በሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ እጃቸው ያለበት የውጭ አገራት የትኞቹ ናቸው?

የፎቶው ባለመብት, Sudan Tribune website
የሱዳን የእርስ በርስ ጦርነት ከሁለት ዓመት ተኩል በኋላም ተባብሶ እንደቀጠለ ነው። ጦርነቱ እንዲራዘም ምክንያት ከሆኑ መካከል የውጭ አገራት ጣልቃ ገብነት ይጠቀሳል።
ለጦርነቱ መቀጠል አስተዋጽኦ ያደረጉ ለሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች የፖለቲካ እና ወታደራዊ ድጋፍ የሚያደርጉ አገራት አሉ።
በጦርነቱ ሳቢያ ከ150,000 በላይ ሰዎች ሲገደሉ፤ ከ12 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።
ዓለም አቀፍ የመሣሪያ ማዕቀብ ቢጣልም የሱዳን ጦር እና የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) አሁንም ድረስ የጦር መሣሪያ እያገኙ ነው።
ከቀጣናው አገራት በሱዳን ጦርነት እጃቸውን ያስገቡ መኖራቸው ነገሮች የበለጠ እንዲካረሩ ምክንያት ሆኗል። ጦርነቱ ወደ አፍሪካ ቀንድ የሚዛመት ዳፋ እንዳያመጣም ይሰጋል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ኤል-ፋሸር ከተማን መቆጣጠሩ የጦርነቱን አቅጣጫ ለውጧል። በከተማዋ ጭፍጨፋ ፈጽሟል በሚል ወታደሮቹ ተከሰዋል።
የሱዳንን ጦር የሚደግፉ እነማን ናቸው?
የሱዳን ጦርን ይደግፋሉ ተብለው የሚታመኑ አገራት ግብፅ፣ ቱርክ፣ ኢራን፣ ሩሲያ እና ኤርትራ ናቸው። አገራቱ አገራት ለወታደራዊው መንግሥት ቀጥተኛ ወታደራዊ ድጋፍ እንደሚሰጡ ይታመናል።
የሱዳን ጦር መሪ ጄነራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሐን ጦርነቱ እንደተነሳ ወደ ግብፅ አቅንተዋል። ግብፅ ጦሩን እንደምትደግፍ የሚጠቁሙ የተለያዩ ሪፖርቶች ወጥተዋል።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሪ ጄነራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ (ሔሜቲ) ግብፅ ለሱዳን የጦር መሣሪያዎች እና የጦር አውሮፕላን ጭምር እንደምትሰጥ ገልጸዋል።
ባለንበት ኅዳር ወር ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በዳርፉር ጥቃት ሲፈጽም ዒላማ ያደረገው "የውጭ ኃይሎች መቀመጫን" እንደሆነ አስታውቋል።
በግብፅ "ይዞታ ሥር ባሉ አካባቢዎች" በሰው አልባ አውሮፕላን ጥቃት መፈጸሙን ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ቅርብ የሆኑ መገናኛ ብዙኃን ገልጸዋል።
ግብፅ በሱዳን ጦርነት ጣልቃ እንዳልገባች በተደጋጋሚ ገልጻለች። ቱርክ በሁለቱም ተዋጊዎች ጎን እንዳልሆነች አስታውቃለች።
ሆኖም ግን የሱዳን ጦር ካርቱምን ጨምሮ ዋነኛ የሱዳን ከተሞችን ከፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እንዲያስለቅቅ እገዛ ያደረጉ ሰው አልባ አውሮፕላኖች ማቅረቧን የሚጠቁሙ ሪፖርቶች ወጥተዋል።
በአውሮፓውያኑ 2025 አጋማሽ የቱርክ ሚዲያ እንደዘገበው ሰው አልባ የጦር አውሮፕላኖችን አንካራ ለሱዳን ጦር በመስጠት ካርቱምን እንዲቆጣጠር አግዛለች። ተጨማሪ ድጋፍ ለሱዳን ጦር እንዲሰጥ ጥሪ ያቀረቡ የቱርክ መገናኛ ብዙኃንም ነበሩ።
ዋሽንግተን ፖስት አምና ባወጣው ዘገባ የቱርክ ግዙፉ የጦር መሣሪያ አምራች ባይራክታር ሰው አልባ አውሮፕላንን ጨምሮ ሌሎች የጦር መሣሪያዎችንም መስጠቷን ጠቁሟል።
'ሚድል ኢስት አይ' በኅዳር ወር ባወጣው ዘገባ እንዳመለከተው ኤል-ፋሸርን የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ከተቆጣጠረ በኋላ ግብፅ እና ቱርክ ለሱዳን ጦር የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናረው ቀጥለዋል።
የሱዳን ጦር ከሩሲያ እና ከኢራን ተዋጊ ጀቶች እና ሰው አልባ አውሮፕላኖች ማግኘቱን የሚጠቁሙ ሪፖርቶችም ወጥተዋል።
በ2023 የኢራን እና የሱዳን ግንኙነት መታደሱን ተከትሎ ኢራን ለሱዳን ጦር ድጋፍ እያደረገች ነው ሲሉ በጥቅምት 2024 ሔሜቲ ክስ አቅርበዋል።
ብሉምበርግ በ2024 ባወጣው ዘገባ ኢራን እና ሩሲያ በቀይ ባሕር "ወታደራዊ የጦር ሰፈር ለመገንባት" ከሱዳን ጦር ጋር እየተነጋገሩ ነው ብሏል።
ኢራን ይሄንን ብታስተባብልም ሩሲያ ግን የጦር ሰፈር ለመገንባት በ2025 ከሱዳን ጦር ጋር ስምምነት ተፈራርማለች።
ሩሲያ በሱዳን ወታደራዊ ሰፈር ለመገንባት ከአውሮፓውያኑ 2017 አንስቶ ስታቅድ ነበር።
ኤርትራ ለሱዳን ጦር ያላትን ድጋፍ በምሥጢር አልያዘችም። ጥር 2025 ላይ የሱዳን ሚሊሻ ከኤርትራ የጦር መሣሪያ እና የወታደሮች ሥልጠና ማግኘቱን አስታውቋል።
ሳዑዲ አረቢያም የሱዳን ጦርን እንደምትደግፍ ጭምጭምታዎች ቢሰሙም በይፋ አቋሟን አልገለጸችም።

አርኤስኤፍን የሚደግፉ አገራት እነማን ናቸው?
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ መሣሪያ፣ የሕክምና ቁሳቁስ እና ሌሎችም ድጋፎችን ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እንደምታቀርብ ይታመናል።
የተባበሩት መንግሥታት ባለሙያዎች ዕውቅና የሰጧቸው ብዙ ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት በቻድ፣ በደቡብ ሱዳን፣ በሊቢያ፣ በሶማሊያ እና በማዕከላዊ አፍሪካን ሪፐብሊክ በኩል ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች፣ ሰው አልባ አውሮፕላኖች እንዲሁም ሌሎች ከፍተኛ የጦር መሣሪያዎችን ሰጥታለች።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ዋነኛ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ደጋፊ መሆኗ ቢታመንም ኬንያ በተለያዩ አጋጣሚዎች የአርኤስኤፍን መሪዎች አስተናግዳለች።
የካቲት 2025 ላይ በኬንያ በተካሄደው የፖለቲካ የውይይት መድረክ ላይ አርኤስኤፍ የራሱን መንግሥት መመሥረቱን ይፋ አድርጓል። በዚህም ምክንያት የሱዳን ጦር በናይሮቢ የሚገኘውን የአገሪቱን ኤምባሲ ለመዝጋትም ተገድዷል።
የሱዳን ጦር፤ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ይደግፋሉ ካላቸው አገራት ማለትም ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ከኬንያ እና ከቻድ ጋር ያለውን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አቋርጧል።
የሊቢያ ብሔራዊ ጦር እና የደቡብ ሱዳን ጦርም ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ይደግፋሉ በሚል በሱዳን ጦር ይከሰሳል።
የደቡብ ሱዳን ጦር "ለአርኤስኤፍ ጦር ቅጥረኛ ወታደሮችን እያቀረበ ነው" ሲል የሱዳን ጦር ከዚህ ቀደም ከስሷል።
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ኬንያ፣ ቻድ፣ ደቡብ ሱዳን እና የሊቢያ ብሔራዊ ጦር የቀረቡባቸውን ክሶች አስተባብለዋል።
የመሣሪያ ሽያጭ
በሱዳን ጦርነት በቀጥታ ባይሳተፉም ቅጥረኛ ወታደር በማቅረም እና ለተዋጊዎቹ የጦር መሣሪያ በማቅረብ ተሳትፎ እንዳላቸው የሚነገርላቸው አገራት አሉ።
በጥቅምት 2025 የፓኪስታን እና የሱዳን ጦር "የ230 ሚሊዮን ዶላር የመከላከያ ስምምነት" የተፈራረሙ ሲሆን፤ ይህም የጦር አውሮፕላን፣ ሰው አልባ አውሮፕላን፣ ወታደራዊ ተሽከርካሪዎች እና የጦር መሣሪያ ጥገናን ያካትታል።
የሱዳን መገናኛ ብዙኃን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚያወጧቸው ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት የሱዳን ጦር "ዘመናዊ ሩሲያ ሠራሽ የሆነውን ሱኮይ ተዋጊ ጄት ከካዛኪስታን እና ኡዝቤኪስታን" ለመግዛት ፍላጎት አለው።
አርኤስኤፍ ቻይና ሠራሽ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ጥቅም ላይ እንደሚያውል የተገለጸ ሲሆን፤ እነዚህ ሰው አልባ አውሮፕላኖች በተባበሩት አረብ ኤምሬትስ አማካኝነት እንደሚገቡም ተጠቁሟል።
ከአፍሪካ አገራት፣ ከዩክሬን እና ከኮሎምቢያ "ቴክኒካ ድጋፍ እና ፓይለቶች" እንደሚያገኝም ተዘግቧል።
በኅዳር 5/2025 የሶማሊያ መከላከያ ሚኒስቴር እንዳለው ከአገሪቱ ሰሜን ምሥራቃዊ የወደብ ከተማ ቦሳሶ አውሮፕላን ማረፊያ ያልታወቁ አውሮፕላኖች ተነስተዋል።
እነዚህ አውሮፕላኖች ወደ ሱዳን፣ ዳርፉር "አንዳች ነገር እያጓጓዙ" እንደነበርም ተገልጿል።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ዝርዝር መረጃ ባይሰጥም፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የሶማሊያን አውሮፕላን ማረፊያዎች በመጠቀም ለአርኤስኤፍ መሣሪያ እንደምትልክ የሚጠቁሙ ሪፖርቶች ወጥተዋል።
የሰላም ጥረት
አሜሪካ የሰላም ስምምነት ላይ እንዲደረስ ሳዑዲ አረቢያ፣ ግብፅ እና የተባበሩት አረብ ኤምሬትስን በማሳተፍ ጥረት አድርጋለች።
ለሦስት ወራት ብቻ የዘለቀ የተኩስ አቁም ላይ ተደርሶ እንደነበርም ይታወሳል።
ሆኖም ግን በይፋ ያልተገለጸ "በአረብ አገራት መካከል የተፈጠረ ልዩነት" ዘላቂ የሰላም ስምምነት ላይ እንዳይረስ ማሰናከሉ ተገልጿል።
የሱዳን ጦር የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ በአደራዳሪነት እንድትሳተፍ ፍላጎት እንደሌለው እና ቱርክ እና ኳታር አሸማጋይ እንዲሆኑ እንደሚሻ ገልጿል።
ሁለቱም ወገኖች በቀጥታ ተገናኝተው ውይይት ለማድረግ ፈቃደኛነት አላሳዩም። ጦርነቱ በቅርብ ጊዜ ያከትማል ብሎ ለማሰብም ያስቸግራል።















