አንድ ብሪታኒያ 195 ሚሊዮን ዩሮ በማግኘት ትልቁ የሎተሪ አሸናፊ ሆነ

ሎተሪ

የፎቶው ባለመብት, PA Media

በ13 የአውሮፓ አገራት ማክሰኞ እና አርብ የሚወጣው 'ዩሮሚልስ' የተሰኘው ሎተሪ ከፍተኛው የተባለለት የ195 ሚሊዮን 707 ሺህ ዩሮ ዕጣን እስካሁን ማንነቱ ያልታወቀ አንድ ብሪታኒያዊ ግለሰብ አሸነፈ።

ከዚህ በፊቱ ከፍተኛው የሎተሪው አሸናፊ በዚህ ዓመት ሚያዚያ ወር ውስጥ የወጣ ሲሆን፣ አሸናፊዎቹ 184 ሚሊዮን ዩሮ በአንድ ጀምበር ይዘው ሄደዋል።

"ይህንን የሎተሪ ዕጣ ለያዘ ብሪታኒያዊ አስደናቂ ምሽት ይሆናል’’ ሲሉ የሎተሪ ድርጅቱ ከፍተኛ ኃላፊ የሆኑት አንዲ ካርተር ተናግረዋል።

"ሎተሪውን የቆረጡ ሰዎች ቲኬቶቻቸውን እንዲመለከቱ እና ዕድለኛው አሸናፊ ከሆኑ እንዲደውሉልን እንጠይቃለን’’ ሲሉም አክለዋል።

በሎተሪው ታሪክ 15 ብሪታኒያውያን ከ100 ሚሊዮን ዩሮ በላይ አሸንፈዋል።

ልዩ ልዩ የሎተሪ ገጠመኞች ያላቸው ዕድለኞች

በተለያዩ አገራት ሰዎች የሚጫወቱት እና የአሜሪካ መንግሥት የሚያዘጋጀው የሎተሪ ዕጣ ወደ መቶ ሚሊዮኖች ከፍ ማለቱን ከተመለከተች በኋላ የ55 ዓመቷ ላውራ ስፓርስ በኢንተርኔት ላይ ዕድሏን ለመሞከር ሎተሪውን ገዛች።

ታዲያ ሎተሪውን ከገዛች ከጥቂት ቀናት በኋላ ከአንድ ሰው ተልኮላት የነበረ ኢሜይል እየፈለገች ባለችበት ወቅት በማይፈለጉ የኢሜይል ማጠራቀሚያ [ፎልደሯ] ውስጥ የ3 ሚሊዮን ዶላር ሎተሪ ማሸነፏን የሚያሳይ መልዕክት አግኝታለች።

ሌላው ደግሞ በብሪታኒያ ገና በ17 ዓመቷ የአንድ ሚሊዮን ዶላር ሎተሪ ያሸነፈችው ጄን፣ ሎተሪው ሲደርሳት አንድ የአስተዳደር ቢሮ ውስጥ ቀላል ሥራ ነበረቻት። በኤደንብራ በአስተኛ አፓርታማ ውስጥ ከእናቷ ጋር ትኖርም ነበር።

መጀመሪያ ያደረገችው ውድ የሆነው ዝርያ ያለው የሳሎን ውሻ መግዛት ነበር። 'ፕሪንሰስ' ብላ ጠራቻት። ከዚያ ውድ የንግድ ስም ያለውን አንድ ቦርሳ መግዛት ህልሟ ነበር። እንዳሰበችውም የሉዊ ቪቶ ቅንጡ ፋሽን የእጅ ቦርሳ ገዛች።

በእነዚህ ሁለት ወጪዎች ብቻ 10 ሺህ ፓውንዶች እልም ብለው ሄዱ። ከዚያ በኋላ ግን ግራ ገባት። ሕይወቴ እላዬ ላይ ሲፈርስ ነበር የሚታየኝ ብላለች ከሦሰት ዓመት በፊት በሰጠችው አንድ ቃለ ምልልስ።

የ3 ሚሊዮን ፓወንድ ሎተሪ ደርሷት አዛውንትን የመንከባከብ ስራዋን የቀጠለችው ሱ ሪቻርድስ

የፎቶው ባለመብት, PA

የምስሉ መግለጫ, 3 ሚሊዮን ፓውንድ አሸናፊ የሆነችው ሱ ሪቻርድስ።

ሌላኛዋ አሸናፊ ሱ ሪቻርድስ በ2016 ወደ ቤቷ እየሄደች እግረ መንገዷን ሱፐር ማርኬት ገብታ ፈጣን ሎተሪ ገዛች። ነገሩን ከቁብም አልቆጠረችውም ነበር። ሎተሪውን ቤት ገብታ ፋቀችው። 3 ሚሊዮን ፓውንድ አሸናፊ አደረጋት።

ደስታዋ ወደር አልነበረምው። ከባሏ ጋር ወደ ኢሴክስ ከተማ ሄደው ቤት ገዙ። አራት መኪኖችን እላዩ ላይ መረቁበት። ከዚያ በኋላ ደግሞ ዓለምን ዞር ዞር ብለው ማየት ጀመሩ።

ነገር ግን አዛውንትን የመንከባከብ ሥራዋን አሁንም በሳምንት ለ90 ሰዓታት ታከናውነዋለች። ምክንያቷ ደግሞ "ሥራዬን ስለምወደው" የሚል ነው።