የአሜሪካ እና የሩሲያ የስለላ ኃላፊዎች በቱርክ ተገናኙ

የሲአይኤ ኃላፊ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአሜሪካ እና የሩሲያ የስለላ ኃላፊዎች ሞስኮ በዩክሬን ስለደቀነችው የኒውክሌር ስጋት እና በሩሲያ “በግፍ” ስለታሰሩ አሜሪካውያን እስረኞች ፊት ለፊት ተገናኝተው ተነጋገሩ።

የሲአይኤ ዳይሬክተር ዊሊያም በርንስ እና የሩሲያ አቻቸው ሰርጌይ ናሪሽኪን ሰኞ ዕለት በቱርክ ዋና ከተማ አንካራ ተገናኝተው ተወያይተዋል።

ክሬምሊን ውይይቶቹ "በአሜሪካ ወገን ተነሳሽነት" እንደተፈጸሙ ገልጻለች።

ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች በኋላ በባለሥልጣናት መካከል የተደረገ ከፍተኛ ኦፊሴላዊ ስብሰባ ነው።

እአአ ከ2005 እስከ 2008 በሩሲያ የአሜሪካ አምባሳደር የነበሩት እና ሩስኪ የሚናገሩት በርንስ በጦርነቱ ማብቃት ዙሪያ እየተደራደሩ አይደለም ሲል ዋይት ሃውስ ተናግሯል።

የኃላፊው መልዕክት "ሩሲያ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ መጠቀሟ የሚያስከትለውን መዘዝ" እና "ወደ ቀጣናዊ አለመረጋጋት ሊያድግ ይችላል" በሚለው ስጋት ዙሪያ መሆኑን ዋይት ሃውስ በመግለጫው ተናግሯል።

በቅርብ ወራት ሞስኮ በዩክሬን ታክቲካል የኒውክሌር ጦር መሳሪያ እንዳትጠቀም አሜሪካ ደጋግማ አስጠንቅቃለች። ከክሬምሊን በተገኘ ፍንጭ ይህንን ለማድረግ ፈቃደኛ እንደምትሆን ገልፃለች።

በመስከረም ወር የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ምዕራባውያን ሩሲያን ለማጥፋት እንደሚፈልጉ በመግለጽ ግዛቷን ለመጠበቅ "ሁሉንም መንገዶችን" እንደሚጠቀሙ አሳስበዋል። ይህም የኒውክሌር ጦር መሳሪያን ለመጠቀም እንደቀነ ስጋት ታይቷል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ዩናይትድ ስቴትስ ዛቻዎቹን በቁም ነገር እንደምትወስድ ተናግራለች።

በርንስ እና የሩሲያ የመረጃ አገልግሎት (ኤስቪአር) ኃላፊ ናሪሽኪን መገናኘታቸውን የቱርክ ፕሬዝዳንት ሬሲፕ ጣይብ ሄርዶጋን ቃል አቀባይ አረጋግጠዋል።

ከዩክሬን ወረራ በኋላ ቱርክ በሩሲያ እና በምዕራባውያን ሃገሮች መካከል ወሳኝ ድልድይ ሆና ብቅ ብላለች።

የዋይት ሀውስ መግለጫ አክሎም በርንስ "ምንም አይነት ድርድር እያካሄደ አይደለም" ሲል አፅንዖት ሰጥቷል። ዋሽንግተን "ዩክሬን በሌለችበት ስለ ዩክሬን ምንም ነገር አይከናወንም" በሚለው መሠረታዊ መርሆ ጸንታ ትቆያለች ብሏል።

ይህ የሆነው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ከቻይና አቻቸው ዢ ጂንፒንግ ጋር በባሊ ኢንዶኔዥያ ከሚካሄደው የቡድን 20 መሪዎች ስብሰባ በተገናኙበት ወቅት ነው።

የዋይት ሃውስ መግለጫ እንዳስታወቀው ሃገራቱ "በዩክሬን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ አጠቃቀምን ወይም ስጋትን መቃወማቸውን አጽንኦት ሰጥተዋል" ብሏል።

የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በመግለጫው ዢ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ መጠቀም እንደማያስፈልግ እና ወደ ኒውክሌር ጦርነቶችን መግባት እንደማያዋጣ ለባይደን ተናግረዋል ብሏል።

የአሜሪካ እና የሩስያን ስብሰባ አስመልክቶ የዋይት ሃውስ ያወጣው መግለጫ አክሎም ባለሥልጣናቱ በሩስያ "በግፍ" ስለታሰሩት የአሜሪካ ዜጎች ጉዳይ እየተወያዩ ነው ብሏል።

በነሐሴ ወር የአሜሪካ የቅርጫት ኳስ ኮከቧ ብሪትኒ ግሪነር የካናቢስ ዘይት በህገ ወጥ መንገድ በማዘዋወር እና በመያዝ የዘጠኝ ዓመት እስራት ተፈርዶባታል።

ሩሲያ ውስጥ ካናቢስ መጠቀም ሕገ-ወጥ ቢሆንም ሞስኮ ግሪነርን “እንደ ፖለቲካ መያዣ” ተጠቅማባታለች ተብሏል።

በሐምሌ ወር መገባደጃ ላይ የባይደን አስተዳደር ግሪነር እንድትፈታ እንዲሁም ሞስኮ በስለላ ወንጀል የከሰሰችው የቀድሞ የባህር ኃይል አባል ፖል ዌላንን ለማስፈታት ከሩሲያ ጋር እስረኛ ልውውጥ ለማድረግ ሀሳብ አቅርቧል።

በአሜሪካ የሩስያ አምባሳደር አናቶሊ አንቶኖቭ ማክሰኞ ከዋይት ሃውስ ባለስልጣናት ጋር በአሜሪካ እስር ቤቶች ስላሉ ሩሲያውያን አያያዝ እንደሚመክሩ የሩሲያ ኤምባሲ አስታውቋል።