ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"የወሊድ ምጣኔን ለማሳደግ ከውጭ አገር ሴቶችን እናስገባ" ያሉ የደቡብ ኮሪያ ባለሥልጣን ከፓርቲያቸው ተባረሩ
በደቡብ ኮሪያ እያሽቆለቆለ ያለውን የወሊድ ምጣኔ ለመጨመር "ከቬትናም ወይም ከሲሪ ላንካ ወጣት ሴቶችን እናስመጣ" ያሉ ባለሥልጣን ከፓርቲያቸው ተባረሩ።
የደቡባዊ ጂንዶ አውራጃ ኃላፊ የሆኑት ኪም ሂ ሶ ይህን አስተያየታቸውን የሰጡት ባለፈው ሳምንት ባካሄዱት ስብስባ ወቅት ነበር።
ኪም በንግግራቸው "ሴቶቹ በገጠር አካባቢ የሚገኙ ወጣት ወንዶችን ሊያገቡ ይችላሉ" ብለዋል።
ይህ የባለሥልጣኑ አስተያየት የተሰማው በዓለም ዝቅተኛ የወሊድ ምጣኔ ያላት ደቡብ ኮሪያ ምጣኔውን ለማሳደግ እየታገለች ባለችበት ወቅት ነው።
እያሽቆለቆለ ያለው የወሊድ ምጣኔዋ አሁን ላይ ያላትን 50 ሚሊዮን ሕዝቧን በ60 ዓመታት ውስጥ በግማሽ እንዲቀንስ ሊያደርገው ይችላል።
ምንም እንኳን ኪም በንግግራቸው ማንሳት የፈለጉት ይህንኑ "የወሊድ ምጣኔ ችግር" እንደሆነ ቢገልጹም በቴሌቪዥን የተላለፈው አስተያየታቸው በበጎ አልተወሰደም።
ይልቁኑ በቬትናም ዲፕሎማሲያዊ ተቃውሞ እንዲነሳ፣ የሕዝብ ቁጣ እንዲቀሰቀስ እና እርሳቸውም ከገዥው ዲሞክራቲክ ፓርቲ እንዲባረሩ ምክንያት ሆኗል።
የፓርቲው ቃል አቀባይ ሰኞ ዕለት ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት የዲሞክራቲክ ፓርቲ ጠቅላይ ምክር ቤት ኪምን ለማባረር ድምጽ ሰጥቷል።
ኪም ከስብሰባው ከአንድ ቀን በኋላ ለንግግራቸው ይቅርታ በመጠየቅ ቁጣውን ለማብረድ ያደረጉት ጥረት አልተሳካም።
ስብሰባው የተጠራው ጂንዶ አውራጃ የሚገኝበትን ግዛት እና በአቅራቢያ ያለች ከተማ ውህደት ላይ ለመወያየት ነበር።
በአገሪቷ የሕዝብ ብዛታቸው እየቀነሰባቸው ያሉ አካባቢዎች በአስተዳደር ምክንያት ከሌሎች ጋር መዋሃድን ይፈልጋሉ።
ኪምም በአስተያየታቸው የሰነዘሩት በገጠር አካባቢ ያለውን የሕዝብ ብዛት ጉዳይ ለማንሳት ፈልገው እንደነበር ፤ ነገር ግን የተጠቀሙት አገላለጽ "ትክክል እንዳልነበር" መናገራቸውን የአገሪቷ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
የደቡብ ጂኦላ ግዛትም "የቬትናም ሕዝቦች እና ሴቶችን አሳዝኗል" ሲል ለኪም ያልተገባ አስተያየት ይፋዊ ይቅርታ መጠየቁ ተዘግቧል።
በሴዑል የሚገኘው የቬትናም ኤምባሲ በበኩሉ በፌስቡክ ገጹ ባወጣው መግለጫ "የኪም አስተያያየት የአገላለጽ ችግር ብቻ ሳይሆን፣ ለስደተኛ ሴቶች እና አነስተኛ ቁጥር ላላቸው ማኅበረሰቦች ያለውን ዋጋ እና አመለካከት ያሳየ ጉዳይ ነው" ሲል አውግዞታል።
የሲሪ ላንካ ባለሥልጣናት የተፈጠረውን ውዝግብ ተከትሎ በይፋ ያሉት ነገር የለም።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሴቶች እና የስደተኞች መብት ተሟጋቾች የኪምን አስተያየት በመቃወም ማክሰኞ በጂንዶ አውራጃ አስተዳደር መሥሪያ ቤት ፊት ለፊት ሰልፍ ለማካሄድ ማቀዳቸው ተነግሯል።