ማዱሮ ከሥልጣን ይወርዳሉ ብሎ የተወራረደ አንድ ግለሰብ 436 ሺህ ዶላር አሸነፈ

ፖሊማርኬት

የፎቶው ባለመብት, LightRocket via Getty Images

ማዱሮ ከመታሰራቸው በፊት የቬንዙዌላው ፕሬዝደንት ከሥልጣን ይወርዳሉ ብሎ ቁማር የተጫወተ አንድ ግለሰብ 436 ሺህ ዶላር ማሸነፉ ተሰማ።

አንዳንዶች ግለሰቡ ምናልባትም የውስጥ መረጃ ይኖረው ይሆናል ሲሉ ጥርጣሬያቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።

ፖሊማርኬት በተሰኘው በክሪፕቶ የሚሠራው የቁማር ድርጅት ኒኮላስ ማዱሮ በአውሮፓውያኑ ጥር ወር መጨረሻ ከሥልጣን ይወርዳሉ ወይስ አይወርዱም የሚል ቁማር አጫውቷል።

ቅዳሜ ንጋት ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ የቬንዙዌላው መሪ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ይፋ ከማድረጋቸው በፊት በርካታ ሰዎች ሲቆምሩ እንደነበር ታይቷል።

ባለፈው ወር የቁማር መጫወቻ መድረኩን የተቀላቀለ አንድ ግለሰብ በቬንዙዌላ ጉዳይ 32 ሺህ 537 ዶላር መድቦ 436 ሺህ ዶላር ማሸነፉ ተሰምቷል።

ቁማሩን የተጫወተው ግለሰብ ማንነት እስካሁን ይፋ አልተደረገም። ማንነቱ ያልታወቀው ግለሰብ ስሙ በተደበላለቁ ቃላት እና ቁጥሮች የተሞላ ነው።

የፖሊማርኬት መረጃ እንደሚያሳየው ባለፈው አርብ ማዱሮ ከሥልጣን ይወርዳሉ የሚለው ቁማር 6.5 በመቶ ዕድል ብቻ ነበረው።

ነገር ግን አርብ ዕኩለ ሌሊት ገደማ ይህ ቁጥር ወደ 11 በመቶ ያደገ ሲሆን፣ ቅዳሜ ሊነጋጋ ሲል ደግሞ ቁጥሩ ወደ ላይ ሲመነደግ ተስተውሏል።

ትራምፕ ማዱሮ በቁጥጥር ስር ውሏል ሲሉ በትሩዝ ሶሻል ማኅበራዊ ሚድያቸው ይፋ ያደረጉት ቅዳሜ ንጋት ነው።

ፖሊማርኬት በጉዳዩ ላይ እስካሁን አስተያየት አልሰጠም።

ቤተር ማርኬትስ የተባለው ድርጅት ኃላፊ የሆነት ዴኒስ ኬሌሄር "ይህ ቁማር ግለሰቡ የውስጥ መረጃ እንዳለው የሚያሳይ ነው" ሲሉ በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር ለሆነው ሲቢኤስ ተናግረዋል።

ሌሎች ግለሰቦችም ማዱሮ ከሥልጣን ይወገዳሉ ብለው መድበው በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ዶላሮች ማሸነፋቸው ታውቋል።

አንዳንድ የሕግ ባለሙያዎች ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉት እንደሆነ ተሰምቷል።

የኒው ዮርክ ዲሞክራት የኮንግረስ አባል ሪቺ ቶሬስ የመንግሥት ሠራተኞች ከቁማሩ ጋር የተያያዘ መረጃ የማግኘት አቅም ካላቸው ቁማር እንዳይጫወቱ የሚከለክል ረቂቅ አዋጅ ሰኞ ዕለት ይፋ አድርገዋል።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት የቁማር ጨዋታዎች በአሜሪካ እየደሩ የመጡ ሲሆን፣ ፖሊማርኬት እና ካልሺ የተባሉ ድርጅቶች ከስፖርት ጀምሮ እስከ ፖለቲካ ባለው መስክ ሰዎች ቁማር እንዲጫወቱ ይፈቅዳሉ።

በአውሮፓውያኑ 2024 በተደረገው የአሜሪካ ምርጫ ማን ያሸንፋል በሚል በርካታ ሰዎች ቁማር የተጫወቱ ሲሆን አቁማር አጫዋች ኩባንያዎቹ በመቶ ሚሊዮን ዶላሮች እንዳጋበሱ ይታመናል።

ኢንዱስትሪው በባይደን ጊዜ ከመንግሥት በርካታ ቁጥጥሮች ይደረግበት የነበረ ሲሆን፣ በትራምፕ ዘመነ-መንግሥት ግን እንደልቡ እንዲንቀሳቀስ ተደርጓል።

የዶናልድ ትራምፕ ልጅ የሆነው ትራምፕ ጁኒየር የካልሺ እና ፖሊማርኬት አማካሪ ቦድር አባል ነው።