የሱዳኑ አርኤስኤፍ ሰብአዊ ተኩስ አቁም ለማድረግ ተስማማ

በጄኔራል መሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ የሚመራው ቡድን ከ18 ወራት ከበባ በኋላ የኤል-ፋሸር ከተማን ተቆጣጥሯል

የፎቶው ባለመብት, Anadolu via Getty Images

የምስሉ መግለጫ, በጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ የሚመራው ቡድን ከ18 ወራት ከበባ በኋላ የኤል-ፋሸር ከተማን ተቆጣጥሯል

የሱዳኑ ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (አርኤስኤፍ) በአሜሪካ የቀረበውን የሰብአዊነት ተኩስ አቁም ስምምነት መቀበሉን ሐሙስ ዕለት አስታውቋል።

የሱዳን ወታደራዊ ጦር ግን እስካሁን ምላሽ አልሰጠም። አርኤስኤፍ መግለጫ ያወጣው በምዕራብ ዳርፉር የሚገኘውን የኤል-ፋሸር ከተማን ከተቆጣጠረ በኋላ ነው።

በከተማዋ ዙሪያ ለ18 ወራት ከበባ አድርጓል። ከበባው እንዲቆም የተባበሩት መንግሥታትን ተደጋጋሚ ጥሪ ችላ በማለቱ ለመሸሽ የማይችሉ ነዋሪዎችን ለረሃብ አጋልጧል።

በተባበሩት መንግሥታት የሚደገፈው ዓለም አቀፉ የረሃብ ክትትል ቡድን በከተማው ውስጥ የረሃብ ሁኔታዎች መከሰታቸውን አረጋግጧል።

አርኤስኤፍ በእግረኛ ወታደሮቹ የጅምላ ግድያ ሪፖርቶች ምክንያት ዓለም አቀፍ ተቃውሞ እያጋጠመው ቢሆንም ቡድኑ ክሱን አስተባብሏል። "ጥሰቶች" በግለሰቦች ደረጃ የተፈጸሙ መሆናቸውን አምኖ አንዳንዶቹን አስሯል።

እአአ በ2023 ነበር በሱዳን ጦር እና በአርኤስኤፍ መካከል የእርስ በእርስ ጦርነት የተጀመረው። ሁለቱም ወገኖች በጦርነቱ ወቅት የተለያዩ የተኩስ አቁም ሐሳቦችን ቢቀበሉም አንዳቸውንም አልተገበሩም።

በመስከረም ወር አሜሪካ፣ ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ከሳዑዲ አረቢያ እና ከግብጽ ጋር በመሆን ለሦስት ወራት የሚቆይ የሰብአዊ ስምምነት፣ ቀጥሎም ወደ ዘላቂ የተኩስ አቁም እና ወደ ሲቪል አገዛዝ ሽግግር የሚሄድ ሐሳብ አቅርበዋል።

የአርኤስኤፍ መግለጫ እንዳመለከተው "የጦርነቱን አስከፊ ሰብአዊ ውጤቶች ለመፍታት" እና "አስቸኳይ የእርዳታ አቅርቦት" እንዲደርስ ለመፍቀድ አራቱ አገራት ባቀረቡት የተኩስ አቁም ሐሳብ መስማማቱን ገልጿል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

ቡድኑ "የግጭቶቹን ዋና ዋና ምክንያቶች በሚፈታ" እና "ፍትሐዊ፣ ሁሉን አቀፍ እና ዘላቂ ሰላም ለመፍጠር ተገቢውን ሁኔታ በሚፈጥር" መንገድ ውይይት እንደሚጠብቅም አክሏል።

የአርኤስኤፍ መግለጫ ከመሰጠቱ በፊት የሱዳን የመከላከያ ሚኒስትር ሐሰን ካብሮን ማክሰኞ ዕለት የአሜሪካውን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር "ሰላምን ለማምጣት ላደረገው ጥረትና ሐሳብ" በብሔራዊ ቴሌቪዥን በተላለፈው ንግግራቸው አመስግነዋል።

ነገር ግን የሱዳን ሕዝብ ከአርኤስኤፍ ጋር ለሚያደርገው ውጊያ ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆናቸውን አክለዋል። "ለጦርነት የምናደርገው ዝግጅት ሕጋዊ እና ብሔራዊ መብት ነው" ብለዋል።

በናይሮቢ የሱዳን ኤምባሲ ኃላፊ መሐመድ ኦስማን አካሻ ረቡዕ ዕለት ለቢቢሲ እንደተናገሩት በአገሪቱ ጦር የሚመራው መንግሥት ጦርነቱን ለማስቆም የሚስማማው አርኤስኤፍ ከፈረሰ፣ መሣሪያዎቹን ካስረከበ እና መሪው ተጠያቂ ካደረገ ብቻ ነው።

"ስለ ተኩስ አቁም ሐሳብ ምንም መረጃ የለኝም። የማውቀው ነገር የሱዳን መንግሥት እና የሱዳን ሕዝብ ይህንን ሚሊሻ ለማሸነፍ ቆርጦ መነሳቱን ብቻ ነው" ብለዋል።

የአርኤስኤፍየ ተኩስ አቁም መግለጫ የመጣው አንድ የእርዳታ ድርጅት በሱዳን ውስጥ የማኅበረሰብ የምግብ ማብሰያዎች ሥራ ሊያቆሙ ከጫፍ መድረሳቸውን ጠቅሶ ካስጠነቀቀ በኋላ ነው።

በአካባቢው ማኅበረሰብ የሚተዳደሩት የምግብ ማብሰያዎች ዓለም አቀፍ የሰብአዊ ቡድኖች ለመድረስ አስቸጋሪ በሆኑባቸው አካባቢዎች ከመሆናቸውም ባለፈ በቸልተኝነት፣ በእጥረት እና በበጎ ፈቃደኞች ድካም ምክንያት የመዘጋት አደጋ እያጋጠማቸው ነው።

ከኢስላሚክ ሪሊፍ የወጣ አንድ ሪፖርት እንደሚያሳየው አብዛኛዎቹ ማብሰያ ጣቢያዎች በስድስት ወራት ውስጥ የመዘጋት አደጋ ተጋርጦባቸዋል።

ግጭቱ የተባበሩት መንግሥታት በዓለም ላይ ትልቁ የሰብአዊ ቀውስ ብሎ የጠራውን ቀውስ ፈጥሯል። ሱዳን ውስጥ ከ24 ሚሊዮን በላይ ሰዎች አጣዳፊ የምግብ እጥረት አጋጥሟቸዋል።

ከኤል-ፋሸር ከበባ ሸሽተው ከወጡት መካከል ብዙዎቹ በታዊላ በሚገኙ ጣብያዎች ውስጥ ይኖራሉ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ከኤል-ፋሸር ከበባ ሸሽተው ከወጡት መካከል ብዙዎቹ በታዊላ በሚገኙ ጣብያዎች ውስጥ ይኖራሉ

የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ኤጀንሲ እንደገለጸው ከቀናት በፊት በአርኤስኤፍ ቁጥጥር ሥር ከዋለው ኤል-ፋሸር ከ60 ሺህ በላይ ሰዎች ሸሽተዋል።

የቡድኑ ተዋጊዎች ከተማዋን ሲቆጣጠሩ ስልታዊ ግድያዎች እንደነበሩ ሪፖርት ተደርጓል።

ከበባውን ያመለጡ ሰዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት "የማይታሰብ" ስቃይ ያጋጠማቸው ሲሆን ለመሸሽ የሞከሩ ሰዎችን ተዋጊዎች ሲያሰቃዩም ተመልክተዋል።

"ፊት ለፊታችን የተገደሉ ሰዎችን አይተናል። ሰዎች ሲደበደቡ ተመልክተናል። በጣም አስፈሪ ነበር" ሲሉ ኤዝልዲን ሐሰን ሙሳ የተባሉ ነዋሪ ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት የኤል-ፋሸር መሪ ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ በኤል-ፋሸር ወታደሮቻቸው የፈጸሟቸውን እና "ጥሰቶች" ሲሉ የጠሩትን ጉዳይ እንደሚመረመር አስታውቀዋል።

በኋላ ላይም ኤል-ፋሸር ግድያዎችን በመፈጸም የተከሰሰ ተዋጊ መታሰሩን የሚያሳይ ቪዲዮ አውጥቷል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ከሳምንት በኋላ በኤል-ፋሸር ስላለው ሁኔታ አስቸኳይ ስብሰባ እንደሚያካሂድ አስታውቋል።