ሱዳን ውስጥ በሐዘን ሥነ ሥርዓት ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት በርካቶች ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty Images
በሱዳን ሰሜናዊ ኮርዶፋን ግዛት ውስጥ በሱዳን ጦር ቁጥጥር ሥር በምትገኘው ኤል ኦቤድ ከተማ አቅራቢያ በሐዘን ሥነ ሥርዓት ላይ በተፈጸመ የድሮን ጥቃት ቢያንስ 40 ሰዎች መገደላቸውን ባለሥልጣናት እና አክቲቪስቶች ተናገሩ።
ሰኞ ዕለት አል ሉዊብ ተብላ በምትጠራው መንደር ድንኳን ውስጥ ተሰብስበው በነበሩ ለቅስተኞች ላይ ለተፈጸመው ጥቃት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይልን (አርኤስኤፍ) ተጠያቂ አድርገዋል። ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ እስካሁን ስለ ጥቃቱ አስተያየት አልሰጠም።
በጥቃቱ የተጎዱ አብዛኛዎቹ ሰዎች ሕይወታቸው ያለፈው ኤል ኦቤድ ውስጥ ወደሚገኝ ሆስፒታል እየተወሰዱ ሳሉ እንደሆነ ተነግሯል። ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላት ኤል ኦቤድ፤ የሱዳንን ዋና ከተማ ኻርቱም በምዕራብ ከሚገኘው ዳርፉት ግዛት ጋር የምታገናኝ ከተማ ነች።
በነዳጅ ሀብት በበለጸገው ኮርዶፋን ውስጥ የሚደረገው ውጊያ እየተጠናከረ የመጣ ሲሆን 20 ሺህ ገደማ ነዋሪዎችም ወደ ኤል ኦቤድ ሸሽተዋል። ነዋሪዎቹ የተፈናቀሉት ከሳምንት በፊት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በግዛቱ ውስጥ የምትገኘውን ባራ ከተማን መቆጣጠሩን ተከትሎ ነው።
ከተማዋ የተያዘችው በዳርፉር የሱዳን ጦር ጠንካራ ይዞታ የነበረችው ኤል ፋሸር ከተማ አርኤስኤፍ እጅ በተገባችበት ተመሳሳይ ጊዜ ነው።
የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተዋጊዎች ኤል ፋሸርን ከተቆጣጠሩበት ጊዜ አንስቶ የጅምላ ግድያ፣ ወሲባዊ ጥቃት፣ አፈና እና ሰፊ ዝርፊያ እንደፈጸሙ መረጃዎች ያመለክታሉ።
የተባበሩት መንግሥታት፤ የአርኤስኤፍ ተዋጊዎች ባራ ከተማ ውስጥም ከሕግ ውጪ የሆኑ ግድያዎችን እንደፈጸሙ መረጃዎች እንደደረሱት አስታውቋል።
የአርኤስኤፍ መሪ ተፈጽመዋል የተባሉ "ጥሰቶችን" ለመመርመር ቃል ገብተዋል። የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ኤል ፋሸር ውስጥ የተፈጸመው ግድያ ማንነት ላይ ያነጣጠረ እና አረብ ባልሆኑ ሰዎች ላይ የተፈጸመ ስለመሆኑ በሰፊው የሚቀርበውን ውንጀላ ውድቅ አድርጓል።
ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት በበኩሉ፤ ይህ ዓይነቱ ድርጊት የጦር ወንጀል እና በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል ተብለው ሊፈረጁ እንደሚችሉ አስጠንቅቋል።
ፍርድ ቤቱ ይህንን መግለጫ ያወጣው የምግብ ደኅንነት ላይ የሚሠራ ዓለም አቀፍ ቡድን ባለሙያዎች የሰጡትን ማረጋገጫ ተከትሎ ነው። ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ላለፉት 18 ወራት ኤል ፋሸር ላይ ባደረገው ከበባ ምክንያት የከተማዋ ነዋሪዎች በጠኔ እየተሰቃዩ መሆኑን ባለሙያዎቹ አረጋግጠዋል።
'ኢንተርግሬትድ ፎድ ሴኩዩሪቲ ፌዝ ኔትዎርክ' የተሰኘው ይህ በተመድ ዕውቅና የተሰጠው ቡድን፤ በደቡብ ኮርዶፋን ግዛት በምትገኘው ካዱግሊ ከተማም አስከፊ የረሃብ ደረጃ ላይ መድረሷን ገልጿል። ይህቺ ከተማም በተመሳሳይ በኤርኤሴፍ ከበባ ተደርጎባታል።
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ሱዳን ውስጥ የሚታየው ሰብአዊ ቀውስ በፍጥነት እየተባባሰ እንደሆነ በማስጠንቀቅ፤ በአገሪቱ የሚካሄደው ጦርነት በአስቸኳይ እንዲቆም ጠይቀዋል።
"ሱዳን ውስጥ ያለው አስከፊ ቀውስ... ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ ነው" ሲሉ ዶሃ ከተማ ውስጥ በተካሄደ ስብሰባ ላይ ተናግረዋል።
"ኤል ፋሸር እና በዙሪያው ያሉ አካባቢዎች... የመከራ፣ የረሃብ፣ የሁከት እና የመፈናቀል ማዕከል ሆኗል። ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ወደ ኤል ፋሸር ከገቡ ወዲህ ደግሞ ሁኔታው ከቀን ወደ ቀን እየተባባሰ ሄዷል" ማለታቸውን የፈረንሳዩ የዚና ወኪል ኤኤፍፒ ዘግቧል።















