የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ምርጫና ቀጠናዊ አንደምታው

አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ

እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ከ2012 እስከ 2017 የሶማሊያ ስምንተኛው ፕሬዝዳንት የነበሩት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ በድጋሚ ተመርጠዋል።

በሦስት ዙር በተካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ 214 አብላጫ ድምጽ በማግኘት፣ ሞሐመድ አብዱላሂ ፈርማጆን አሸንፈው ሥልጣነ መንበሩን ተረክበዋል።

በሥልጣን ዘመናቸው፣ በሶማሊያ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን፣ አልፎም ሶማሊያ ከአፍሪካ ቀንድ አገራት እንዲሁም ከምዕራቡ ዓለም አገራት ጋርም እርቀ ሰላም እንድታወርድ እንደሚሠሩ ቃል ገብተዋል።

ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ በ2017 በድጋሚ ሲወዳደሩ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ፈርማጆ እንደረቷቸው ይታወሳል። አሁን ደግሞ መልሰው ሥልጣኑን ከፈርማጆ ተረክበዋል።

በኮቪድ-19 ምክንያት ከዓመት በላይ ተራዝሞ የነበረው ምርጫ በሶማሊያ ለወራት የዘለቁ ውዝግቦች መጫሩ አይዘነጋም።

የአገሪቱ የታችኛው ምክር ቤት የምርጫ ማራዘሚያ ውሳኔን በማጽደቅ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ፈርማጆን የሥልጣን ዘመን ለሁለት ዓመት ማራዘሙን ተከትሎ በሶማሊያ ፖለቲከኞች መካከል የተፈጠረው ስንጥቅ በመዲናዋ ሞቃዲሾ ሁከት ማስከተሉ ይታወሳል።

በፌደራል መንግሥት ደጋፊዎችና ተቃዋሚዎች መካከል በተነሳ ግጭት ቢያንስ 10 ሰዎች መገደላቸው ተዘግቧል።

በተለይም በፈርማጆ እና በጠቅላይ ሚኒስትር መሐመድ ሑሴን ሮብሌ መካከል የተፈጠረው እሰጣ ገባ ተካሮ፣ ፈርማጆ ጠቅላይ ሚኒስትሩን ከሥልጣን እስከማገድ ደርሰዋል።

የፖለቲካ ውጥንቅጡ ያሰጋቸው የአፍሪካ ኅብረት፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ አሜሪካ እና እንግሊዝ ፈርማጆ የሥልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም መወሰናቸውን ኮንነዋል። እንዲያውም አሜሪካ "በሥልጣን ማራዘሙ በተሳተፉት" ላይ ማዕቀብ እንደምትጥልም ዝታ ነበር።

በሌላ በኩል ትላንት ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን በመቶዎች የሚቆጠሩ የአሜሪካ ወታደሮች እንደገና በሶማሊያ እንዲሰማሩ ፈቃድ መስጠታቸው ተገልጿል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ 700 የሚጠጉ ሶማሊያ ውስጥ ሰፍረው የነበሩ ሁሉም ወታደሮቻቸው አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ያሳለፉትን እርምጃ ባይደን ቀልብሰው፣ የአሜሪካ የልዩ ተልዕኮ ኃይል አባላት በድጋሚ እንደሚሰማሩ ተነግሯል።

የ30 ዓመታት የእርስ በእርስ ጦርነት ያሽመደመዳት ሶማሊያ በበርካታ ውስጣዊና ውጫዊ ፖለቲካዊ ፍላጎቶች የተወጠረች አገር ናት። በዚያ ላይ ስር የሰደደ ሙስና እንዲሁም የጎሳ ክፍፍል ይንጣታል።

አክራሪው ታጣቂ ቡድን አል-ሸባብ ሶማሊያን ከጥግ ጥግ ከማናጋት አልፎ የአፍሪካ ቀንድ ስጋት ከሆነም ሰነባብቷል።

የመካከለኛው ምሥራቅም ይሁን የምዕራቡ ዓለም አገራት ሶማሊያ ላይ ካላቸው ልዩ ፖለቲካዊ ፍላጎት ባሻገር፣ አሳሳቢው ድርቅ እና ምጣኔ ሀብታዊ ቀውስ ሕዝቡን እየፈተነው ይገኛል።

ለመሆኑ የሐሰን ሼክ ሞሐሙድ መመረጥ ለሶማሊያ፣ ለአፍሪካ ቀንድ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ምን ማለት ነው? በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነትስ ሊለወጥ ይችላል?

ዳሰሳችንን ከኢትዮጵያ ጀምረን ወደ ቀጠናው ከዚያም ወደ ሶማሊያ እናደርጋለን።

አዲሱ ፕሬዝዳንት እና ኢትዮጵያ

በአዲሱ ፕሬዝዳንት ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ እና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት ምን ሊመስል ይችላል? የሚለውን ለመገመት ከኢትዮጵያ እና ከቀድሞው ሶማሊያ ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ፈርማጆ ግንኙነት ጋር የተያያዙ ሁለት ቁልፍ ነጥቦችን እናንሳ።

አንደኛው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን መምጣታቸውን ተከትሎ ከኤርትራው ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ እና ከፈርማጆ ጋር የደረሱት ሦስትዮሽ ስምምነት ነው።

ሁለተኛው ቁልፍ ነጥብ ደግሞ የሶማሊያ ወታደሮች በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ተሳትፎ ነበራቸው የሚለው ያልተረጋገጠ ክስ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ፈርማጆ እና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ እአአ በ2018 መባቻ ላይ የሦስትዮሽ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ፈርማጆ እና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ እአአ በ2018 መባቻ ላይ የሦስትዮሽ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፣ የቀድሞው ፕሬዝዳንት ፈርማጆ እና ፕሬዝዳንት ኢሳያስ እአአ በ2018 መባቻ ላይ የሦስትዮሽ ስምምነት መፈራረማቸው ይታወሳል።

በእርግጥ ይህ ስምምነት ዝርዝር ይዘቱ ምንድን ነው? ለሚለው ግልጽና ይፋዊ መረጃ ባይወጣም፣ ስምምነቱ ሲፈረም ፈርማጆ በትዊተር ገጻቸው "በአስመራ ከተማ ስምምነት በመፈረማችን ኩራት ይሰማኛል። ስምምነቱ የምጣኔ ሀብት፣ የፖለቲካ፣ የደኅንነት፣ የባህልና የማኅበረሰብ ትብብርን የሚያጎለብት ነው" ብለው ነበር።

በቀጣይ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሁለቱን መሪዎች ወደ ጎንደር ከተማ ጋብዘዋቸው በአስመራ ስለተፈረመው የሦስትዮሽ ስምምነት ውይይት ማድረጋቸው ተዘግቧል።

ይህንን የሦስቱ መሪዎች ስምምነት በጥርጣሬ የተመለከቱ የፖለቲካ ልሂቃን ድምጻቸውን ማሰማታቸው አይዘነጋም።

ይህ የሦስትዮሽ ግንኙነት በአዲሱ ፕሬዝዳንት ሊቀጥል ይችላል? ስንል የአፍሪካና ኦሪየንታል ስተዲስ አጥኚና የምሥራቅ አፍሪካን ፖለቲካ በቅርበት የሚከታተሉት አቶ ነዓምን አሸናፊን ጠይቀናል።

የሦስትዮሽ ግንኙነቱ ቀጠናዊ ትስስርን "ገሸሽ ያደረገ ነው" ተብሎ ሲተች እንደነበረ በመጥቀስ "አዲሱ ፕሬዝዳንት የሦስትዮሽ ስምምነቱን ጥለው ሊወጡ ይችላሉ" ይላሉ።

በሶማሊያ ልሂቃን ዘንድ ይህ ስምምነት ሲተች እንደነበር በማንሳት፣ ምናልባትም አዲሱ ፕሬዝዳንት ስምምነቱን እንደማያስቀጥሉ ያብራራሉ።

"የሦስትዮሽ ግንኙነቱ ቀርቶ ሁለቱ አገራት [ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ] አዲስ የሁለትዮሽ ግንኙነት መጀመር ይኖርባቸዋል። ግንኙነቱ አል-ሸባብ የሚፈጥረውን የፀጥታ ስጋት እንዲሁም የተከሰተውን ድርቅ ያማከለ መሆን አለበት" ሲሉም በኢትዮጵያ በኩል መወሰድ ስለሚኖርባቸው የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ አቅጣጫ ለውጦች ያስረዳሉ።

በሌላ በኩል፣ የሶማሊያ ወታደሮች በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ተሳትፎ ነበራቸው ስለሚለውን ያልተረጋገጠ ክስ አቶ ነዓምንን ጠይቀናል።

"ክሱ እውነት ከሆነ ከዚህ በኋላ [ስምሪቱ] አይኖርም። ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ እንደ ሞሐመድ አብዱላሂ ፈርማጆ ጦርነቱ ውስጥ ጣልቃ ከመግባት ይልቅ የማደራደር፣ የማሸማገል ሚና ሊኖራቸው ይችላል" ሲሉ መልሰዋል።

ለዚህ መከራከሪያ ነጥብ እንደ ማስረጃ የሚያቀርቡት ሁለት ነጥቦችን ነው።

በመጀመሪያ ደረጃ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እንዲሁም የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድርና የህወሓት ሊቀ መንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል ለአዲሱ ፕሬዝዳንት የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት ማስተላለፋቸውን ያጣቅሳሉ።

"ሁለቱም መግለጫ ማውጣታቸው [አዲሱ ፕሬዝዳትን] አንዳች ሚና በቀጠናው እንደሚኖራቸው ጠቋሚ ነው" ይላሉ አቶ ነዓምን።

በሁለተኛነት የሚጠቅሱት ሶማሊያ ለአገር ውስጥ ደኅንነቷ የኢትዮጵያን ሰላም አስከባሪዎች መፈለጓን ነው።

በኢትዮጵያ ጦርነት ከተፋፋመ፣ በአሚሶም ስርና ውጭም ሶማሊያ ውስጥ የተሰማሩት የኢትዮጵያ ሰላም አስከባሪዎች ወደ አገር ቤት ሊመለሱ የሚችሉበት ዕድል እንደሚሰፋ በመጥቀስ አዲሱ መሪ "የኢትዮጵያ ጦር እዛው ሆኖ ሶማሊያን የማረጋጋት ሥራ እንዲቀጥል የሚፈልጉ ይመስለኛል" በማለት ያስረዳሉ።

የኢትዮጵያ ጦር ሶማሊያን ጥሎ እንዳይወጣ በሚል ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ በኢትዮጵያ የፌደራል መንግሥትና በትግራይ ኃይሎች መካከል ሰላም እንዲወርድ የመደገፍ ሚና እንደሚኖራቸው ነው አቶ ነዓምን የሚጠብቁት።

የሁለቱ አገራት ግንኙነት ምን ሊመስል ይችላል? የሚለው በጠቅላላው ሲቃኝ በአንድ በኩል አብዛኞቹ የሶማሊያ ፖለቲካ ልሂቃን አገራቸው አሁን ለገባችበት ቀውስ ኢትዮጵያን ተጠያቂ በማድረግ ጥላቻ አዘል አስተያየት ቢሰነዝሩም፣ በሌላ በኩል አዲሱ ፕሬዝዳንት ከኢትዮጵያ ጋር መልካም ግንኙነት እንደነበራቸው ያስረዳሉ።

"ከኢትዮጵያ ጋር መልካም ግንኙነት አላቸው። አዲስ አበባ በተደጋጋሚ ይመጡ ነበር። ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ጋር የቀረበ ግንኙነት ነበራቸው። ከዚህ ቀደም ሥልጣን ላይ ስለነበሩና አካባቢውን ስለሚያውቁትም መመረጣቸው እንደ ጸጋ ሊወሰድ ይችላል።"

በተቃራኒው ግብፅና ሌሎችም የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት የሶማሊያን "እጅ መጠምዘዝ" እንደሚችሉ ጠቅሰው፣ ይህም በተለይም ከግብፅ በኩል ወደ ኢትዮጵያ አደጋ እንደሚቃጣ ያስረዳሉ።

"የመካከለኛው ምሥራቅን ሚና ለማስፋት ሶማሊያን እንደ መነሻ ይጠቀሟታል። ቱርክ የሶማሊያን ምጣኔ ሀብትና ፖለቲካ ስለምትቆጣጠርም የአዲሱ ፕሬዝዳንት ምርጫ አስጊ ሊሆን ይችላል።"

የአፍሪካ ቀንድና አዲሱ የሶማሊያ ፕሬዝዳንት

የአፍሪካ ቀንድ ከውስጣዊ የፖለቲካ ቀውስ አልፎ በአገራት መካከል በሚነሳ የወሰን፣ የጥቅማ ጥቅምና ሌሎችም ግጭቶች ይታመሳል።

ኬንያ እና ሶማሊያ፣ ሱዳን እና ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ደቡብ ሱዳን እንዲሁም ሌሎችም የቀጠናው አገራት በተጠንቀቅ ይጠባበቃሉ።

ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ "ሰላምን በመስበክ" እንደሚታወቁ የሚጠቅሱት አቶ ነዓምን "ለንግግር ክፍት ይመስላሉ። እንደ ፈርማጆ በሌላ አገር ጣልቃ የመግባት አዝማሚያ ሳይሆን ከጎረቤቶቻቸው ጋር ሰላም የመፍጠር አዝማሚያ ያላቸው ይመስላል" ሲሉ ያስረዳሉ።

በሶማሊያ፣ በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መሪዎች መካከል የተፈረመው ሦስትዮሽ ስምምነትን በተመለከተም "ምንነቱ የማይታወቅ፣ ኢጋድን የዘለለ ስምምነት ነው። ፖለቲካዊ፣ማኅበራዊ ወይም ምጣኔ ሀብታዊ ለማለት የሚቸገር ስምምነት መሰል ነው። [አዲሱ ፕሬዝዳንት] በዚህ በማያውቁት ስምምነት ላይ ይገባሉ ብዬ አላምንም" ሲሉ ያክላሉ።

ይህ ስምምነት ከተገታ፣ በቀጣይ ኬንያ፣ ሱዳን፣ ደቡብ ሱዳን፣ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ እና ሶማሊያም የተሳተፉበት ቀጠናዊ ትስስር ለመፍጠር ዕድል ሊፈጥር እንደሚችል ያምናሉ።

አዲሱ ፕሬዝዳንት በተለይም ከጎረቤቶቻቸው ጋር ሰላም ማውረድ እንደሚሹ በበዓለ ሲመታቸው ገልፈዋል።

ስለዚህም በሶማሊያ እና በኬንያ እንዲሁም በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ መካከል የሚከሰቱ የድንበር ግጭቶች እንደሚረግቡ ተስፋ አለ።

"የቀጠናውን አሰላለፍ ከመካከለኛው ምሥራቅ፣ ከቱርክ እና ከምዕራቡ አገራት ፍላጎት ጋር አጣጥመው ከጎረቤቶቻቸው ጋር ሰላም እንደሚያወርዱ ይታመናል" ይላሉ አቶ ነዓምን።

2017 ላይ ያሸነፏቸው ፈርማጆን በ2022 መልሰው አሸንፈዋቸዋል።

የፎቶው ባለመብት, EPA

የምስሉ መግለጫ, 2017 ላይ ያሸነፏቸው ፈርማጆን በ2022 መልሰው አሸንፈዋቸዋል።

ለሶማሊያ አዲስ ጅማሮ?

ተንታኞች እንደሚሉት፣ የሐሰን ሼክ ሞሐሙድ በድጋሚ መመረጥ ሶማሊያን እንደ አዲስ ለመገንባት ለሚደረገው ጥረት መነሻ ተደርጎ ይቆጠራል።

በሌላ በኩል የሶማሊያን ውስብስብ ፖለቲካ፣ የውስጥና የውጭ ጠንካራ ፍላጎቶችን ከግምት በማስገባት የፕሬዝዳንቱ የሥልጣን ዘመን በፈተና እንደሚሸበብ ይገመታል።

አቶ ነዓምን በበኩላቸው፣ በከፍተኛ ሙስና እና የፖለቲካ ንቅዘት ሲታማ የነበረውን የፈርማጆ አስተዳደር አውርዶ የመጣ አዲስ አመራር እንደመሆኑ "ለሶማሊያ አዲስ ተስፋ ያጭራል" ሲሉ አዲሱን አስተዳደር ይገልጹታል።

በፈርማጆ እና በጠቅላይ ሚኒስትራቸው መካከል ተፈጥሮ የነበው ውዝግብ ከጎሳ አባላት ባለፈ በፖለቲካ ልሂቃኖች መካከል ክፍተት ፈጥሮ እንደነበር በማስታወስ፣ አዲሱ ጅማሮ የሶማሊያን የፖለቲካ ተዋናዮች ወደ አንድ ጠረጴዛ አምጥቶ ሰላም ለማውረድ በር እንደሚከፍት ይጠብቃሉ።

ፈርማጆ የሥልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም በመሞከራቸው የተነሳው ውዝግብ ሶማሊያ ካሳየችው ማንሰራራት እየተንሸራተተች ነው የሚል ስጋት እንደጫረ ጠቅሰው፣ ቀውሱን ከማርገብ አንጻር ፕሬዝዳንቱ ተስፋ እንደሚጣልባቸው ያክላሉ።

የተባበሩት መንግሥታት ወደ ረሃብ ሊሸጋገር ይችላል ላለው ድርቅ መፍትሄ ከማበጀትና አል-ሸባብን ከመዋጋት አንጻር እንደ አሜሪካ ካሉ አጋር አገራት ጋር በትብብር ለመሥራት የአዲሱ ፕሬዝዳንት መመረጥ ከፍተኛ ሚና አለው።

"ውስብስቡ የሶማሊያ ፖለቲካ በአንድ ምሽት፣ በአንድ ፕሬዝዳት ይፈታል ባይባልም አዲስ ጅማሮ ነው ማለት ይቻላል" ይላሉ አቶ ነዓምን።

በሌላ በኩል ደግሞ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫው በ329 የጎሳ ወኪሎች የተካሄደ እንጂ ሕዝቡ የተሳተፈበት አለመሆኑን በማንሳት፣ ፖለቲካዊ ተሳትፎ እንዳልተረጋገጠ ያስረዳሉ።

ጥቂት ስለ ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ

አዲሱ ፕሬዝዳንት በትምህርት ዘርፍ ይታወቃሉ። የምረጡኝ ቅስቀሳቸው ማጠንጠኛ ሶማሊያን ከተቀረው ዓለም ማስታረቅና የሕዝቡን አንድነት ማረጋገጥ ነው።

የተወለዱት እአአ በ1955 ሂራን ግዛት ነው። በሞቃዲሾ በመካከለኛው መደብ ሰፈር አድገው ከሶማሊያ ብሔራዊ ዩኒቨርስቲ በምህንድስና በ1981 ተመርቀዋል።

በቅርብ የሚያውቋቸው ዝምተኛና የማይታበዩ ሰው ናቸው ይሏቸዋል።

ሶማሊያ ለ30 ዓመታት በእርስ በእርስ ጦርነት ስትናጥ አገሪቱን ጥለው ካልሄዱ ጥቂት መሪዎች መካከልም አንዱ ናቸው።

ሁለተኛ ዲግሪ ከመሥራታቸው በፊት በሕንድ ቦሆፓል ዩኒቨርስቲ አስተማሪ ነበሩ።

ወደ ሶማሊያ ሲመለሱ በተባበሩት መንግሥታት የተዘረጋውን የመምህራን ሥልጠና ለመምራት በትምህርት ሚኒስቴር ተቀጠሩ።

በ1991 ማዕከላዊው መንግሥት ሲንኮታኮት፣ በዩኒሴፍ የትምህር ኃላፊ ሆነው ተቀጠሩ።

ከሦስት ዓመታት በኋላ፣ በሞቃዲሾ ጦርነቱ ከተነሳ ወዲህ ግንባር ቀደም ከሆኑ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አንዱን ከፈቱ።

የሙስሊም ወንድማማችነት (Muslim Brotherhood) የሶማሊያ ቅርንጫፍ የሆነው አል-ኢላህ ጋር ግንኙነት አላቸው።

የጎሳ ግጭት በተነሳበት ወቅት ለማኅበረሰቡ የትምህርት ሥርዓት በመዘርጋት ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል።

ቡድኑ ከግብፅና ሱዳን ጋር ተመሳሳይ በሆነ የእስልምና አስተምህሮት የሚተዳደር ትምህርት ቤቶች ከፍቷል።

እንደ አል-ሸባብ እና አል-ቃይዳ ያሉ አክራሪዎችንም ያወግዛል።

ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ "ለዘብተኛ ሙስሊም" ተብለው ይታወቃሉ።

በጦርነት የደቀቀችውን ሶማሊያ ለመደገፍ በንግድ ሰዎች የተቋቋመው 'ዩኒየን ኦፍ ኢስላሚክ ኮርትስ' ከተባለው ፍርድ ቤት ጋርም ትስስር አላቸው።

የአዲሱ ፕሬዝዳንት ደጋፊዎች እንደሚሉት፣ ሰላምና መረጋጋትን ለመመለስ የሚሠሩ መሪ ናቸው።

በ1990ዎቹ የሲቪል ማኅበራት ውስጥ ከፍተኛ ንቅናቄ ያደርጉ ነበር። የጎሳ ግጭትን በማርገብም ይታወቃሉ።

ሞቃዲሾን ለሁለት ሰንጥቆ በሁለት ተፎካካሪ ጎሳዎች እንድትመራ ያደረጋት "ግሪን ላየን" የተባለውን አካሄድ ለማፍረስ በተደረገው ድርድር ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል።

ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ ከፍተኛ ድርቅን ጨምሮ በበርካታ ችግሮች የተሸበበች አገር ነው ከፈርማጆ የሚረከቡት።

የተባበሩት መንግሥታት እንደሚለው፣ ድርቁ ካልተገታ ወደ ረሃብ ከፍ ሊል ይችላል።

ከ3.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በረሃብ አፋፍ ላይ ሆነው አፋጣኝ የምግብ እርዳታ ይጠብቃሉ።

ሶማሊያን የኑሮ ውድነትና የዩክሬን ጦርነት ያባባሰው የዋጋ ግሽበትም ይፈትናታል።

በፌደራል መንግሥቱና በክልሎች መካከል እየሰፋ ያለው ልዩነትም ሌላው የሐሰን ሼይክ ሞሐሙድ የቤት ሥራ ይሆናል።

ሙስና ሌላው የሶማሊያ ማነቆ ነው።

ተንታኞች እንደሚሉት አዲሱ ፕሬዝዳንት አገራቸው ከኬንያ፣ ጂቡቲ እና ከተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ጋር ያላትን ግንኙነት የማደስ ኃላፊነትም ተጥሎባቸዋል።

ሐሰን ሼክ ሞሐሙድ 2012 ላይ ሲመረጡ አገራቸው ከምዕራባውያን እና ከአፍሪካ አገራት ጋር መደበኛ የዲፕሎማሲ ትስስሯን እንድታድስ አስችለዋል።

በሌላ በኩል በአስተዳደራቸው ስር ያለውን ሙስና ማስወገድ አልቻሉም ተብለው ይታማሉ።