ለኩባ ይሰልሉ የነበሩት የአሜሪካ ዲፕሎማት የ15 ዓመት እስር ተፈረደባቸው

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በአንድ ወቅት በቦሊቪያ የአሜሪካ አምባሳደር ሆነው ያገለገሉት ዲፕሎማት ለኩባ በመሰለል ወንጀል የ15 ዓመት እስር ተፈረደባቸው።
የ73 ዓመቱ ቪክቶር ማኑኤል ሮቻ ከ40 ዓመታት በላይ ለኩባ መንግሥት መረጃን በድብቅ ያስተላልፉ እንደነበርም አቃቤ ሕግ አስረድቷል።
በየካቲት ወር ላይ በማያሚ ፍርድ ቤት ቀርበው የነበሩት ማኑኤል ሮቻ ጥፋተኛ አይደለሁም የሚለውን ቃላቸውንም በመቀየር የፍርድ ሒደቱ እንዲቀር እና በስምምነት እንዲቋጭ አድርገዋል።
የረዥም ጊዜ ዲፕሎማት የነበሩት እኝህ ግለሰብ ለኩባ ይሰልሉ እንደነበር ይፋ መሆኑ በአገራቱ መካከል የነበረው ውዝግብ ከፍተኛው መገለጫ ነው ተብሏል።
ግራጫ የማረሚያ ቤት የደንብ ልብስ ለብሰው አርብ ዕለት የቀረቡት የቀድሞው ዲፕሎማት በማያሚ ለሚገኘው የፌደራል ፍርድ ቤት “ጥፋተኛ ነኝ” ብለዋል።
በዚህም ከእስር ቅጣት በተጨማሪም 500 ሺህ ዶላር ቅጣት መክፈል እና ከባለስልጣናት ጋር መተባበር ይጠበቅባቸዋል።
የአሜሪካ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ሜሪክ ጋርላንድ የቀድሞውን ዲፕሎማት ወንጀሎች “በውጭ ወኪል የአሜሪካ መንግሥት ላይ ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ እና ለረዠም ጊዜ የቆየ ሰርጎ ገብነት አንዱ ነው” ሲሉም ፈርጀውታል።
በኮሎምቢያ የተወለዱት ቪክቶር ማኑኤል ሮቻ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በዬል እና ሃርቫርድ ዩኒቨርስቲዎች ነው። በአውሮፓውያኑ 1999 – 2022 ባለው ወቅትም በቦሊቪያ የአሜሪካ አምባሳደር እንዲሁም በአርጀንቲና፣ በሆንዱራስ፣ በሜክሲኮ እና በዶሚኒካን ሪፐብሊክ በተለያዩ የዲፕሎማሲ ሥራዎች ላይ አገልግለዋል።
የአሜሪካ ብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤትን ጨምሮ በተለያዩ የመንግሥት ኃላፊነቶችም አገልግለዋል።
የዲፕሎማትነታቸው አገልግሎት ካበቃ በኋላም ማኑኤል ሮቻ ኩባን ጨምሮ ላቲን አሜሪካ እና ካሪቢያንን በበላይነት ለሚያየው የአሜሪካ ጦር ደቡባዊ ዕዝ አማካሪ ሆነው አገልግለዋል።
በአውሮፓውያኑ 2022 የአሜሪካ የፌደራሉ ምርመራ ቢሮ፣ ኤፍቢአይ ወኪል ማንነቱን ደብቆ ለኩባ የስለላ አገልግሎት ወኪል እየሰራ መሆኑን ለማኑኤል ሮቻ በዋትስ አፕ እንደገለጸላቸውና የኤፍቢአይ ወኪሉ “በሃቫና ካሉ ጓደኞችህ” መልእከት አለኝ ሲል ለቀድሞው ዲፕሎማቱ መናገሩን በፍርድ ቤት ሰነዱ ተመላክቷል።
ከማኑኤል ሮቻ ጋር በነበሩ ሦስት ተከታታይ ስብሰባዎችም የቀድሞው ዲፕሎማት ለኩባ እንዴት ይሰልሉ እንደነበር ዝርዝር መረጃዎችን አጋርተዋል። በአንድ ወቅት ማኑኤል ሮቻ ኩባን እና ራሱን ለመግለጽ “እኛ” የሚለውን ቃል የተጠቀሙ ሲሆን “እኛ በጋራ የፈጸምነውን እንከላከላለን” በማለት ቃል ገብተዋል።
አሁንም “ከእኛ [ኩባ] ጋር ነህ ወይ? ተብለው” በኤፍቢአይ ወኪሉም ሲጠየቁ “ለኩባ መንግሥት ያለው ታማኝነት ጥያቄ ውስጥ መግባቱ አናዶኛል። ወንድነቴ ላይ ጥያቄ እንደማንሳት ነው” ማለታቸውም ተጠቅሷል።
በአውሮፓውያኑ 1959 ፊደል ካስትሮ በኩባ ደሴት ላይ አብዮት በማስነሳት አሜሪካ የምትደግፈውን መንግሥት ማስወገዳቸውን ተከትሎ አሜሪካ ጋር የነበራቸው ግንኙነት ተካረረ። አሜሪካም በኩባ ላይ ከፍተኛ ማዕቀብ ጥላባት ቆይታለች።












