የሶማሊያና የኢትዮጵያ መሪዎች በሶማሊያ ላይ የተጣለው የጦር መሳሪያ ማዕቀብ እንዲነሳ ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, Office Of The Prime Minister
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ሶማሊያ የተጣለባትን የጦር መሳሪያ ማዕቀብ እንዲያነሳላት ያቀረበችውን ጥያቄ እንዲያጤነው የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ መሪዎች ጠየቁ።
የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ለሁለት ቀናት በኢትዮጵያ ያደረጉት ጉብኝት ተከትሎ ሁለቱ አገራት በጥምር ባወጡት መግለጫ የጦር መሳሪያው ማዕቀብ መነሳት ሶማሊያ ከአልሻባብ የተጋረጠባትን ስጋት ለመቅረፍ ሁነኛ ነው ብሏል።
ከተመረጡ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ መስከረም 18 እና 19/2015 ዓ.ም. ጉብኝታቸውን ያደረጉት የሶማሊያው ፕሬዚዳንትና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ውይይታቸውን ተከትሎ አገራቱ በጋራ በሚሰሯቸው ጉዳዮች ላይ በዛሬው ዕለት በጋራ መግለጫ አውጥተዋል።
ሁለቱ መሪዎች የሁለትዮሽ የምጣኔ ሀብት ትብብር፣ ሽብርተኝነት እና ጽንፈኝነት መዋጋት እንዲሁም የጋራ እና አህጉራዊ ጉዳዮችን አንስተው የተወያዩ ሲሆን በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ በማተኮርም ቅድሚያ በሚሰጧቸው ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል።
መሪዎቹ ከተስማሙባቸው ጉዳዮች መካከል የሁለቱን አገራት የግዛት ሉዓላዊነት እና አንድነትን በማክበር ላይ የተመሰረተ ለዘመናት የዘለቀውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማጠናከር ስምምነት ላይ ደርሰዋል።
የእስልምና ፍርድ ቤቶች ኅብረት ወይም አልሸባብ ከመምጣቱ በፊት ሶማሊያ ውስጥ የፀጥታ ስጋት በሚፈጠርበት ወቅት ሠራዊቷን የምታስገባው ኢትዮጵያ፣ በተለይም ከአልሻባብ ጋር በነበረው ትግል ዋና አጋር ሆና መቀጠሏ ይታወሳል።
ኢትዮጵያ አልሻባብን ለማጥፋት በሚደረገው ትግልም ጣልቃ ገብነት አሳይታለች ተብላ ብትተችም ሁለቱ መሪዎች ለኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ክብርን ሰጥተዋል።
መሪዎቹ ባወጡትም መግለጫ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ለሶማሊያ ሰላም፣ መረጋጋት እና ግንባታ ከፍተኛውን መስዋዕትነት ከፍሏል ብለዋል።
አገራቱ የጋራ ጠላት ብለው የጠሩትን ሽብረተኝነትን እና ፅንፈኝነትን በመዋጋት ውጤታማ በሆነ መንገድ ለመተባባር ቁርጠኝነት እንዳላቸውም ገልጸዋል።
በዚህም የፀጥታ መዋቅሮቻቸው የትብብር ስልቶቻቸውን እንዲያጠናክሩ መመሪያ መስጠትን ጨምሮ የመረጃ ልውውጥ ለማድረግም ተስማምተዋል።
በዚህም ታጣቂው ቡድን አልሻባብ በሶማሊያ ውስጥ የደቀነውን የፀጥታ ስጋት በብቃት ለመታገልና በበቂ ሁኔታ ለመታጠቅ በአገሪቱ ላይ የተጣለው የጦር መሳሪያ ማዕቀብ የመነሳትን ጥያቄ የፀጥታው ምክር ቤት እንዲያጤነው ጠይቀዋል።
ከአልቃኢዳ ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚነገርለት እስላማዊው ቡድን አልሻባብ ከሶማሊያ ባሻገር በጎረቤት አገራት ውስጥም የሽብር ጥቃቶችን ሲፈጽም መቆየቱ ይታወሳል።
ከጥቂት ወራት በፊት ደግሞ ቡድኑ ሶማሊያ ከኢትዮጵ ጋር የምትጋረውን ረጅም ድንበር አልፎ በመግባት ለመጀመሪያ ጊዜ ጠንካራ ወታደራዊ ጥቃት ፈጽሞ ነበር።
በዚህም በርካታ የቡድኑ አባላት እንዲሁም ከፍተኛ አመራሮች በኢትዮጵያ ኃይሎች መገደላቸውንና መማረካቸውን የኢትዮጵያ መንግሥት ይፋ አድርጓል።
አዲስ የተመረጡት የሶማሊያው ፕሬዝዳንት አገሪቱን ለማረጋጋት አልሻባብን መቆጣጠር ቁልፍ ተግባራቸው መሆኑን በመግለጽ፣ የመንግሥታቸውን ሠራዊት እያጠናከሩ ይገኛሉ። ለዚህም እንዲያግዛቸው በመንግሥታቱ ድርጅት የተጣለው ማዕቀብ እንዲነሳ ይፈልጋሉ።
ለ30 ዓመታት ያህል የቆየው የጦር መሳሪያ ማዕቀብ እንዲነሳ የሶማሊያ የፌደራል መንግሥት ለተተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ጥያቄ ማቅረቡም ተገልጿል።
በሲያድ ባሬ ይመራ የነበረው የሶማሊያ ማዕከላዊ መንግሥት መፍረሱን ተከትሎ ለቀጠለው የእርስ በርስ ጦርነት እና እየከፋ ለመጣው የሰብዓዊ ሁኔታንም ለማረጋጋትም በሚል ነበር የጦር መሳሪያ ማዕቀቡ የተጣለው።
የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት በአውሮፓውያኑ 1992 የጣለው የጦር መሳሪያ ማዕቀብ የጊዜ ገደብ ሳይኖረው ክፍት ሆኖ እንዲቆይ መወሰኑ ይታወሳል።












