ትራምፕ የድንበር ጥበቃ ኃላፊያቸውን ተቃውሞ ወደበረታበት ሚኒሶታ ግዛት ላኩ

የትራምፕ አስተዳደር የድንበር ጉዳይ ኃላፊ የሆኑት ቶም ሆማን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ቶም ሆማን ሕጋዊ ሰነድ የሌላቸውን ስደተኞች ከአሜሪካ በማባረር ጉዳይ የትራምፕ ቀኝ እጅግ ሆነው ያገለግላሉ

በአሜሪካዋ ሚኒያፐለስ ከተማ አንድ አሜሪካዊ ግለሰብ በፌዴራል ፖሊሶች መገደሉን ተከትሎ በስፍራው የነበሩት ከፍተኛ የስደተኞች ቁጥጥር ኃላፊ ለቅቀው እየወጡ መሆኑን ዋይት ሐውስ አስታውቋል።

የድንበር ዘብ አዛዡ ግሪጎሬ ቦቪኖ እና ሌሎች የስደተኞች ቁጥጥር ባለሥልጣናት ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ የተደረጉ ሲሆን የትራምፕ ቀኝ እጅ የሚባሉት የድንበር ጥበቃ ኃላፊው ቶም ሆማን ወደ ሚኒሶታ ግዛት ይላካሉ።

ባለፈው ቅዳሜ አሌክ ፕሬቲ የተባለ አሜሪካዊ ዜጋ መገደሉን ተከትሎ በሚኒያፐለስ ከተማ ከፍተኛ ተቃውሞ ተቀስቅሷል።

ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ይህን መወሰናቸው ምናልባትም ስደተኞችን አፈላልጎ በመያዝ ከሀገር የማባረር ተግባራቸውን ለጊዜው ገታ ለማድረግ ማሰባቸውን ያሳያል ተብሏል።

ነገር ግን አሁንም የትራምፕ አስተዳደር ሕጋዊ ወረቀት የሌላቸው ስደተኞችን ከሀገር የማስወጣት ተግባሩን መቀጠሉን ጥናቶች ያሳያሉ።

ተቃዋሚዎች እና የፌዴራል ፖሊሶች የነበራቸውን አለመግባባት በስልኩ እየቀረፀ የነበረው ፕሬቲ ከመኮንኖቹ ጋር ተጋጭቶ በርካታ ጊዜ በጥይት ተመትቶ ሲወድቅ የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች ተለቀዋል።

ከግድያው በኋላ በከተማዋ የነበረውን ሁኔታ ሲከታተሉ የነበሩት ቦቪኖ ነበሩ።

የድንበር ዘብ ኃላፊው ከግድያው በኋላ ፕሬቲ የፌዴራል ፖሊሶችን "ለመጨፍጨፍ" አስቦ ነበር ማለታቸውን ቁጣውን አባብሶታል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

የሀገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስቴር በለቀቀው መግለጫ ግለሰቡ የእጅ ሽጉጥ ይዞ ስለነበር የፖሊስ መኮንኖቹ ራሳቸውን ለመከላከል ነው የተኮሱት ብሏል።

የዓይን እማኞች፣ የአካባቢው ባለሥልጣናት እና የሟች ቤተሰቦች ፕሬቲ በእጁ ስልክ እንጂ ሽጉጥ አልያዘም ሲሉ የሚኒስቴሩን መግለጫ አጣጥለዋል።

ወላጆቹ ገዢው መንግሥት "በጣም የሚያሳምሙ ውሸቶችን" አሰራጭቷል ሲሉ ወቀሳቸውን አሰምተዋል።

ከግድያው በፊት ቦቪኖ፤ ትራምፕ በተለያዩ ከተሞች ለሚያካሂዱት ስደተኞችን በቁጥጥር ሥር አውሎ ከሀገር የማባረር እርምጃ ቀንደኛው ሰው ነበሩ።

ግለሰቡ የፖሊስ መኮንኖቻቸው የሚያደርጉት 'ኦፕሬሽን' የሚያሳይ ተንቃሳቃሽ ምስል ማኅበራዊ ሚድያቸው ላይ አከታትለው በመለጠፍ ይታወቃሉ።

ቦቪኖን ተክተው ወደ ሚኒሶታ ግዛት የሄዱት በስደተኞች ጉዳይ ጠንከር ያለ አቋም ያላቸው ቶም ሆማን በቀጥታ ለፕሬዝደንቱ ሪፖርት ያደርጋሉ።

ሆማን በቀድሞው ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ አስተዳደር ወቅት ስደተኞችን ከሀገር የማባረር ተግባር ላይ ተሰማርተው ይሠሩ ነበር።

ቦቪኖ እና ሌሎች ባለሥልጣናት ከተማዋን ለቅቀው ይወጣሉ ቢባልም ሚኒያፐለስ ከተማ ሰኞ ዕለት በተቃውሞ ስትናጥ ውላለች።

"በርካታ ሰዎች ሥራቸውን መሥራት አልቻሉም። ከቤታቸው መውጣት አልቻሉም። ፍራቻ ላይ ናቸው" ሲሉ የሚኒያፐለስ እህት ከተማ የምትባለው ሴይንት ፖል ነዋሪ የሆኑት ጆርጅ ኮርዴሮ ተናግረዋል።

ፕሬቲ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ውስጥ በፌዴራል ፖሊስ የተገደለ ሁለተኛው አሜሪካ ዜጋ ሲሆን ከሁለት ሳምንታት በፊት ሪኔ ጉድ የተባለች ግለሰብ በተመሳሳይ በስደተኞች ቁጥጥር እና ጉምሩክ አስፈፃሚ (አይስ) ፖሊስ መገደሏ የሚታወስ ነው።

የአሜሪካ መገናኛ ብዙኃን ሰኞ ቦቪኖ ከመንበራቸው እንዲነሱ ተደርገዋል የሚል ዘገባ ቢያሰሙም የሀገር ውስጥ ደኅንነት ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ይህን አስተባብለዋል።

በትራምፕ ትዕዛዝ መሠረት 3 ሺህ ገደማ የሚሆኑ የድንበር ጥበቃ እና የአይስ ፖሊሶች በሚኒያፐለስ ከተማ ተሰማርተዋል። ይህ የከተማዋን ነዋሪዎች ብቻ ሳይሆን የግዛቲቱን ባለሥልጣናት እና የሁለቱንም ፓርቲዎች አባላት አስቆጥቷል።

ትራምፕ ሰኞ ከዲሞክራቶቹ የሚኒሶታ ግዛት አስተዳዳሪ ቲም ዋልዝ እና የሚኒሶታ ከተማ ከንቲባ ጄኮብ ፍሬይ ጋር እንደመከሩ ተነግሯል። ፕሬዝደንቱ በቅርቡ ሁለቱን ግለሰቦች መተቸታቸው አይዘነጋም።