ትራምፕ በቅርቡ አምባገነን ያሏቸውን ዘለንስኪን "ጀግና" ሲሉ አወደሱ

ቮሎድሚር ዘለንስኪ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለዩክሬኑ አቻቸው ቮሎድሚር ዘለንስኪ "ከፍተኛ ክብር" እንዳላቸው ገለጹ።

ትራምፕ ይህንን ያሉት ከፕሬዚዳንት ዘለንስኪ ጋር በዋይት ሐውስ አርብ ያደርጉታል ከተባለው ውይይት ቀደም ብሎ ነው።

በቅርቡ አምባገነን ብለው ፕሬዚዳንቱን መወረፋቸውን አስመልክቶ ቢቢሲ ይቅርታ ይጠይቁ እንደሆነ ላቀረበላቸው ጥያቄ "ይህንን መናገራቸውን ማመን እንዳልቻሉ" ገልጸዋል። በተጨማሪም ፕሬዚዳንት ዘለንኪን "በጣም ጀግና" ሲሉ አወድሰዋቸዋል።

ትራምፕ ፕሬዚዳንት ዘለንስኪን ያወደሱት በዩክሬን እና በሩሲያ መካከል ያለውን ጦርነት ለማስቆም ከዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ኪር ስታርመር ጋር ከተነጋገሩ በኋላ ነው።

አርብ ዕለት ከዘለንስኪ ጋር የሚደረገውን ውይይት "በጣም ጥሩ" ሊሆን እንደሚችል ግምታቸውን ያስቀመጡት ትራምፕ ሰላምን ለማስፈን የሚደረጉ ጥረቶች "በሚፈለገው ፍጥነት እየሄዱ ነው" ብለዋል።

ትራምፕ የዩክሬኑን ጦርነት ለመቋጨት ከሩሲያ ጋር የተናጠል ውይይት በሳዑዲ አረቢያ ማካሄዳቸው ምዕራባውያን አጋሮቻቸውን ያስደነገጠ ሆኗል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ ጦርነቱን በመጀመር ዘለንስኪን ወንጅለው እንዲሁም "ድርድር ላይ ቀደም ብሎ መድረስ ይችል ነበር" ሲሉ ወቅሰዋቸዋል።

"ሶስት ዓመታት ፈጅቷል። መቋጨት ትችል ነበር። በፍጹም [ጦርነቱን] መጀመር አልነበረብህም። ድርድር ላይ መድረስ ትችል ነበር" ሲሉ ባለፈው ማክሰኞ የተናገሩት።

ነገር ግን ትናንት ሐሙስ ከሰር ኬር ጋር ከተገናኙ በኋላ ትራምፕ ከዘለንስኪ ጋር ስለሚኖራቸው ውይይት ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ " በጣም ጥሩ ውይይት የምናደርግ ይመስለኛል። በደንብ እንግባባለን" የሚል ምላሽ ነው የሰጡት።

የቢቢሲው ጋዜጠኛ ዘለንስኪ አሁንም "አምባገነን" ናቸው ብለው ያስቡ እንደሆነ ላቀረበላቸው ጥያቄ " ይህንን ብዬ ነበር? እንደዚያ ማለቴን ማመን አልችልም" ሲሉ መልሰዋል።

ዘለንስኪ ለጦርነቱ ሰላማዊ ዕልባት ለመስጠት የሚደረጉ የሰላም ድርድሮች ለአገራቸው የደህንነት ዋስትናዎችን የሚያስገኝ እንዲሆን ተስፋን ሰንቀዋል።

በሰላም ውይይቱ ላይ የተጠየቁት ትራምፕ "ለብዙ ነገሮች ክፍት እንደሆኑ" ገልጸው ነገር ግን ድርድሩነ ለማስፈጸም ምን ዓይነት እርምጃዎች ይተገበራሉ የሚለውን ከመወሰናቸው በፊት ሩሲያ እና ዩክሬን ስምምነት ላይ መድረስ አለባችው ብለዋል።

ዘለንስኪ አርብ በሚያደርጉት ጉብኝት አሜሪካ የዩክሬንን ብርቅዬ ማዕድናትን ማግኘት የሚያስችላትን ስምምነት ይፈራረማሉ ተብሎ ይጠበቃል።

ትራምፕ አሜሪካ በዩክሬን የማዕድን መዳረሻ ካገኘች ሩሲያ ለወደፊቱ ልታደርሰው የሚችለውን ጥቃት የሚከላከል እንደሆነ ጠቁመዋል።

"ማስቆሚያ ነው ማለት ይቻላል። አሜሪካ በዩክሬን ተገኝታ ከበርካታ ሰራተኞቿ ጋር የሚያስፈልጋትን ማዕድን እያወጣች ማንም አይደፍረንም" ብለዋል።

የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ወታደሮቻቸው የሰላም አስከባሪ ኃይል አካል ሆነው በዩክሬን እንዲሰፍሩ ለመላክ አገራቸው ዝግጁ መሆናቸውን አስረድተዋል።