የሱዳኑ አርኤስኤፍ ለተኩስ አቁም በተስማማ በማግስቱ በመዲናዋ የድሮን ጥቃት መፈጸሙ ተዘገበ

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የሱዳኑ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) የሰብአዊ ተኩስ አቁም ለማድረግ እንደሚስማማ ከገለጸ ከአንድ ቀን በኋላ በአገሪቱ ዋና ከተማ ኻርቱም የፍንዳታ ድምጽ ተሰማ።
የሱዳን ጦር በሚቆጣጠራት ኻርቱም የሚገኙ ነዋሪዎች ሌሊት ላይ የድሮን እና የፍንዳታ ድምጽ ሰምተው ከእንቅልፍ መንቃታቸውን ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ ተናግረዋል።
የሐሙስ ሌሊቱ ፍንዳታ ወታደራዊ ካምፕ እና የኃይል ጣቢያ አቅራቢያ የተፈጸመ እንደሚመስል ነዋሪዎች ገልጸዋል።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ስለ ጉዳዩ አስተያየት አልሰጠም። የሱዳን ጦር በበኩሉ፤ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ የተኩስ አቁሙን "አለማክበሩን" በመጥቀስ የተኩስ አቁም ስምምነት ለመፈጸም እንደሚቸገር አስታውቋል።
ሁለቱ ኃይሎች ከሚያዝያ 2015 ዓ. ም. ጀምሮ እያካሄዱት ባሉት ደም አፋሳሽ የእርስ በእርስ ጦርነት ምክንያት ቢያንስ 150,000 ሰዎች ተገድለዋል። ከ12 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ደግሞ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል።
በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፍ የረሃብ ክትትል ቡድል በውጊያ ቀጣናዎች ውስጥ ጠኔ እየተንሰራፋ መሆኑን በዚህ ሳምንት አረጋግጧል።
አዲስ የድሮን እንቅስቃሴ የተሰማው ኻርቱም ከተማ ውስጥ ብቻ አልነበረም። ከከተማዋ በሰሜናዊ አቅጣጫ 300 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በምትገኘው እና በሱዳን ጦር ቁጥጥር ሥር ባለችው አትባራ ከተማም ተመሳሳይ እንቅስቃሴ ተስተውሏል።
አንድ ነዋሪ፤ "ጸረ አውሮፕላን መከላከያዎች መትተው ጥለዋል። ግን በከተማው ምሥራቃዊ ክፍል እሳት ሲነሳ ተመልክቻለሁ፣ የፍንዳታ ድምጽም ሰምቻለሁ" ሲሉ ለኤኤፍፒ ተናግረዋል።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በአሜሪካ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች፣ ሳውዲ አረቢያ እና ግብጽ የቀረበውን የሰብአዊ ተኩስ አቁም ለመቀበል መስማማቱን የገለጸው የአሁኑን ጥቃት ከመፈጸሙ አንድ ቀን አስቀድሞ ነበር።
አራቱ አገራት ይህንን ዕቅድ ያቀረቡት መስከረም ላይ ነበር። በዕቅዱ መሠረት የተኩስ አቁሙ በሒደት ወደ ቋሚ የተኩስ አቁም የሚለወጥ ሲሆን ቀጥሎም ወደ የሲቪሊያን አስተዳደር ምሥረታ ይሸጋገራል።
የሱዳን መንግሥት "የውጭ ጣልቃ ገብነት" እንደሆነ በመግለጽ ይህንን ዕቅድ ውድቅ አድርጎት ነበር።
የአገሪቱን ጦር "በውጭ ቅጥረኛ ወታደሮች ላይ ከሚተማመን ዘረኛ ሽብርተኛ ታጣቂ ቡድን" እኩል አደርጎ ለማቅረብ የሚደረግ ማንኛውንም ሙከራ እንደሚቃወምም አስታውቆ ነበር።
የአገሪቱ ጦር ይህንን አቋሙን ከገለጸ በኋላ የስምምነት ዕቅዱ ተቀይሮ እንደሆን ግልጽ አይደለም።
ይሁን እንጂ በደቡብ አፍሪካ የሚገኙት የሱዳን አምባሳደር፤ አገራቸው ዕቅዱን ለመቀበል ጊዜው ገና መሆኑን አርብ ዕለት በተካሄደ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል።
አምባሳደሩ ኦስማን አቡፋቲማ አዳም መሐመድ፤ "በጦርነቱ መጀመሪያ ላይ ብዙ የተኩስ ማቆም ስምምነቶች ነበሩን። ነገር ግን ከልምዳችን እንደምንረዳው [ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ለስምምነቶቹ] ምንም ዓይነት ክብር አልነበረውም" ብለዋል።
"የተኩስ አቁም ስምምነቶቹን የሚጠቀሙባቸው ወደ አዲስ ሥፍራዎች ለመንቀሳቀስ እና መንግሥት ላይ ለመዝመት ነው" ሲሉም ተደምጠዋል።
አምባሳደሩ፤ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች በተኩስ አቁም ንግግሮች ላይ መሳተፏን ተቃውመዋል። ለዚህም በምክንያትነት የጠቀሱን በአገሪቱ መንግሥት የሚነሳውን የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ለፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መሣሪያ እና የውጭ ተዋጊዎችን ታቀርባለች የሚል ክስን ነው።















