ብቸኛ ለሆኑ ሰዎች እፎይታን የሚሰጡት የደቡብ ኮሪያ መደብሮች

ሴዑል ከተማ እግረኛ መንገድ ላይ ምልክት የያዘች ሴት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, እያደገ የመጣውን ብቸኝነትን ለመዋጋት ተልዕኮ በያዘችው ሴዑል ከተማ ታዋቂ የእግረኛ መንገድ ላይ 'ማምለጫ ክፍል በግማሽ ክፍያ' የሚል ምልክት ይታያል

ደቡብ ኮሪያ የተጓዘችበት ለውጥ ግልብጥብጥ እንድትል አድርጓታል።

ትውልዱ በጦርነት ከተመሰቃቀለ ግብርና መር ማኅበረሰብ ወደ በለፀገች አገር ዜጋነት ተቀይሯል።

ከጥቂት አስርት ዓመታት በፊት ከስድስት እስከ ስምንት ልጆች ያለው ሰፊ ቤተሰብ በአንድ ቤት ውስጥ መኖሩ የተለመደ ነበር።

ይኹን እንጂ ለዓመታት ወደ ከተሞች የሚደረግ ፍልሰት ቤተሰቦች እንዲመናመኑ እና እንደ ዋና ከተማዋ ሴዑል ያሉ ከተሞች ደግሞ በሕዝብ ብዛት እንዲጨናነቁ አድርጓል።

የማይቀመስ የቤት ዋጋ፣ የኑሮ ውድነት እና አድካሚ የሥራ ሰዓታት በርካታ ወጣቶች ትዳር እና ቤተሰብ ምሥረታን አሽቀጥረው እንዲጥሉ አድርጓል።

በሌላ በኩል ለዕለት ከዕለት ሕይወት እየተዋደቁ ባሉ ልጆቻቸው ችላ የተባሉ አዛውንቶች ያለ ተመልካች ቀርተዋል።

ሔ-ኪዩንግ በሴዑል አዲስ ወደ ተከፈተው ልብ አሟቂ መደብር እግሯ ሲረግጥ ፈገግ እያለች ነው።

የ29 ዓመቷ ሔ-ኪዩንግ ምናልባትም በደቡብ ኮሪያ መዲና ብቸኝነትን ለመፋለም አዲስ ጥረት በሆነው እንቅስቃሴ ለመጠቀም የምትገመት አይደለችም። ምክንያቱም አፍላ ወጣት መሆኗ ነው።

ነገር ግን ሔ-ኪዩንግ በየቀኑ ወደ መደብሩ ጎራ እያለች በነፃ የሚሰጠውን ፈጣን ምግብ 'ኑድልስ' በመያዝ ሰዓታትን ከሌሎች ጎብኚዎች እና የማኅበራዊ ጉዳይ ሠራተኞች ጋር ትጫወታለች።

"ለራሴ 'ሌላ ቀን፤ ከብቸኝነት ስሜት ለማምለጥ ሌላ መላ' እያልኩ እነግረዋለሁ" ትላለች ሔ-ኪዩንግ።

በአስራዎቹ ዕድሜዋ ላይ ሳለች ቤተሰቦቿን ጥላ በመጥፋቷ ከዘመዶቿ ምንም ዓይነት ግንኙነት የላትም። ጓደኞቿም ቢሆኑ በኬ-ፓፕ የሙዚቃ ቡድን 'ሱፐር ጁኒየር' ወዳጅነታቸው በበይነ መረብ የተዋወቀቻቸው ናቸው፤ እናም በቅርብ አይኖሩም።

አሁን ላይ ሥራ ላይ ባለመሆኗም የምታወራቸው የሥራ ባልደረቦች የሏትም።

ብቻዋን ነው የምትኖረው። አብዛኛውን ጊዜዋንም መሬት ላይ ተኝታ በእጅ ስልኳ የእንስሳት ቪዲዮዎችን እየተመለከተች ታሳልፋለች።

"ወደ መደብሮቹ ካልሆነ ሌላ የምሄድበት ምንም ቦታ የለኝም።"

ሔ-ኪዩንግ ባለፈው መጋቢት ወር የተከፈቱትን አራት መደብሮች ከጎበኙ ከ20 ሺህ ሰዎች መካከል አንዷ ናት።

መደብሩ ውስጥ ሰዎች ቁጭ ብለው ፊልም ሲያዩ
የምስሉ መግለጫ, የመኖሪያ ቤት ሳሎን የሚስለው መደብሩ ለሰዎች ምቾትን እና ባለሙያዎችን ያቀርባል
Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ሴዑል መደበሮቹ በተከፈቱ በመጀመሪያው ዓመት፣ አምስት ሺህ ሰዎችን ብቻ ጠብቃ ነበር።

በከተማዋ ሰሜን ምሥራቅ ክፍል ዶንጋዱሙን የተከፈተው ይህ መደብር በየቀኑ ከ70 እስከ 80 ሰዎች ይጎበኙታል።

አብዛኞቹ ጎብኚዎች በ40ዎቹ እና በ50ዎቹ ዕድሜ የሚገኙ ናቸው። ነገር ግን ሔ-ኪዩንግ የመደብሩን አገልግሎት ለማግኘት ጎራ የምትል ብቸኛዋ ወጣት አይደለችም።

በአውሮፓውያኑ 2022 የተደረገ ጥናት ይፋ እንዳደረገው በሴዑል ከ19 እስከ 39 ዓመት የሚገኙ 130 ሺህ የሚሆኑ ወጣቶች ከማኅበረሰቡ የተገለሉ አሊያም ራሳቸውን ያገለሉ ናቸው።

ይህ ጥናት በላጤነት የሚመሩ ቤቶች በመዲናዋ 40 በመቶ መድረሳቸውንም ይፋ አድርጓል።

ይህም እያሽቆለቆለ ባለው የውልደት እና የጋብቻ ምጣኔ ላሳሰበው የአገሬው መንግሥት ሌላ ራስ ምታት ሆኗል።

ቢቢሲ መደበሮቹን ሲቃኝ በርካታ ጎብኚዎች ሴት፣ ወንድ፤ ወጣት፣ ሽማግሌ አግዳሚ ወንበሮች ላይ ተቀምጠው በጋራ ፊልም እየተመለከቱ ነበር።

የሴዑል የብቸኝነት መከላከያ ክፍል ኃላፊ ኪም ሴ-ሆን "ትስስርን በዝቅተኛ ደረጃ ለማበረታታት የፊልም ቀን አለን" ይላሉ።

መደብሮቹ ካፌ የመሰለ ከባቢ ያላቸው ልብን ለማሞቅ ታስበው የተነደፉ ናቸው።

በአንድ ጥግ በኩል አንዲት በዕድሜዋ የገፋች ሴት ዓይኗን ገርበብ አድርጋ የማሳጅ ወንበሩ ላይ ተቀምጣለች። በሌላ ጥግ የአገሪቱ መለያ የሆነው 'ኑድልስ' ተደርድሮ ይታያል።

"'ራመን' በደቡብ ኮሪያ የምቾቶች እና የደስታ ምልክት ነው" ሲሉ ኪም ያብራራሉ።

ኑድል ፓስታው እስኪደርስ ድረስ ጎብኚዎች ስላሉበት ሁኔታ እና አኗኗራቸው አጭር ዳሰሳ እንዲሞሉ ይደረጋል።

እነዚህ ሰዎች ሴዑል ለመድረስ የምትፈልጋቸው እና ቁጥራቸው እያደገ ከመጣው ከማኅበራዊ ሕይወት ገለልተኛ ከሆኑት መካከል ጥቂቶቹ ናቸው።

በአንድ መደብር አማካሪ የሆነችው ሊ ኢን-ሶክ "ጣፋጭ ያልሆነው ምግብ ብቻህን የምትመገበው ነው የሚለውን አባባል ታውቀዋለህ? የሚመጡ አዛውንቶች ምግብ በደንብ እየበሉ እንደሆነ እጠይቃለሁ።ጥያቄውን ብቻ በመጠየቃቸው እንባቸው ያቀራል" ትላለች።

ከተፋታች እና ያደጉት ልጆቿ የራሳቸውን ሕይወት ለመገንባት ከቤት ከወጡ በኋላ ብቸኝነት ምን ዓይነት ስሜት እንዳለው በደንብ ትረዳለች።

ከኢን-ሶክ ሴት ልጅ ጋር ተቀራራቢ ዕድሜ ያላት ሔ-ኪያንግ ወደ መደብሩ ጎራ እንዳለች ወዲያው አስተውላታለች።

ሊ ኢን-ሱክ ለካሜራው ፈገግ ብላ
የምስሉ መግለጫ, ሊ ኢን-ሱክ በአንደኛው መደብር አማካሪ ሆና ታገለግላለች

እንደ አብዛኞቹ ጎብኚዎች ሔ-ኪያንግ በመጀመሪያ ቀኗ ዝምታን መርጣለች፤ ሌሎችን ለማነጋገር አልደፈረችም። ለሁለተኛ ጊዜ ስትመጣ ግን ኢን-ሱክን ማነጋገር ጀመረች።

የሴዑልን ሹማምንት ያሳሰባቸው እና እርምጃ እንዲወስዱ የገፋቸው ቁጥሩ እያደገ የመጣው "የብቸኝነት ሞት" ነው።

አረጋዊያን ብቻቸውን በተቆራመዱበት ቤት ሞተው፣ አስከሬናቸው ከቀናት አሊያም ከሳምንታት በኋላ ይገኛል።

ተልዕኮው ወዲያው ሰፋ ብሎ ብቸኝነትን ራሱን መታገል ላይ አተኮረ። ነገር ግን ሴዑል እንዲህ ዓይነት መላ ስትፈልግ የመጀመሪያዋ አይደለችም።

በአውሮፓውያኑ 2018 ዩናይትድ ኪንግደም የብቸኝነት ሚኒስትር ሾማለች።

ጃፓን ደግሞ ይህን ፈለግ በመከተል ችግሩን ለመቅረፍ በተለይ በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት በዋናነት የሥራ ኤጄንሲ መሥርታለች።

ከማኅበረሰቡ ሙሉ ለሙሉ መነጠል በጃፓን በጣም የተለመደ ክስተት ከመሆኑ የተነሳ 'ሂኪኮሞሪ' የሚል ስም አለው።

በደቡብ ኮሪያም ቁጥራቸው እያደገ የመጣ ወጣቶች በፍላጎታቸው በጣም ውድድር ከበዛበት ማኅበረሰብ ራሳቸውን እያገለሉ ነው።

በሴዑል የፀረ-ብቸኝነት መርሃ ግብር ከሚመሩ ኃላፊዎች መካከል የሆኑት ሊ ይ-ጆንግ "ምንአልባት እዚህ ያደረሰን ወረርሽኙ ሊሆን ይችላል" ይላሉ።

ልጆቻቸው ጓደኞቻቸው ለመጠየቅ ቤታቸው ሲመጡ እንኳ ስልኮቻቸው ላይ አንገታቸውን እንደሚቀብሩ ይገልፃሉ።

"አሁን አሁን ሰዎች ጓደኞች ለመተዋወቅ እንዴት ከባድ እንደሆነ ይናገራሉ። እንደ ማኅበረሰብ ብቸኝነት ልንቀርፈው የሚገባ ጉዳይ ሆኗል" ይላሉ።

ስልካቸው ላይ ያቀረቁ ሰዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከዕለት ወደ ዕለት ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣው ደቡብ ኮሪያውያን ከማኅበረሰቡ የተገለሉ እንደሆነ ጥናት ያመላክታል

የመጀመሪያው እርምጃ ማውራት ለሚፈልጉ ሰዎች ነፃ የስልክ መስመር መዘርጋት ነበር።

በ2023 በመላው አገሪቱ በየተደረገ ጥናት አንድ ሦስተኛ የሆኑ የኮሪያ አዋቂዎች እርዳታ የሚጠይቁት አሊያም ሐዘን ሲሰማቸው የሚያነጋግሩት ሰው እንደሌላቸው ይፋ አድርጓል።

አማካሪዎች በየትኛውም አርዕስት ላይ ለመነጋገር ለ40 ደቂቃ የስልክ ልውውጥ ይሰጣሉ።

ፓርክ ሰንግ-አህ ከቢሮዋ በቀን ሦስት ጊዜ ስልክ ትደውላለች።

"በርካታ ወጣቶች እነዚህን ውይይቶች እንደሚፈልጉ ሳይ ተገረምኩ። በሆዳቸው ያመቁትን ሸክም ማጋራት ይፈልጋሉ። ነገር ግን በወላጆች አሊያም በጓደኝነት በአመዛኙ የኃይል ሚዛን አለ። ስለዚህ ወደ እኛ ይመጣሉ"።

ከዚያም "ልብ አሟቂ መደብሮች" ተከትለው ብቅ አሉ። ለብቸኛ ሰዎች የሚዳሰሱ፣ የሚጨበጡ ስፍራዎች ሆኑ።

በዶንግዳሙን መደብር ለመክፈት የተፈለገው በአነስተኛ ገቢ የሚተዳደሩ ሰዎች በአቅራቢያው በመኖራቸው ነው። በዚህ አካባቢ ነዋሪዎች በጠባብ እና የተከፋፈሉ አፓርትመንቶች ለብቻቸው ይኖራሉ።

የ68 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ሶህን ፊልም ለማየት እና ጠባብ ቤታቸውን ለማምለጥ በሳምንት አንድ ጊዜ ይመጣሉ።

"[መደብሩ] ከመወለዴ በፊት መከፈት ነበረበት። ሁለት፤ ሦስት ሰዓት እንኳ ማሳለፍ ጥሩ ነው" ይላሉ።

ሶህን ከአምስት አስርት ዓመታት በላይ የአልጋ ቁራኛ የሆኑትን እናታቸውን በመንከባከብ አሳልፈዋል። በዚህም ምክንያት ትዳር አልመሠረቱም፤ ልጆችም አላፈሩም።

እናታቸው ሲያርፉ ዋጋ እንደከፈሉ ግልፅ ሆነላቸው፤ብቻቸውን ቀሩ።

እርሳቸውም የአንጎል ሕመምተኛ ሲሆኑ ባዶ ኪሳቸውን ከዘራቸውን ይዘው ሲጓዙ ቢውሉ ለእርሳቸው የሚሆን ምንም ስፋራ አለማግኘታቸውን ይናገራሉ።

"ቦታዎች ገንዘብ ይጠይቃሉ፤ ወደ ሲኒማ ቤት መሄድ ገንዘብ ያስከፍላል" ይላሉ።

ሁለት አረጋዊያን እየተጫወቱ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, አብዛኞቹ የደቡብ ኮሪያ አረጋዊያን ብቸኝነት እንደሚሰማቸው ሪፖርቶች ያመላክታሉ

መደብሮቹ በዋናነት የተከፈቱት ሌላ መሄጃ ለሌላቸው ሰዎች ማረፊያ እንዲሆኑ በማሰብ መሆኑን የመደብሩ አስተዳዳሪ ሊ ቦ-ሂዩን ይናገራሉ።

ፊልም ከማሳየት በላይ በሞቃታማ ወራት ኪስ ላጠራቸው ሰዎች የአየር ማቀዝቀዣ ያቀርባሉ።

ከዚህም በላይ መደብሮቹ እርዳታ ለመጠየቅ መገለልን ለሚፈሩ ብቸኛ የሆኑ ሰዎች እፎይታ የሚሰጡ ስፍራዎች ናቸው።

"ምቹ መደብር" በሚል የተሰጣቸው ስም ሆን ተብሎ ሲሆን፤ በአገሪቱ በተለይ በአረጋዊያን የማኅበረሰብ ክፍል መጥፎ ስም ከሚሰጠው የአዕምሮ ክሊኒክ ራቅ ለማድረግ ታስቦ ነው።

እንዲህም ሆኖ ታዲያ ለመጀመሪያ ጊዜ እግራቸው ደጁን ሲረግጥ ከመገለል ሕይወታቸው ጋር ተዳምሮ ቁጥብነት ይታይባቸዋል።

የመደብሩ ኃላፊ ጎብኚዎች በመጀመሪያ ሌሎች ሰዎችን ለማነጋገርም ሆነ አብረው ለመመገብ ምቾት እንደሚነሳቸው ይገልፃሉ።

"ብቸኝነቱ ለቀናት፣ለወራት እና ለግማሽ ዓመት የሚደጋገም ከሆነ ከስሜት በላይ ነው" ሲሉ ሊ ያብራራሉ።

"ሰዎች ካሉባቸው ስፋራዎች ራሳቸውን ያርቃሉ። ስለዚህ በርካታ ሰዎች ምግቡን ይዘው ለመሄድ ይጠይቁናል። ምክንያቱም ከሌሎች ሰዎች ጋር መመገብ አይፈልጉም"።

ኃላፊዎች ማውራት እንደማይጠበቅባቸው እና በአንድ ጠረጴዛ ቁጭ ብለው ምግባቸውን መመገብ እንደሚችሉ ያስረዷቸዋል።

ሔ-ኪዩንግ ዝምተኛዋ እና አዲሷ ጎብኚ ከሆነች አሁን ወራት አልፈዋል።

እና ለውጥ አለው? የመደብሩ አማካሪ ኢን- ሱክ ከአገር ውስጥ ጋዜጣ ጋር ቃለ ምልልስ እያደረገች ሳለች በመሀል ልጇ ተነሳች። በድንገት የተደበደበች ያህል ደርቃ ቀረች፤ ድምጿ ተቆራረጠ።

ሔ-ኪዩንግ "ላቅፍሽ ነው" አለቻት።

ከመደብሩ አንድ ክፍል ሌላኛው ጥግ መጥታ እጆቿን ዘርግታ ኢን-ሱክን እንደ እናቷ አቀፈች።