በአዲስ አበባ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ተግባር ይፈጸምባቸዋል የተባሉ ሆቴሎች ተዘጉ

የፎቶው ባለመብት, A.A City Admin
በአዲስ አበባ ከተማ የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ተግባር ይፈጸምባቸዋል የተባሉ የንግድ ተቋማት የመዝጋት እርምጃ መጀመሩን የከተማው አስተዳደር አስታወቀ።
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ ቢሮ ከከተማዋ ፖሊስ ጋር በመተባበር የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት ተግባር ይፈጸምባቸዋል ብሎ በጠረጠራቸው ሆቴሎችን፣ ባሮችን እና ሬስቶራንቶችን እያሸገ መሆኑን አስታውቋል።
ቢሮው “ከነባሩ የአገራችን ባህል፣ ወግ፣ የአኗኗር ሥርዓት እና ሃይማኖቶች ባፈነገጠ መልኩ የግብረ-ሰዶም ተግባር በሚያስፈጽሙ ሆቴሎች፣ ሬስቶራንቶች፣ ፔንሲዮኖች እና መሰል የመዝናኛ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ ከሕብረተሰቡ በሚደርሰው ጥቆማ መሠረት አስተማሪ እርምጃ” መውሰድ ጀምሪያለሁ ብሏል።
የከተማው አስተዳደር “በሰውም በአምላክም ዘንድ የተጠላ ድርጊት በሚፈጽሙ እና በሚያስፈጽሙ” ተቋማት ላይ ካለ አንዳች ርህራሄ እርምጃ መውሰዴን አጠናክሬ እቀጥላለሁ ያለ ሲሆን፣ ጥቆማ መቀበያ አማራጭ ስልኮችንም አስተዋውቋል።
ከሰሞኑ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ በስፋት የተሰራጨ ያልተረጋገጠ መረጃን ተከትሎ በአገሪቱ የተመሳሳይ ጾታ የሚቃወሙ ድምጾች በስፋት ሲሰሙ ቆይተዋል።
ይህን ተከትሎ በቅርቡ በኢትዮጵያ የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪ በሆኑ እና ናቸው በተባሉ ሰዎች ላይ ያልተጠበቀ ጥቃት እየተሰነዘረ መሆኑን የተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን መብት ተሟጋች የሆነው ቤተ ጎራማይሌ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።
ቡድኑ በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጭ ያሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች መሰል ጥቃቶችን እንዲያወግዙ ጠይቆ ማኅበራዊ ሚዲያ አስተዳዳሪዎችም በተመሳሳይ ጾታ አፍቃሪያን ላይ የኃይል እምጃ እንዲወሰድ ጥላቻን በሚያስተላልፉ ላይ እርምጃ እንዲወስዱ ጠይቋል።
የተመሳሳይ ጾታ ግንኙነት በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ ሥነ-ሥርዓት የሚያስቀጣ ሲሆን፣ በአገሪቱ ያሉ የእምነት ተቋማትም ይህንን ሁኔታ በጽኑ ያወግዙታል።








