ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ከማኅበራዊ ሚዲያ ቪዲዮ አልፈው ገበያቸው በመላው ዓለም የደራው የኮሪያ የውበት መጠበቂያዎች
የቀንድ አውጣ ፈሳሽ (ለሃጩ) በመላው ዓለም የቆዳ ውበት መጠበቂያ ዋነኛ ምሥጢራዊ ግብዓት ይሆናል ብሎ ማን ገመተ?
ነገር ግን እውን ሆኗል። የቆዳ ውበት መጠበቂያ የሆነው ይህ የቀንድ አውጣ ዝልግልግ ፈሳሽ የቲክቶክ ማስታወቂያ ከመሆን አልፏል።
ይህም 'ኮስአርኤክስ' የተባለውን የደቡብ ኮሪያ አነስተኛ ማምረቻን በመላው ዓለም እንዲሠራጭ አድርጎታል።
አሁን 'አሞሬፓስፊክ' በተባለው የደቡብ ኮሪያ ግዙፍ የውበት መጠበቂያ አምራች ኩባንያ ስር ሆኗል።
የሚያጣብቀው ፈሳሹ ሲረሙ በአጭር ጊዜ በመላው ዓለም መዳረሱ የኮሪያ የውበት መጠበቂያ ምርቶች በስፋት ውጤታማ እየሆኑ እንደሆነ ይነግራል።
እንከን የለሽ ለመምሰል መሞከር በማኅበረሰብ ውስጥ ውድድር በሆነበት በዚህ ጊዜ በስፋት በተሠራጩ የማኅበራዊ የትስስር ገፅ ይዘቶች እና የፋሽን አዝማሚያዎች ተገፋፍቶ አሁን ላይ ትልቁ የደቡብ ኮሪያ ኢንደስትሪ ነው።
የአገር ውስጥ ገበያው ብቻ እንኳን በ2024 13 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ነው። የምርቱ ሽያጭም በእጥፍ ያድጋል ተብሎ ይጠበቃል።
ከአገር አልፎ የተቀረው ዓለም በኮሪያ የውበት መጠበቂያ ምርቶች ፍቅር ወድቋል። ምንአልባት የኮሪያ ሙዚቃ (ኬ-ፓፕ)፣ የኮሪያ ፊልም (ኬ-ድራማ) ዓለም አቀፍ ክስተት በመሆናቸው ያን ያህል አያስገርምም።
'ኬ-ቢውቲ' እየተባለ በጅምላ የሚጠራው የኮሪያ የውበት መጠበቂያ ምርት አሁን በቸርቻሪዎች መደርደሪያ ትልቅ ቦታ እያገኘ ነው።
በ2025 ግማሽ ዓመት ደቡብ ኮሪያ የዘመናዊ የውበት መጠበቂያ እናት የምትባለውን ፈረንሳይ በመቅደም እና ዩናይትድ ስቴትስን በመከተል የዓለማችን ሁለተኛ ግዝፍ የውበት መጠበቂያ ምርቶች ላኪ አገር ሆናለች።
በቲክቶች፣ ኢንስታግራም እና ዩቲዩብ "የኮሪያ ቁዳ ውበት ጥበቃ" ብለው የመፈለጊያ ሳጥኑ ላይ ከሞላችሁ በተፅዕኖ ፈጣሪዎች ቪዲዮ ጎርፍ ትጥለቀለቃላችሁ። አንዳንዶቹ ተፅዕኖ ፈጣሪዎች በመቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተከታዮች ያሏቸው ናቸው።
የምርቱን ንጥረ ነገር እየነቀሱ፣ ከታሸገበት ሳጥን ሲያወጡ እያሳዩ "ከእኔ ጋር አብራችሁ ተዘጋጁ" የሚል ይዘት ያለው ቪዲዮ ይሠራሉ።
የውበት ተፅዕኖ ፈጣሪ እና በአሜሪካ መቀመጫውን ያደረገ የኮሪያ የውበት መጠበቂያ ምርድ የሆነው 'ክሬቭ ቢውቲ' መሥራች ሊያ ዩ "በጣም ብዙ ምርቶች እና መለያዎች (ብራንዶች) አሉ። እናም እንደ ደንበኛ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ምርቶች ትጋለጣላችሁ። በጣም የበዛ እና በውድድር ተሞላ ነው" ትላለች።
ከተወዳጅነቱ ጀርባ ያለው ቀመር
ከኮሪያ የውበት መጠበቂያ ምርቶች ውስጥ በፍነት እያደገ ያለ ፈጠራ አለ። አዲስ ቀመር የያዘ ምርት በየወሩ ብቅ ይላል።
እንደ የሳመን ዓሳ የዘር ፍሬ የያዘ ምርት ከዚህ ቀደም ለሸማቾች ያን ያህል ሳቢ አልነበረም። ዛሬ ግን ከለንደን እስከ ሎስ አንጀለስ ድረስ የመፀዳጃ ቤት መደርደሪያዎች ላይ ዋነኛ ምርቶች ናቸው።
ለዚህ ሽግግር ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃን ሁነኛ ሚና አላቸው። በዋና ከተማዋ ሴዑል ይፋ የሆኑ ምርቶች በአሜሪካ፣ በዩናይትድ ኪንግደም፣ በሕንድ እና በአውስትራሊያ ቲክቶክ እና ኢንስተግራም ወዲያው ብቅ ይላሉ።
ሆኖም ግን በተለይም በወጣቶች ላይ የቁንጅና አስተያየት ላይ እያረፈ ያለው የማኅበራዊ ጫና አሳሳቢ ነው። ባለሙያዎች በማኅበራዊ ትስስር ገፆች በተደጋጋሚ የቁንጅና ይዘቶችን መመልከት ጭንቀትን እንደሚያባብስ እና ለከፍተኛ ወጪ ይዳርጋል ሲሉ ያስጠነቅቃሉ።
የአሞሬፓስፊክ ኩባንያ ሥራ አስፈፃሚ ኪም ሴንግ-ሁዋን "ማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃንን ከመጠን በላይ መጠቀም ወይም በሥርዓት አለመጠቀም ለችግር ይዳርጋል" ይላሉ። አክለውም ስመ ጥር ኩባንያዎች የማኅበራዊ መገናኛ ብዙኃንን በደንብ ሚዛናዊ አድርገው ሊጠቀሙ ይገባል ብለዋል።
ይህ ችግር ኢንደስትሪው ወደ ምዕራባዊያን አገራት በደንብ ሲሠራጭ ማደጉ አይቀሬ ነው።
ሎሬል በ2024 የደቡብ ኮሪያውን ግዙፍ ኩባንያ የገዛ ሲሆን፤ ግዢው ከፍተኛ በተመጣጣኝ ዋጋ የኮሪያን የውበት መጠበቂያ ምርቶች በማቅረብ ፍላጎቱን ለመሙላት እንደሚያግዝ ገልጿል።
ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማትም ከኮሪያ ምርቶች ጋር የተያያዙ እንደ ሩዝ ውሃ ያሉ ንጥረ ነገሮችን በስፋት እየተጠቀሙ ነው።
አብዛኞቹ የደቡብ ኮሪያ የውበት መጠበቂያ አምራቾች ከአገሪቱ ግዝፍ ኩባንያዎች መሃል ናቸው።
አሞሬፓስፊክ ብቻዋን ግማሽ ያህሉን የአገር ውስጥ ገበያ ይሸፍናል። ይህን ያህል ግዙፍ ቢሆንም እንኳ ለአዲስ ሀሳቦች ሲል ትናንሽ አምራቾች ላይ ዐይኑን አያነሳም።
በ2024 አሞሬፓስፊክ 6.2 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ ምርቶችን ሸጧል። ኤልጂ ሀውስሆልድ እና ጤና የተባለ ሌላ ግዙፍ ድርጅት 4.1 ቢሊዮን ዶላር መሸጡን ሰነዶች ያሳያሉ። የሽያጩ መጠን በደቡብ ኮሪያ የወጪ ንግድ ላይም ጎልተው ይታያሉ።
በ2025 የመጀመሪያ ግማሽ ዓመት የወጪ ንግዱ 15 በመቶ ከፍ በማለት ታይቶ የማይታወቅ 5.5 ቢሊዮን ዶላር ሽያጭ ተፈፅሟል። የዚህ ምሥጢርም የአሜሪካ እና የአውሮፓ ገበያ ከፍ ማለቱ ሲሆን፤ ይህም ደቡብ ኮሪያ ከውበት መጠበቂያ የወጪ ንግዷ 10 ቢሊዮን ዶላር እንዲያልፍ አድርጓል።
ለአሞሬፓስፊክ ሥራ አስፈፃሚ ሁሉም ደንበኞች አንድ አይደሉም።
"እንደ ጃፓን፣ ኮሪያ እና ቻይና ያሉ አገራት ፍፁም የሆነ ቆዳን በሚመለከት የበለጠ ፍላጎት አለ። በአውሮፓ ሽቶ ዋነኛው ዘርፍ እና በአሜሪካ ደግሞ ሜካፕ የተሻለ ተወዳጅ ነው" ይላሉ።
"ነገር ግን ሁኔታዎች አሁን እየተቀየሩ ነው" ሲሉ የምዕራባዊያን ደንበኞች የወጣት ቆዳ እንዲኖራቸው እና ቆዳቸውን ከፀሐይ ለመጠበቅ ያላቸው ፍላጎች መጨመሩን ያመለክታሉ።
ከውድድሩ ጋር መሯሯጥ
እየጨመረ የመጣውን ፍላጎት ለማሟላት 30 ሺህ የሚሆኑት የደቡብ ኮሪያ የውበት መጠበቂያ አምራቾች ከፍተኛ ጫና አለባቸው።
ኩባንያዎቹ ምርምር፣ የቀመር እና የተለያዩ የምርት ዝርያዎችን በሚያመርት ክፍል ይታገዛሉ። አንዳንድ ትላልቅ ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን አነስተኛ ስም ባላቸው ኩባንያዎች አሠርተው ያቀርባሉ።
ውድድሩ እየተስፋፋ በሄደ ቁጥር ኩባንያዎች ግልፅ እንዲሆኑ እና ንጥረ ነገሮች ላይ እንዲያተኩሩ እንዲሁም ምርቶቻቸው ከስመ ጥር ሰዎች መተዋወቅ በላይ የተባሉትን እንዲሠሩ እንዲያደርጉ ጫና እየበረታባቸው ነው።
ታዋቂ የውበት ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆነችው ሚያ ቼን "አሁን ከትላልቅ ብራንዶች እየገዛን አይደለም። ስለ ንጥረ ነገሮች ነው እያወራን ያለነው፤ ከየት እንደሚገኝ፣ ምን እንደሚሠራ" ትላለች።
"አብዛኞቹ የኮሪያ የቆዳ ምርቶች ከተፈጥሯዊ ነገሮች ነው የሚገኙት፤ እና ሁላችንም ቆዳችን የጎንዮሽ ጉዳት እንዲደርስበት አንፈልግም።"
ኢንደስትሪው በገበያ መቀየርም እየተመራ ነው።
ቻይና አሁን ትልቋ የውጭ ገዢ አይደለችም። በኮሪያ እና በጃፓን ምርቶች ተጥለቅልቆ የነበረው ገበያ አሁን በራስ ምርት እየሸፈነ ነው።