-ፋሸርን መያዙ ከተሰማ በኋላ ነው ትራምፕ ጣልቃ ለመግባት የወሰኑት።

የአርኤስኤፍ ወታደሮች በኤል-ፋሸር ሰዎችን በመግደል፣ በመድፈር እና ዝርፊያ በመፈጸም ተከሰዋል።

ጎሳ ተኮር በሆነው የወታደሮቹ ጥቃት የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ወደ 5,000 እንደሚጠጋ ተገልጿል።

ወታደሮች ግድያ እና ስቅይት ሲፈጽሙ የሚያሳይ ቪድዮ ይቀርጻሉ። "የድል ቪድዮ" በሚልም በማኅበራዊ ሚዲያ ይለቋቸዋል።

ኤል-ፋሸር በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ሥር ከገባች በኋላ መሪው መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሔሜቲ) የተኩስ አቁም ለማድረግ ዝግጁ መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የጅምላ ግድያ በመፈጸም የጠፋውን የወታደሮቻቸውን ስም ለማጽዳት ያሰቡም ይመስላል።

የሱዳን ጦር አመራሮች ግን በጦር ሜዳ በደረሰባቸው ሽንፈት ምክንያት ወደ ድርድር ጠረጴዛው ለመምጣት አልፈቀዱም።

የጦሩ መሪ ጄነራል አብደል ፋታሕ አል-ቡርሐን የተኩስ አቁም እንደማይቀበሉ አስታውቀዋል። የተባበሩት መንግሥታት ዕውቅና የሚሰጠው ለአል-ቡርሐን መንግሥት ነው።

ሔሜቲ አቋማቸውን በማለሳለስ በይፋ ለተኩስ አቁም ዝግጁ መሆናቸውን ቢገልጹም የሱዳን ጦር ግን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አሸባሪ ነው ብሎ በመፈረጅ ውጊያውን ቀጥሏል።

ሔሜቲ በአደባባይ ስለ ተኩስ አቁም ቢያወሩም ወታደሮቻቸው ግን አሰቃቂ ጥቃት በመፈጸም ይከሰሳሉ።

የሱዳን ጦር አመራሮች የደረሰባቸውን ሽንፈት ለመበቀል እና ያጡትን ይዞታ መልሰው በቁጥጥራቸው ሥር ለማዋል ዝተዋል።

ባለፉት 40 ዓመታት በደቡብ ሱዳን፣ ዳርፉር እና ሌሎችም አካባቢዎች በነበረው ውጊያ የሱዳን አመራሮች ለአሸማጋዮች ቅድመ ሁኔታ ያስቀምጣሉ።

አሁን አገሪቱ በተለያየ ግዛት ተከፋፍላ በሁለቱ ተዋጊዎች አመራር ሥር ገብታለች። ትራምፕ ይሄንን ችግር ለመቅረፍ ቆርጠው ተነስተዋል።

ቀጣናዊ አገራት ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እና ለሱዳን ጦር ድጋፍ ይሰጣሉ።

ግብፅ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና ቱርክ የሱዳን ጦርን በመሣሪያ ይደግፋሉ። የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን እንደምትደግፍ የምርመራ ዘገባዎች እና የደኅንነት ሪፖርቶች ቢወጡም አስተባብላለች።

ሔሜቲ እና አል ቡርሐን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ሰላም እንዲመጣ የመጀመሪያው እርምጃ መሆን ያለበት ቀጣናዊ አገራት ለተዋጊዎች ድጋፍ እንዳይሰጡ ማድረግ ነው።

ላለፉት ስድስት ወራት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ማርኮ ሩብዮ እና የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች አማካሪ ማሱድ ቦሉስ ዕቅድ ሲያረቁ ቆይተዋል።

አሜሪካ፣ ግብፅ፣ ሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ያሉበት "Quad" የተባለ ጥምረት ተፈጥሯል።

የተኩስ አቁም ላይ መድረስ፣ ሰብአዊ እርዳታ ማስገባት እና በሲቪሎች የሚመራ መንግሥት ማቋቋም ዋነኛ ግቦቻቸው ናቸው።

ጥምረቱ ባለፈው ወር በዋሽንግተን ተገናኝቷል። ሆኖም ግን በተዋጊዎቹ መካከል ያለውን ልዩነት ማጥበብ አልቻሉም።

መሐመድ ቢን ሳልማን ትራምፕ የሱዳንን ጦርነት እንዲያስቆሙ መጠየቃቸው ጥምረቱ የሚኖረውን ሚና ከፍ ያደርጋል።

የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ፕሬዝዳንት ሼኽ መሐመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን አቋማቸውን እንዲለውጡ ማድረግ የሚችሉት ትራምፕ ናቸው።

ሳዑዲ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፤ ሱዳን፣ የመን እና ሶርያን ጨምሮ በመላው የአረብ አገራት የበላይነት ለማግኘት ፉክክር ውስጥ መሆናቸው መሰናክል ሊሆን ይችላል።

ሁለቱ አገራት 'ሙስሊም ብራዘርሁድ' ላይ ያላቸው አቋምም የተለያየ ነው።

የአል-ቡርሐን ጦር ኢስላሚስቶቸን የሚያካትት ሲሆን ከኦማር አል-በሽር ዘመን አንስቶ ከፍተኛ ሃብት እና አቅም ያላቸው ናቸው። ስለዚህም የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ወደ ሱዳን ጦር ሊያዘነብል ይችላል።

ትራምፕ ሳዑዲ እና የተባበሩት አረብ አሜሬቶች ለሱዳን ጉዳይ ቅድሚያ እንዲሰጡ ማሳመንም ይጠበቅባቸዋል።

ሁለቱ አገራት ቅድሚያ የሚሰጡት ለጋዛ እና ሶርያ ነው።

መሐመድ ቢን ሳልማን ለትራምፕ ካቀረቡት ጥያቄ በዘለለ የሱዳን ጦርነት እንዲቆም ድጋፍ ስለመስጠታቸው ግልጽ አይደለም።

አል-ቡርሐን ልዑል አልጋ ወራሹ ለትራምፕ ያቀረቡትን ጥያቄ ሲሰሙ፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶችን ገሸሽ የሚያደርግ እንደሆነ በማመን ሐሳቡን በአወንታዊ መንገድ የተቀበሉት ይመስላል።

ሳዑዲ የአሸማጋይነት ሚናዋ የጎላ እንዲሆን ይሻሉ።

ትራምፕ ስኬታማ ለመሆን የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ድጋፍ እንዳትሰጥ ማሳመን አለባቸው።

ሆኖም ግን የአብርሃም አኮርድስ ዋነኛ ማጠንጠኛ አገር መሆኗ አጣብቂኝ ውስጥ ይከታቸዋል።

አሜሪካ አሁን ላይ የዲፕሎማሲ ጫና ማሳደርን አማራጭ አድርጋለች። ሱዳናውያን የሰላም ጭላንጭል ለማየት ተስፋ ሰንቀዋል።

ለሰላም የተቋቋመው የአገራት ጥምረት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እንዲደረስ ቢያደርግም እንኳ ብዙ ሥራ ይጠብቀዋል።

ሰብአዊ እርዳታ ለማዳረስ የሚያስፈልገውን 3 ቢሊዮን ዶላር ማግኘት ቀላል አይሆንም። ያለ ሰብአዊ እርዳታ ደግሞ የተኩስ አቁም ጸንቶ አይቆይም።

ሱዳናውያን ተማረዋል። የጦር ጀነራሎላቸውን ማመንም አቁመዋል። አል-በሽርን ከሥልጣን ያወረደው ሕዝብ ፍትሕ እንዲሰፍን ይጠይቃል።

የአረብ አገራት ሰላም ካሰፈኑ ሱዳን እስከወዲያኛው ድረስ ጥገኛ ሆና እንደምትቀጥልም ይሰጋሉ።

* አሌክስ ደ ዋል የወርልድ ፒስ ፋውንዴሽን ዳይሬክተር ናቸው። በአሜሪካ፣ ተርፍስ ዩኒቨርስ በሕግ እና ዲፕሎማሲ ትምህርት ክፍል ያስተምራሉ።