በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ላይ የሚያጠነጥን ዘጋቢ ፊልም ለእይታ ይበቃል ተባለ

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አርማ

የፎቶው ባለመብት, General Attorney Twitter Page

ባለፉት ዓመታት በእስር ጥላ ስር ይገኙ በነበሩ ዜጎች ላይ ተፈፅመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ላይ አትኩሮቱን ያደረገ ዘጋቢ ፊልም በተለያዩ የቴሌቭዥን ጣብያዎች ለእይታ እንደሚበቃ የጠቅላይ አቃቤ ህግ የኮሚኒኬሽን እና ህዝብ ግንኙነት ክፍል ኃላፊ አቶ ዝናቡ ቱኑ ገለፁ።

አቶ ዝናቡ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ዘጋቢ ፊልሙ እንደየቴሌቭዥን ጣብያዎቹ መርኃ ግብር ዛሬ ወይንም ነገ ለተመልካች ይደርሳል።

መስሪያ ቤታቸው መረጃ እንደማይደብቅ የተናገሩት አቶ ዝናቡ በበርካታ የቴሌቭዥን ጣብያዎች የመታየቱን ፋይዳ በዚሁ ምክንያት እንደሆነ ያስረዳሉ።

"እኛ ትክክለኛ ለሆነ ሚዲያ ሁሉ መረጃውን እንሰጣለን" ብለዋል ቃል አቀባዩ።

ከሳምንታት በፊት ከብረታ ብረት እና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን ጋር በተያይዘ ተፈፅመዋል በተባሉ ከባድ የሙስና ወንጀሎች ዙርያ የሚያጠነጥን ፊልም በመንግሥታዊ እና ከመንግሥት ጋር ይቀራረባሉ በሚባሉ የቴሌቭዥን ጣብያዎች ታይቶ የመወያያ ርዕስ ሆኖ እንደከረመ አይዘነጋም።

ተቺዎች እርምጃውን "የዘጋቢ ፊልም ፍርድ" ሲሉ የነቀፉት ሲሆን፤ ፍርድ ቤት ቀርበው ጥፋተኝነታቸው ያልተረጋገጠን ተጠርጣሪዎች ላይ ቀድሞ ብያኔ ያስተላለፈ ነው ሲሉ ቅዋሜያቸውን ገልፀዋል።

በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን በጋዜጠኞች ተጠይቀው የነበሩት አቶ ዝናቡ የፊልሙ ይዘት ለፍርድ ቤት ከተላከው የወንጀል ዝርዝር የተለየ ስላልሆነ በፍትሕ ሂደቱ ላይ ጣልቃ እንደመግባት አይቆጠርም ሲሉ ምላሽ መስጠታቸውም ይታወቃል።

ቢቢሲ ፊልሙ ይተላለፍባቸዋል ከተባሉ የቴሌቭዥን ጣብያዎች ከአንደኛው ያገኘው መረጃ አንደሚያሳየው ይህ 1ሰዓት ከ15 ደቂቃ ርዝማኔ ያለውዘጋቢ ፊልም ዛሬ ምሽት ከ2፡30 በኋላ የሚታይ ሲሆን፤ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈፅሞባቸዋል የተባሉ ተጠቂዎችን ምስክርነት ያካተተ ነው።