'ሥራችን መግደል ብቻ ነው'- የሱዳኑ አርኤስኤፍ እንዴት ጭፍጨፋ ፈጸመ?

የአርኤስኤፍ ታጣቂዎች ፈገግ ብለው ከተቃጠሉ መኪናዎች ፊት ለፊት
የምስሉ መግለጫ, የአርኤስኤፍ ታጣቂዎች ፈገግ ብለው ከተቃጠሉ መኪናዎች ፊት ለፊት ይታያሉ

ማስጠንቀቂያ፡ ይህ ዘገባ ግድያዎችን የሚመለከቱ መግለጫዎችን ይዟል

ተዋጊዎች በፒክአፕ መኪና ላይ ሆነው በዘጠኝ አስከሬኖች አጠገብ ሲያልፉ እየሳቁ ነበር።

"ይህንን ሥራ ተመልከቱ። ይህንን የዘር ማጥፋት ተመልከቱ" ሲል አንዱ በደስታ ተናገረ።

ካሜራውን ወደራሱ አዙሮ ፈገግ ካለ በኋላ ባልደረቦቹን መቅረጽ ጀመረ። ሁሉም የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች (አርኤስኤፍ) አርማ ያለበትን ወታደራዊ ልብስ ለብሰዋል። "ሁሉም በዚህ መንገድ ይሞታሉ" ሲል ተናገረ።

የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ባለፈው ወር በሱዳን ኤል-ፋሸር ከተማ ከሁለት ሺህ በላይ ሰዎችን ሳይገደሉ አልቀሩም ያሉበትን እልቂት እያወደሱ ነው።

ሰኞ ዕለት ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) "የጦር ወንጀሎች እና በሰው ልጅ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች" ተፈጽመዋል ወይ የሚለውን እየመረመረ መሆኑን ተናግሯል።

ኤል-ፋሸር የአርኤስኤፍ ቁልፍ ዒላማ ነበር። በዳርፉር ግዛት በሱዳን ጦር የተያዘው ጠንካራው ቦታ ነበር። አርኤስኤፍ በ2023 መንግሥት የመሠረተው ጥምረት ከፈረሰበት ጊዜ ጀምሮ ከአገሪቱ ጦር ጋር አውዳሚ ጦርነት ጀምረዋል።

ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ ከ150 ሺህ በላይ ሰዎች በጦርነቱ እንደተገደሉ ይገመታል። ሁለቱም ወገኖች በጦር ወንጀሎች ይከሰሳሉ። ተመሳሳይ ክሶች ከኤል-ፋሸር ውድቀት በኋላም ተደግመዋል።

ካርታ

ከዓለም የተቆራረጠች ከተማ

ከተማዋን ለሁለት ዓመታት ያህል በከበባ ሥር ካቆየ በኋላ፣ ከነሐሴ ወር ጀምሮ አርኤስኤፍ ይዞታውን ለማጠናከር እና የቀረውን የሲቪል ሕዝብ ለማገድ ተንቀሳቀሰ።

የሳተላይት ምሥሎች እንደሚያሳዩት ወታደሮች በኤል-ፋሸር ዙሪያ ግዙፍ የሆነ የአሸዋ መከላከያ መገንባት ጀምረዋል።

የመግቢያ መንገዶችን ዘግተው የእርዳታ ቁሳቁሶችን አግደዋል። በጥቅምት ወር መጀመሪያ ላይ ቀለበቱ ከተማዋን ሙሉ በሙሉ ከበባት።

አንድ አጎራባች መንደር ጭምር ከከበባው አልተረፈችም። ውጥረቱ እየተባባሰ ሄዶ መስከረም 19 በአንድ መስጊድ ላይ አርኤስኤፍ ባደረሰው ጥቃት 78 ሰዎች ተገደሉ።

የተባበሩት መንግሥታት በበኩሉ በጥቅምት ወር በተፈናቃዮች ካምፕ ላይ በተደረጉ የድሮን እና የመድፍ ጥቃቶች 53 ተጨማሪ ሰዎች ተገድለዋል ሲል ገለጸ።

ለቢቢሲ ቬሪፋይ የደረሱ ቪዲዮዎች አርኤስኤፍ የምግብ እና አስፈላጊ አቅርቦቶችን እንዳይገቡ እገዳ ለመጣል እንደሞከረ ጠቁመዋል።

በጥቅምት ወር ደግሞ እጆቹንና እግሮቹን በብረት ሰንሰለት ታስረው ከዛፍ ላይ ወደታች የተንጠለጠለ ሰው የሚያሳይ ቪዲዮ ወጣ። ግለሰቡ ወደተከበበችው ከተማ ዕቃ ለማስገባት ሞክሯል ሲል ቪዲዮውን የሚቀርጸው ሰው ይከሰዋል።

"በፈጣሪ ስም እምልልሃለሁ፣ አንተ ውሻ ለዚህ ሥራህ ዋጋ ትከፍላለህ" ሲለው፤ እስረኛው ሕይወቱን ለማትረፍ ለመነ።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአርኤስኤፍ ወታደሮች ወደ ከተማዋ መግባት ሲጀምሩ ደግሞ በእግረኛ ጦር ግጭት ውስጥ ገብተዋል።

ካርታ

ያልታጠቁ ሰዎች ግድያ

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ጥቅምት 26 አርኤስኤፍ የመጨረሻውን እና በከተማው ውስጥ ያለውን ዋና የጦር ሰፈር ተቆጣጠረ። የ6ኛው እግረኛ ክፍል ዋና መቀመጫ ነበር።

ወታደሮቹ ዋናውን የጦር ሰፈር ከተቆጣጠሩ በኋላ የጦር መሣሪያቸውን ይዘው እየሳቁ ሲጎበኙ ተቀርጿል።

በተመሳሳይ ቀን የአርኤስኤፍ አዛዥ አብዱል ራሒም ዳጋሎ (የአርኤስኤፍ መሪ መሐመድ 'ሄሜቲ' ዳጋሎ ወንድም) የጦር ሰፈሩን ሲጎበኙ ታይተዋል።

ከ2003-2005 በዳርፉር በመቶ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከገደለው የጃንጃዊድ ሚሊሻ የተወደለው አርኤስኤፍ ሱዳን ውስጥ አረብ ባልሆኑ ቡድኖች ላይ ጭካኔ ፈጽሟል ተብሎ ለረዥም ጊዜ ተከሷል።

በበይነ መረብ የተለቀ ቪዲዮ የቡድኑ ተዋጊዎች በኤል-ፋሸር በሲቪል ሕዝብ ላይ ዓመፅ ለማነሳሳት እንዳሰቡ ይጠቁማል።

ቡድኑ ኤል-ፋሸርን ከመቆጣጠሩ በፊት ለወራት ከከተማው ብዙም መረጃ አይወጣም ነበር። ከጦሩ መውጣት ከጥቂት ሰዓታት በኋላ አርኤስኤፍ የፈጸማቸውን ግፎች የሚያሳይ ቪድዮ መውጣት ጀመረ።

ቢቢሲ ቬሪፋይ ከተነተናቸው በጣም አስደንጋጭ ቪዲዮዎች አንዱ በከተማው ምዕራባዊ ክፍል በሚገኝ የዩኒቨርሲቲ ሕንፃ ላይ በደርዘን የሚቆጠሩ አስከሬኖች ወለሉ ላይ ተበታትነው ያሳያል።

ነጭ ቱታ የለበሱ አንድ አዛውንት በሬሳዎቹ መካከል ብቻቸውን ተቀምጠው ነበር። ጠመንጃ የታጠቀ ተዋጊ ወደ እሳቸው ሲቀርብ ደረጃውን ለመውረድ ሞከሩ።

ታጣቂው መሣሪያውን አንስቶ ሰውዬውን በአንድ ጥይት ተኩሶ ሲመታቸው ወደ ወለሉ ወደቁ። በድርጊቱ ያልተደናገጡት የቡድኑ አባላት ከአስከሬኖች ውስጥ የሌላ ሰው የእግር ሲንቀሳቀስ ተመለከቱ።

"ይህ ሰው ለምን በሕይወት ተገኘ" ሲል አንድ ታጣቂ ጮኸ። "ግደሉት!"

በዬል የሰብአዊ ምርምር ላብራቶሪ በታተመው ሪፖርት መሠረት ጥቅምት 26 የተነሱት የሳተላይት ምሥሎች እንደሚያሳዩት ከሆነ በኤል-ፋሸር፣ ኤሲ ጎዳናዎች ላይ ግድያዎች መፈጸማቸውን የሚያረጋግጡ ይመስላሉ።

ተንታኞቹ በምሥሎቹ ውስጥ የሚታዩ ትላልቅ "ክምችቶችን" አጉልተው አሳይተዋል። እነዚህም "ከአዋቂ የሰው አካል መጠን ጋር የሚጣጣሙ እና በቀደሙት ምሥሎች ላይ የማይገኙ" ናቸው ብለዋል።

በተጨማሪም ሪፖርቱ በሰው ደም ምክንያት የተከሰቱ ምልክቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ የሚገልጸውን "ቀለም መቀየር" ጠቁሟል።

ለቢቢሲ የተናገሩ አንድ የዓይን ምስክር "ብዙ ዘመዶቻችን በአንድ ቦታ ተሰብስበው ሁሉም እንደተገደሉ" መመልከታቸውን ተናግረዋል።

ሌላ ምስክር ደግሞ አርኤስኤፍ የአንዲትን ግለሰብ "ሁሉንም ንብረቶቿን ከወሰደ በኋላ" ስትገደል ማየቱን አስታውሷል።

ካርታ

ዋናው የአርኤስኤፍ ኃይል ኤል-ፋሸርን ሲወር፣ ሌላ የታጣቂዎች ቡድን በከተማው ዳርቻ ላይ ቆይቶ በርካታ ያልታጠቁ ምርኮኞችን በጭካኔ ገድሏል።

አብዛኛው ይህ ጥቃት የተፈፀመው ከኤል-ፋሸር ስምንት ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ቦታ ነው። የተረጋገጡ ቪዲዮዎች እንዳሳዩት ከሆነ በደርዘን የሚቆጠሩ የሲቪል ልብስ የለበሱ አስከሬኖች ታይተዋል። አንዳንዶቹ ሴቶች ይመስላሉ።

ሌሎች ቪዲዮዎች ደግሞ መኪናን ጨምሮ በርካታ ንብረቶች በእሳት ተቃጥለው መበታተናቸውን ያሳያሉ። በቪዲዮዎች ላይ በተሽከርካሪዎቹ መካከል የተበተኑ አስከሬኖችም ይታያሉ።

የጥቃቱ ቁልፍ ሰው ቀደም ሲል በቢቢሲ ቬሪፋይ የተለየው እና በበይነ መረብ ስሙ 'አቡ ሉሉ' የሚባለው የአርኤስኤፍ አዛዥ ነው።

በሁለት ቪዲዮዎች ላይ ያልታጠቁ ምርኮኞችን ሲገድል ይታያል። አንድ የዓይን ምስክር ለቢቢሲ እንደተናገረው "ልጆችን ጨምሮ በርካታ ንፁኃን ሰዎችን እንዲገድሉ ለወታደሮቹ ትዕዛዝ ሰጥቷል።"

በአንድ ቪዲዮ ላይ አቡ ሉሉ የተጎዳ ሰው ለመግደል ሲዘጋጅ አንድ የአርኤስኤፍ ወታደር ጣልቃ ለመግባት ሲሞክር ይታያል። እስረኛው "አውቅሀለሁ፤ ከጥቂት ቀናት በፊት ደውዬልሀለሁ" ሲል ይማጸናል።

አቡ ሉሉ የሰውየውን ልመና ወደጎን በማለት "በፍፁም ምሕረት አላደርግም። ሥራችን መግደል ብቻ ነው" ይላል።

ከዚያም ጠመንጃውን በዘፈቀደ ካነሳ በኋላ በተደጋጋሚ ተኩሶ ያልታጠቀውን ሰው መታው።

ሌላ ቪዲዮ ላይ ደግሞ ዘጠኝ ያልታጠቁ ምርኮኞችን ሲገድል ያሳያል። ከቀናት በኋላ የወጣው ቪዲዮ አስከሬኖቹ በወደቁበት ቦታ እንደተተዉ ያሳያል።

በግድያዎቹ ውስጥ ከተሳተፉት መካከል ብዙዎቹ የአርኤስኤፍ ልብሶችን ለብሰዋል።

"የዘር ማጥፋት" ተፈጽሟል በሚል ደስታቸውን ሲገልጹ የሚታዩ ታጣቂዎችም እንዲሁ የአርኤስኤፍ መለያ ልብሶችን ለብሰዋል።

የአርኤስኤፍ አርማ ያለው ወታደራዊ ዩኒፎርም የለበሱ ታጣቂዎች
የምስሉ መግለጫ, የአርኤስኤፍ አርማ ያለው ወታደራዊ ዩኒፎርም የለበሱ ታጣቂዎች

የአርኤስኤፍ አዛዦች ጉዳዩን ለመቆጣጠር የሚያደርጉት ጥረት

ከጭፍጨፋው በኋላ የአርኤስኤፍ መሪ ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ ወታደሮቻቸው "ጥሰቶችን" እንደፈጸሙ አምነው ክስተቶቹ እንደሚመረመሩ ተናግረዋል።

አንድ ከፍተኛ የተባበሩት መንግሥታት ባለሥልጣን ባለፈው ሳምንት አርኤስኤፍ አንዳንድ ተጠርጣሪዎችን እንዳስያዘ ማስታወቁን ተናግረዋል።

ቢቢሲ ቬሪፋይ ግድያውን በተመለከተ ዘገባ ካወጣ በኋላ ከታሰሩት መካከል አቡ ሉሉ ይገኙበታል። በአርኤስኤፍ ይፋዊ የቴሌግራም ገጽ ላይ በኤል-ፋሸር ዳርቻ ላይ ወደሚገኝ እስር ቤት መወሰዱ ይታያል።

የዬል ተንታኞች አርኤስኤፍ "የጅምላ ጭፍጨፋ ጥሰቶችን መረጃ እያጠፋ ነው" ሲል ከሷል።

ኅዳር 4 የወጣ አንድ ሪፖርት እንዳመለከተው የሳተላይት ምሥሎች "ከአርኤስኤፍ ይዞታ በስተሰሜን በሚገኝ ቦታ" እና በኤል-ፋሸር በሚገኘው የሕፃናት ሆስፒታል አቅራቢያ መቃብሮችን እንደነበሩ ለይተዋል።

ቢቢሲ ቬሪፋይ ጥቅምት 30 በሆስፒታሉ ግቢ ውስጥ የሚታዩ ነጭ እቃዎች ከ1.6 ሜትር እስከ 2 ሜትር ርዝመት እንዳላቸው ለመለካት ችሏል።

ይህ ከአዋቂ ሰው ቁመት ጋር የሚስተካከል ሲሆን በሱዳን ውስጥ በተለምዶ ከሚታየው የቀብር ሥነ ሥርዓት ጋር የሚመሳሰል ነው።

አርኤስኤፍ የጦር ምርኮኞች ተገቢው ጥበቃ እንደሚደረግላቸው በማኅበራዊ ሚዲያው አሳውቋል
የምስሉ መግለጫ, አርኤስኤፍ የጦር ምርኮኞች ተገቢው ጥበቃ እንደሚደረግላቸው በማኅበራዊ ሚዲያው አሳውቋል

ይህ በእንዲህ እንዳለ፤ የአርኤስኤፍ እና የተያያዥ ቡድኖች የማኅበራዊ ሚዲያዎች ትርክቱን ለመቀየር እየሞከሩ ነው።

ተዋጊዎቹ ለሲቪሎች እርዳታ ሲሰጡ የሚያሳዩ ቪዲዮዎች በአንዳንድ ተጠቃሚዎች ተጋርተዋል። የታጣቂዎቹ የሚዲያ ቢሮ ደግሞ የጦር ሠራዊት የጦር ምርኮኞች ሰብአዊ አያያዝን የሚያሳዩ በርካታ ቪዲዮዎችን አጋርቷል።

አርኤስኤፍ የተለያዩ የማኅበራዊ ሚዲያ ዘመቻቸውን ቢጀምርም በኤል-ፋሽር የፈጸሙት ጥቃት ዓለም አቀፍ ቁጣን ቀስቅሷል።

ቢቢሲ ቬሪፋይ በጉዳዩ ላይ አስተያየት እንዲሰጥ ለአርኤስኤፍ ጥሪ ቢያቀርብም ምላሽ አላገኘም።