የቀድሞው የኬንያ ምክትል ፕሬዝዳንት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የግድያ ሙከራ እንደተፈጸመባቸው ተናገሩ

ሪጋቲ ጋቻጓ

የፎቶው ባለመብት, AFP/Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ባለጸጋ የንግድ ሰው የሆኑት ፖለቲከኛው ሪጋቲ ጋቻጓ፤ በትውልድ ሥፍራቸው ማውንት ኬንያ ግዛት ታዋቂ ናቸው

ታዋቂው የኬንያ ተቃዋሚ ፖለቲከኛ ሪጋቲ ጋቻጓ እሑድ ዕለት የቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ላይ የግድያ ሙከራ ተደርጎብኛል አሉ።

በአውሮፓውያኑ 2024 በቀረበባቸው ክስ ምክንያት ከምክትል ፕሬዝዳንትነታቸው የተነሱት ጋቻጓ፤ በኒየሪ ግዛት በሚገኝ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሥርዓት አልባ የፖሊስ አባላት ጥይት እና አስለቃሽ ጭስ በመጠቀም ጥቃት ፈጽመዋል ሲሉ ከስሰዋል።

ጥቃቱ እንዲፈጸም ያዘዙት የቀድሞ አጋራቸው የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ናቸው ሲሉም ማስረጃ ሳያቀርቡ ወንጅለዋል። ፕሬዝዳንቱ የቀረበባቸውን ውንጀላ በተመለከተ አስተያየት አልሰጡም።

የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኪፕቹምባ ሙርኮመን የተፈጸመውን ድርጊት "ተቀባይነት የሌለው" ሲሉ ኮንነዋል።

ፖሊስ ምርመራ መጀመሩን ያስታወቀ ሲሆን እስካሁን ድረስ ምንም ዓይነት የአካል ጉዳት እንዳልደረሰ ገልጿል።

ለፖሊስ የደረሰው ሪፖርት እንደሚያመለክተው፤እሑድ ከቀኑ አምስት ሰዓት ገደማ ላይ በቅዱስ ጴጥሮስ አንግሊካን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ አስለቃሽ ጭስ ተወርውሮ የጸሎት ሥነ ሥርዓቱ ተስጓጉሏል።

በቤተ ክርስቲያኑ ቅጥር ግቢ ውስጥ የነበሩ በርካታ ተሽከርካሪዎች መጎዳታቸውን የገለጸው ፖሊስ፤ የዐይን እማኞች እንዲተባበሩ ጠይቋል።

ባለሀብት እና የፕሬዝዳንት ሩቶ ዋነኛ ተቃዋሚ የሆኑት ጋቻጓ፣ በደኅንነት አባሎቻቸው ታጅበው ደኅነነቱ ወደ ተጠበቀ ሥፍራ መወሰዳቸውን ተናግረዋል። በወቅቱ የነበረውን ሁኔታ የሚያሳዩ ፎቶዎችንም በኤክስ ገጻቸውን ላይ አጋርተዋል።

Skip podcast promotion and continue reading
የቢቢሲ አማርኛ ዩቲዩብ ቻናል

ዜና፣ ትንታኔ እና ታሪኮችን በምሥል እና በድምጽ ለማግኘት

ይህንን በመጫን ሰብስክራይብ ያድርጉ

End of podcast promotion

በኋላ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫም፤ ጥቃቱ "የተቀነባበረ ድራማ ነው" በሚል በመንግሥት ደጋፊ ጦማሪዎች የቀረበውን አስተያየት ውድቅ አድርገዋል።

"አስለቃሽ ጭስ ከየት እናገኛለን? ኤኬ-47 ጠመንጃ ከየት እናመጣለን?" ሲሉ 'ዴሞክራሲ ፎር ዘ ሲቲዝንስ' የተሰኘ ፓርቲ የሚመሩት የቀድሞ ምክትል ፕሬዝዳንት ጠይቀዋል።

የአገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሙርኮመን በበኩላቸው፤ ጥቃቱን የፈጸሙት ሰዎች ተይዘው ለፍትሕ እንደሚቀርቡ የፖሊስ አዛዡ ቃል እንደገቡላቸው ገልጸዋል።

በኤክስ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍም፤ "በየትኛውም ቦታ በተለይም ደግሞ በአምልኮ ሥፍራ ውስጥ የሚፈጸም የኃይል ድርጊት ተቀባይነት የለውም" ብለዋል።

"ፖሊስ ያለምንም ፍርሃት ወይም አድልዎ በቆራጥነት በመንቀሳቀስ ይህንን ድርጊት የደገፉ እና የፈጸሙ ግለሰቦችን በማኅበረሰቡ ውስጥ ያላቸውን ደረጃ ወይም ፖለቲካዊ ግንኙነት ከግምት ውስጥ ሳያስገባ እርምጃ መውሰድ አለበት" ሲሉም አሳስበዋል።

በኬንያ ሕገ መንግሥት መሠረት ጋቻጓ በሴኔቱ ጥፋተኛ መባላቸው በድጋሚ የመንግሥት መሥሪያ ቤትን እንዳይመሩ ያግዳቸዋል።

የቀድሞው ምክትል ፕሬዝዳንት የብሔር ክፍፍልን መቀስቀስ እና የመንግሥት ኃላፊነት ሲይዙ የገቡትን ቃለ መሃላ መጣስን ጨምሮ 11 ክሶች ቀርበውባቸዋል። ከእነዚህ ውስጥ በአምስቱ ጥፋተኛ ተብለዋል፤ እሳቸው ግን በክሶቹን በሙሉ ጥፋተኛ እንዳልሆኑ ተናግረዋል።

ይህም ቢሆን ግን ፖለቲከኛው በሚቀጥለው የአውሮፓውያኑ ዓመት በሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንደሚወዳደሩ ተናግረዋል። ጥፋተኛ የተባሉባቸውን ክሶች በተመለከተም ለአገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የይግባኝ አቤቱታ አቅርበዋል፤ ፍርድ ቤቱ እስካሁን ድረስ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ አልሰጠም።

በ2022 በተደረገው ምርጫ ፕሬዝዳንት ሩቶ እና ጋቻጓ ወደ ሥልጣን የመጡት አንድ ላይ ተወዳድረው ነበር።

ሩቶ ከቀድሞ ምክትል ፕሬዝዳንታቸው ጋር ያደረጉት ጥምረት በኬንያ መራጮች ዘንድ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የኪኩዩ ተወላጆች በሚገኙበት ማውንት ኬንያ አካባቢን በከፍተኛ ድምጽ እንዲያሸንፉ አስችሏቸዋል።