መነኮሳቱ ወደ ቬጋስ ተጉዘው ቁማር ለመጫዎት ገንዘብ የሰረቁት የሚሉና ሌሎች አጫጭር ዜናዎች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ሶማሊያ
በሶማሊያው ፕሬዚደንት ሞሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆ ላይ የቀረበው ክስ ውድቅ ተደረገ።
ይህ የሆነው የሃገሪቱ ሕግ አውጪ ምክር ቤት አባላት ፕሬዝዳንቱ እንዲከሰሱ የሚጠይቀውን የውሳኔ ሃሳብ የሚደግፉ በቂ የምክር ቤቱ አባላት ድጋፍ ማግኘት ባለመቻሉ ነው።
ኬንያ
ኬንያዊው እግርኳሰኛ አለን ምቦቴ በመብረቅ ተመትቶ ህይወቱ አለፈ።
ተጫዋቹ በመብረቅ የተመታው አብረውት የሚጫወቱት የቡድኑ አባላት ጎል አስቆጥረው እየጨፈሩ በነበረበት ወቅት ሲሆን ሌሎች 6 ተጨዋቾችም ጉዳት አጋጥሟቸዋል።
***
ኬንያ በ1፣ 5፣ 10፣ 20 ሳንቲሞቹ ላይ የነበረው የፕሬዚደንቶች ምስል በተለያዩ እንስሳቶች ምስል ልትተካ ነው።
ፕሬዚደንት ኡሁሩ ኬንያታ በቀጣይ ለመገበያያ የሚውሉት ሳንቲሞች የኬንያን ታሪካዊና ባህላዊ እሴት ያሳያሉ ብለዋል።
በተጨማሪም ማየት የተሳናቸው ሰዎችም ሳንቲሞቹን በቀላሉ መለየት እንዲያስችላቸው ሆነው ይሰራሉ ብለዋል ባለስልጣናቱ።
ሞዛምቢክ
የሞዛምቢክ መንግስት በሌሉበትና ባልሰሩበት ደመወዝ የሚከፈላቸው 30 ሺህ ሰራተኞች ማግኘታቸውን አስታወቀ።
በዚህ ምክንያት መንግስት ባለፉት 2 ዓመታት ብቻ ለ250 ሚሊየን ዶላር ኪሳራ እንደተዳረገ የመንግስት ሰራተኞች ሚንስትር ካርሜሊታ ናማሹላ አስታውቀዋል።
ደቡብ አፍሪካ
በደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን የሚገኝን መስጂድ ከባለስልጣናት ማስጠንቀቂያ ደረሰው።
የአካባቢው የጤና ጥበቃ ባለስልጣናት መስጂዱ የሚያሰማው አዛን የድምፅ ብክለት እያስከተለ ነው በሚል ደብዳቤ ጽፏል።
ጋምቢያ
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር የቀድሞ የጋምቢያ ፕሬዚደንትና ቤተሰቦቻቸው ወደ አሜሪካ እንዳይገቡ እግድ ጣለ።
ውሳኔው የተላለፈባቸው የሙስና ወንጀል ሰርተዋል በሚል ሲሆን ፕሬዚደንቱ በኢኳቶሪያል ጊኒ በስደት እየኖሩ ይገኛሉ።
ጋቦን
በጋቦን በቅርቡ የተሻሻለውን ህገ መንግስት በመቃወም ሰራተኞች አድማ መቱ።
ፕሬዚደንት አሊ ቦንጎ ለህክምና ከአገር በወጡበት ወቅት የአገሪቱ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚደንቱ የሚንስትሮች ምክርቤትን እንዲመሩ ህጉን በማሻሻሉ ነው።
ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ
በቅርቡ የኖቤል የሰላም ሽልማትን የተረከቡት ኮንጓዊ ዶክተር ደኒስ ሙክዌጂ በአገሪቱ በዚህ ወር ከሚካሄደው ምርጫ በኋላ ግጭቶች ሊፈጠሩ እንደሚችሉ ስጋታቸውን ገለፁ።
ስጋታቸው ምርጫው ነፃ፣ ፍትሃዊና ሰላማዊ አይሆንም የሚል ነው።
ዶክተር ደኒስ ሙክዊጂ የአስገድዶ መድፈር ለተፈፀመባቸው በአስር ሽህ የሚቆጠሩ ሴቶች ህክምና የሰጡ ዶክተር ናቸው።
አሜሪካ
በካሊፎርኒያ ከሚገኝ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ገንዘብ የሰረቁ መነኮሳት ጥፋታቸውን አመኑ።
መነኮሳቱ በላስቬጋስ ቁማር ለመጫወት ሲሉ 500 ሺህ ዶላር ተማሪዎች ለትምህርት ከከፈሉትና በእርዳታ ከተገኘ ገንዘብ ላይ እንዳጭበረበሩ ታውቋል።












