ከፍተኛ ገንዘብ እያስከፈለ የሴቶችን መቀመጫ የሚያሳድግ አደገኛ መርፌ የሚወጋው ግለሰብ

ሪክ ሶውዬር
የምስሉ መግለጫ, በርካታ ሴቶችን ለውስብስብ እና አደገኛ የጤና እግር የዳረገው ሪክ ሶውዬር ራሱን "በብሪታኒያ ድንቁ የቢቢኤል ዶክተር" ሲል ይጠራል

ራሱን "የውበት አማካሪ" ሲል የሚጠራው 'የታዋቂ ሰዎች ዶክተር' ለደንበኞቹ አደገኛ የሆነ የኮስሜቲክስ መድኃነት በሕገ ወጥ መንገድ እንደሚሰጥ የቢቢሲ ምርመራ አጋለጠ።

ሪኪ ሶውየር የተባለው ግለሰብ 'ብራዚሊያን በት ሊፍት' (ቢቢኤል) የተባለውን የሴቶች የመቀመጫ መጠንን የሚያሳድግ መድኃኒት በመርፌ በመስጠት ይታወቃል።

ቢቢሲ አምስት ደንኞቹን ያናገረ ሲሆን፣ እኒህ ደንበኞች መርፌ ከተወጉ በኋላ ባጋጠማቸው ህመም ምክንያት ሆስፒታል የገቡ ናቸው። ሌሎች 30 ሴቶች ደግሞ ሴፕሲስ እና ኔክሮሲስ የተባሉ ከባድ የጤና እክሎች እንዳጋጠመቻው ቢቢሲ ተረድቷል።

አንዲት ሴት ግለሰቡ በሰጣት ሕክምና ምክንያት ያጋጠማትን ህመም እያስታወሰች "ከስቃዩ ሞት ይሻለኛል" ስትል መቀመጫን ለማሳደግ ያደረገችው "ሕክምና" ያስከተለባትን ስቃይ ጠቅሳለች።

በርካታ የብራዚል ባለሥጣናት ሶውዬር የተባለው ግለሰብ በአካካቢያቸው ይህንን የጤና ጠንቅ የሆነን ሕክምና እንዳይሰጥ አግደውታል።

ቢቢሲ በድብቅ የቀረፀው ቪድዮ ሰውዬው ትክክለኛ ባልሆነ የሕክምና መመሪያ አንቲባዮቲክስ (ፀረ ተህዋሲ መድኃኒት) ሲሰጥ ያሳያል። ይህን ማድረግ ወንጀል ነው። በተጨማሪም ግለሰቡ መድኃኒት ለማዘዝ የሚያስችው የሕክምና ፈቃድ ያለው አይደለም።

ቢቢሲ አድራሻውን ከኢንስታግራም ገፅ እንዳገኘ በመምሰል ቢቢኤል የተባለውን ሕክምና ለማግኘት 200 ፓውንድ ቀብድ ከፍሎ ቀርቦታል። የሕክምናው ሙሉ ዋጋ 1200 ፓውንድ ነው፤ ይህም በብር ሲሰላ ከ1.9 ሚሊዮን ብር በላይ ነው።

ምንም እንኳ ይህ የሴቶችን መቀመጫ የሚያሳድገው ሕክምና "በሙያው የዳበረ ዕውቀት እና ልምድ ባላቸው ዶክተሮች" ይሰጣል ተብሎ ቢተዋወቅም፣ ክሊኒኩ ውስጥ አንድም ሰው አልነበረም። አነስተኛው ክሊኒክ የሚገኘው ምሥራቅ ለንደን ውስጥ ነው።

ግለሰቡ የቢቢሲን ሪፖርተር "ለምን 2000 ሺህ ፓወንድ ከፍለሽ 500 ሚሊ ሊትር አትወጊም" እያለ ሲጎተጉታት ይታያል። በኋላ ሪፖርተሯ መወጋት እንደማትፈልግ እና የምርመራ ሥራ ላይ እንደሆነች ስታሳውቀው እንድትወጣለት ጠይቆ በሩን ዘግቶታል።

የቢቢሲን ቪድዮ የመረመሩት የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ባለሙያው ዳልቪ ሁምዛህ ያዩት ነገር "እጅግ እንዳስደነገጣቸው" ተናግረው፤ ሰውዬው የሚፈፅመውን ነገር "በጣም አደገኛ ነው" ብለዋል።

የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ባለሙያው ዳልቪ ሁምዛህ
የምስሉ መግለጫ, የፕላስቲክ ቀዶ ሕክምና ባለሙያው ዳልቪ ሁምዛህ የግለሰቡ ድርጊት "አደገኛ ነው" ይላሉ

ቢቢኤል ለተሰኘው ሕክምና የሚሰጠው አሲድ ለፊት ቀዶ ሕክምናም የሚውል ነው። ይህ አሲድ በብዛት ሲወጋ ጤና ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ ከማሳደር አልፎ ለደም መርጋት እና ለሌላም ውስብስብ የጤና እክል ያጋልጣል።

ሶውዬር በቀን ለሰባት ሰዎች ሕክምና ሊሰጥ እንደሚችል እና በሳምንት ስድስት ቀናት እንደሚሠራ በኩራት ሲናገር በቪድዮ ተቀርጿል። በዚህም የተነሳ ደንበኞቹ በሺዎች የሚቆጠር ፓውንድ ይከፍሉታል።

ከደንበኞቹ መካከል አንዷ የሆነው ጆዋን ቢቢኤል የተሰኘውን ሕክምና እንዳገኘች ትናገራለች። የዌስል ነዋሪዋ ጆዋን የሁለት ልጆች እናት ናት። ለሕክምና ስትል ሰዓታት የፈጀ ጉዞ አድርጋ ነው የመጣችው።

መቀመጫዋ እንዲያደግ በመመኘት ያደረገችው ሕክምና አሁን ይቆጫታል። በጠቅላላው 2 ሺህ ፓውንድ ከፍላ አንድ ሊትር ፈሳሽ ተወግታለች። ነገር ግን ከሕክምናው በኋላ ያጋጠማትን ህመም ልትቋቋመው አልቻለችም።

የመቀመጫዋን መጠን ከፍ ለማድረግ ስትል ብዙ ገንዘብ ከፍላ "በሕክምናውን" ሂደት ውስጥ ካለፈች በኋላ ያጋጠማት ያልጠበቀችው ነገር ነበር። ጆዋን በጣም ከባድ ስቃይ እንደነበረባት እና መቀመጥ እንኳ እንዳቃታት ታስታውሳለች። ቤቷ ስትደርስ መራመድ ሁላ አቅቷት እንደነበርም አትዘነጋም።

ጆዋን
የምስሉ መግለጫ, ጆዋን መቀመጫ የሚያሳድገውን መርፌ ከተወጋች በኋላ ከባድ ህመም እንዳጋጠማት ትናገራለች

ለግለሰቡ በተደጋጋሚ ስትደውልለት መፍትሄ የሚሆን ነገር በራሱ በኩል ከማድረግ ይልቅ "አንቲባዮቲክስ ውሰጂ" የሚል ምላሽ ነበር የሚሰጣት። ይሄን ጊዜ በሰውነቷ ውስጥ ኢንፌክሽን ተፈጥሮ በመስፋፋት ውስብስብ እና አደገኛ ወደ ሆነ ደረጃ ላይ እደረሰ ሄደ።

ጆዋን ወደ ሆስፒታል አቅንታ ሕክምና ከተደረገላት በኋላ ለጤናዋ መቃወስ ምክንያት የሆነውን መቀመጫን የሚያሳድ "ሕክምናውን" ያደረገላትን ሪኪ ሶውዬር ለሚባለው መልዕክት ስትልክለት ኢንስታግራም ገፁ ላይ 'ብሎክ' እንዳደረጋት ትናገራለች።

እንደመታደል ሆኖ ጆዋን የቀዶ ሕክምና ሳያስፈልጋት ልታገግም ችላለች።

ሌላኛዋ ደንበኛው የነበረችው ሉዊዝ ሞለር ናት። የ28 ዓመቷ ሞለር መርፌውን ከተወጋች ከአምስት ቀናት በኋላ ነው ራሷን ሆስፒታል ውስጥ ያገኘችው። ለእናቷ ደውላ "ልሞት ነው መሰል" ብላ እንደነገረቻት ታስታውሳለች።

ሉዊዝም እንደ ጆዋን ከባድ ኢንፌክሽን አጋጥሟት ነበር። ዶክተሮችም በገጠማት ችግር ምክንያት ሕይወጠወን ጭምር ልታጣ እንደምትችል አስጠንቀቅዋታል። በሽታው እንዳይስፋፋ በማለት ከግራ መቀመጫዋ የሞቱ ሴሎችን ቆርጠው አስወግደዋል።

ሉዊዝ ሞለር

የፎቶው ባለመብት, Janet Taylor

የምስሉ መግለጫ, ሉዊዝ ሞለር መርፌውን ከተወጋች ከአምስት ቀናት በኋላ ነው ሆስፒታል የገባችው

የሉዊዝ እናት ሰውዬው "ሰው ሊሞት እንደሚችል እያወቀ እንዴት ነው እንዲህ የሚያደርገው" ስትል ትጠይቃለች። ግለሰቡን ለፍርድ ለማቅረብ ያደረገችው ጉዞ ስኬታማ አልነበረም።

ለፖሊስ ሪፖርት ስታደርግ ልጇ ሉዊዝ ሕክምናውን በፈቃዷ እንዳደረገችው የሚገልጽ ቅፅ ላይ በመፈረሟ ክሷ የትም እንደማይደርስ ነው የተነገራት።

ዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ ሰውነት ውስጥ የሚሞሉ ፈሳሾችን መውጋት የቀዶ ሕክምና ሳላልሆነ የሚቆጣጠረውም አካል የለም።

ባለፈው መስከረም አሊስ ዌብ የተባለችው ግለሰብ በቢቢኤል ምክንያት ሕይወቷ ማለፉ ተሰምቷል። ይህም በዩናይትድ ኪንግደም የመጀመሪያዋ ሴት አድርጓታል።

የአሊስን ሞት ተከትሎ በርካታ ተቋማት ቀዶ ሕክምና የሌለባቸው ሕክምናዎች በተለይ ለውበት ሲባል የሚከናወኑ ሕክምናዎች የተሻለ ቁጥጥር እንዲደረግባቸው መጠየቅ ጀምረዋል።