የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ተሳታፊዎች ግጭቱን ከሚያባብስ ድርጊት እንዲቆጠቡ ብሊንከን ጠየቁ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ኃላፊ አንቶኒ ብሊንከን በሰሜን ኢትዮጵያ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ተሳታፊ የሆኑ ኃይሎች ግጭቱን የሚያባብሱ ድርጊቶችን እንዲያቆሙ ጥሪ አቀረቡ።
አንቶኒ ብሊንከን በትዊተር ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት መልዕክት የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግሥታት በትግራይ ውስጥ የሚያካሂዱትን “የጋራ ወታደራዊ ጥቃት” እንዲያቆሙ ጠይቀዋል።
በተጨማሪም በትግራይ ኃይሎች በኩልም “የጠብ አጫሪነት ተግባራትን” የክልሉ ባለሥልጣናት ከመፈጸም እንዲቆጠቡ የውጭ ጉዳይ ኃላፊው አሳስበዋል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫም ግጭቱ እየተባባሰ መሆኑን እና በሰው እና በንብረት ላይ የሚደርሰው ጉዳትን የሚያመለክቱ ሪፖርቶች መውጣታቸው በጥልቅ አሳስቧታል ብሏል። በተለይም የሽሬ አካባቢን በመጥቀስ ሰላማዊ ሰዎችን ያልለየ ጥቃትን በዋቢነት ጠቅሷል።
በነሐሴ ወር አጋማሽ ላይ በትግራይ ኃይሎች አማካይነት በአማራ ክልል ቆቦ አቅራቢያ የተካሄደው ዘመቻ ጦርነቱ እንዲባባስ ማድረጉን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ አመልክቷል።
ሁለት ዓመት ሊሞላው በተቃረበው በሰሜን ኢትዮጵያ በሚካሄደው ጦርነት ባለፈው ዓመት መጋቢት ወር ላይ የተደረገው የተኩስ አቁም፣ ነሐሴ ላይ ተደናቅፎ ጦርነት ከጀመረ በኋላ ውጊያዎች እየተካሄዱ መሆናቸው ይዘገባል።
ብሊንከን ጨምረውም የኢትዮጵያ መንግሥት እና የትግራይ ክልል ባለሥልጣናት ጦርነቱን ለማብቃት የሰላም መንገድን መከተል ያለባቸው አሁን ነው ብለዋል።
ለዚህም በአፍሪካ ኅብረት መሪነት የሚካሄድ የሰላም ንግግርን አሜሪካ እንደምትደግፍ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ኃላፊ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።
ከሁለት ሳምንታት በፊት የአፍሪካ ኅብረት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ሊያካሂደው አስቦት በነበረው የሰላም ንግግር ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት እና የትግራይ ኃይሎች እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርቦ፣ ሁለቱም ወገኖች ተሳታፊ ለመሆን ፈቃደኛ መሆናቸውን ገልጸው እንደነበር ይታወሳል።
ነገር ግን ምክንያቱ በግልጽ ባልተገለጸ ሁኔታ ንግግር ሊደረግበት የታሰበው ቀን ወደ ሌላ ጊዜ መተላለፉ ከመነገሩ ባሻገር፣ አሸማጋይ ይሆናሉ ከተባሉት ሦስት የቀድሞ አፍሪካውያን መሪዎች መካከል አንዱ የሆኑት የኬንያው የቀድሞ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ መሳተፍ እንደማይችሉ ገልጸዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት አምባሳደር ማይክ ሐመር አዲስ አበባ ውስጥ ከኢትዮጵያ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር ተገናኝተው መወያየታቸው ተነግሯል።
በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነት ሰላማዊ መቋጫ የሚያገኝበትን መንገድ ለማገዝ ከሳምንት በፊት ወደ አፍሪካ የመጡት አምባሳደር ሐመር በደቡብ አፍሪካ፣ በኬንያ እና በአዲስ አበባ ጉብኝት ላይ ናቸው።
የአሜሪካ መንግሥት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛው በጉዟቸው ከየአገራቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት እና መንግሥታዊ ካልሆኑ ተቋማት ተወካዮች ጋር እንደሚገናኙ ተገልጾ ነበር።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳሳወቀው አምባሳደር ሐመር አርብ ዕለት ከሚኒስትሩ አቶ ደመቀ መኮንን ጋር ጦርነቱን ለማብቃት ስለሚደረገው የሰላም ጥረት ተወያይተዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት ጦርነቱ በሰላማዊ መንገድ መፍትሄ እንዲያገኝ ለሚደረገው ጥረት ተባባሪ እና ዝግጁ መሆኑን አቶ ደመቀ የገለጹ ሲሆን፣ ሐመርም አሜሪካ በአፍሪካ ኅብረት ጥላ ሥር የሚደረገውን የሰላም ንግግር እንደምትደግፍ ማረጋገጣቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል።
ከቀናት በፊት አሜሪካንን ጨምሮ ስድስት ምዕራባውያን አገራት በሰሜን ኢትዮጵያ ተባብሶ የቀጠለው ግጭት እና ሰብአዊ ቀውስ በእጅጉ እንዳሳሰባቸው በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በኩል ባወጡት መግለጫ አሳውቀው ነበር።
አገራቱ ሁሉም ወገኖች ለግጭቱ ወታደራዊ መፍትሄ እንደማይኖረው ተገንዝበው፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ባለመው በአፍሪካ ኅብረት በሚመራው ንግግር ውስጥ እንዲሳተፉ ለኢትዮጵያ መንግሥት እና ለትግራይ ክልል ባለሥልጣናት ጥሪ አቅርበዋል።
በመጪው ጥቅምት 24/2015 ዓ. ም. ሁለት ዓመት የሚሞላው ጦርነት በአሥር ሺዎች ለሚቆጠሩ ሰዎች ሞት፣ ለመቶ ሺዎች መፈናቀል፣ ሚሊዮኖችን ደግሞ ሰብአዊ እርዳታ ጠባቂ ከማድረግ ባሻገር ከባድ ቁሳዊ ውድመትን ማስከተሉ ሲዘገብ ቆይቷል።












